Site icon ETHIO12.COM

መሬት ከመንግስት ሰርቀዋል የተባሉ ተከሰሱ – አዲስ አበባ 120 የሌብነት ክስ ይመሰረታል

በህገወጥ መንገድ በአርሶ አደርና በአርሶ አደር ልጅ ስም የይዞታ መብት በማጽናት የመንግስት ባዶ ቦታን በወሰዱ እና እንዲወሰድ ባደረጉ 21 ግለሰቦች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የተቋቋመው የፀረ ሙስና ኮሚቴ 127 ክስ ለመመስረት የሚያስችሉ ጥቆማዎችን ማሰባሰቡን ገለፀ

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈፃሚን ጨምሮ በ21 ግለሰቦች በአርሶ አደርና በአርሶ አደር ልጅ ስም ለ11 ግለሰቦች ካርታ በማዘጋጀት 5 ሺህ 593 ካሬ ሜትር ይዞታን መብት በማፅናት እና አማካይ የሊዝ ዋጋው ከ11 ሚሊየን ብር የሆነ የመንግስት ባዶ ቦታን ወስደዋል እና እንዲወሰድ አድርገዋል በሚል ነው ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው፡፡

በዛሬው እለት ክስ የተመሰረተባቸው ተክሳሾች የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መልካሙ በቃናን ጨምሮ ሌሎች በተለያየ የአመራርነት እና በባለሙያነት እያገለገሉ የሚገኙ ግለሰቦች ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ግለሰቦቹ ከሌሎች ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያወጣውን መመሪያ ቁጥር 4/2007 መሰረት የይዞታ ማረጋጋጫ የሚጠይቅ ሰው ማሟላት የሚገባውን መስፈርት ያላሟሉ፣ በህገወጥ መንገድ አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጅ ነን ያሉ 11 ግለሰቦችን የይዞታ ካርታ በማዘጋጀት አማካይ የሊዝ ዋጋው ከ11 ሚሊየን 900 ሺህ 67 ብር ከ31 ሳንቲም የሆነ የመንግስት ባዶ ቦታን በመስጠት፣ የካርታ መብት በማፅናት እንዲሁም 5 ሺህ 593 ካሬ ሜትር ይዞታን በህገወጥ መንገድ ወስደዋል ሲል ዐቃቤ ህግ በክሱ ዘርዝሯል።

በአጠቃላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1 ሀ እና የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 9/1 ሀ እና ንዑስ ቁጥር 2 በመተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባበብ በመጠቀም በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።

እንደ ኤፍቢሲ ዘገባ ከተከሳሾቹ መካከል የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መልካሙ በቃና እና የክፍለ ከተማው የመሬት ማስከበር ጥበቃ ኦፊሰር ካርታ አረጋጋጭ ባለሙያ ገለታ ደበሌ ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በጽህፈት ቤት ከጠበቃቸው ጋር ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተቋቋመው የፀረ ሙስና ኮሚቴ 127 ክስ ለመመስረት የሚያስችሉ ጥቆማዎችን ማሰባሰቡን ገለፀ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ አደረጃጀት የተቋቋመው የፀረ ሙስና ኮሚቴ 127 ክስ ለመመስረት የሚያስችሉ ጥቆማዎችን ማሰባሰብ መቻሉን አስታወቀ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመውን የፀረ ሙስና ኮሚቴ ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፀረ ሙስና ኮሚቴ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ማቋቋማቸው ይታወቃል።

የኮሚቴው ሰብሳቢና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፤ ኮሚቴው ሁለት ንዑሳን ኮሚቴዎችን አደራጅቶ በይፋ ተግባራዊ የሥራ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረ ግዜ አንስቶ 127 ክስ ለመመስረት የሚያስችሉ የሙስና ጥቆማዎችን ከሕዝብ ማሰባሰብ መቻሉን ገልጸዋል።

ከ127 ከሕዝብ የተሰበሰቡ ጥቆማዎች መካከል 64ቱን በፍጥነት በመለየትና የክስ መዝገብ በማደራጀት ለሕግና ምርመራ ንዑስ ኮሚቴ መመራቱን ጨምሮ 37 ጥቆማዎች ላይ በቂ መረጃ በማሰባሰብ የክስ መዝገብ የማደራጀት ሥራ መሰራት መቻሉን ተናግረዋል ።

በቀሪዎቹ ከሕዝብ የተሰበሰቡ የሙስና ጥቆማዎች ላይም መረጃና ማስረጃ እንዲሁም የክስ መዝገብ የማደራጀት ስራ በዘላቂነት በንዑሳን ኮሚቴዎች በኩል እየተከናወነ ነው ያሉት ሰብሳቢዋ አጠቃላይ መረጃ የማሰባሰብና የክስ መዝገብ የማደራጀት ስራዎች ከፌደራል ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ጋር በቅንጅት የሚከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመረጃ ማሰባሰብ ሂደት እስካሁን እየመጡ ያሉ ጥቆማዎች የሚበረታቱና የተጀመረውን የፀረ ሙስና ትግል የሚያጠናክሩ ናቸውም ብለዋል።

ነዋሪዎች በዘላቂነት በ11 ክፍለከተሞች የተደራጁ የጥቆማ መስጫ ሳጥን አገልግሎትን ጨምሮ በተመረጡ ወሳኝ ተገልጋይ በሚበዛባቸው የሴክተር ተቋማት እንዲሁም በነጻ የስልክ መስመር 9977 ጥቆማ መስጠት የሂደቱ ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ ማቅረባቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ዜናው የኢዜአ ነው

Exit mobile version