Site icon ETHIO12.COM

በአክሲዮን የተቋቋሙ ኩባንያዎች የህዝቡን አንጡራ ጠራርገው ወዴት ሄዱ?

አክሲዮን በአቋራጭ መበልጸጊያ፣ በተቀደሰ ዓላማና አሳብ ላይ ተንተርሶ ዝርፊያ የተካሄደበት፣ በርካቶች እጃቸውን አጨብጭበው በባዶ የቀሩበት ወይም ብራቸው በስራ ማስኬጃ ስም ተሰልቅጦ… በአክሲዮን ስም የዜጎችን ሃብት ሰልቅጠው በውጭ አገር ” አገር ወዳድ ታጋና፣ ተንታኝ፣ የዘር ድርጅት ጠበቃ፣ በላምናምን የሆኑ ..” ብዙ ናቸው። ተሳክቶላቸው መልካም እርምጃ የተራመዱት እንዳሉ ሆነው፣ የህዝብ ሃብት ጨልፈው ስለተሸበለሉትና ሳይሽበለሉም … ሁሉንም ቤት ይቁጠረውና የውድነህን ዘነበን ጥቆማ እንዳለ አንብቡት።

አንድ ሰሞን- እንዲያው አንድ ሰሞን ብቻ በኢትዮጵያ ጠባብ ገበያ ውስጥ በአክሲዮን ሽያጭ የሚቋቋሙ ኩባንያዎች እንደ አሸን በዝተው ነበር። የተወሰኑ አደራጆች ሰብሰብ ብለው የአከሲዮን ማህበር ማቋቋም እንደ ፋሽን ሆኖ ነበር።

በቀላሉ እና በአቋራጭ ፈረንካ የማግኛም መንገድ ሆኖ ነበር። በሌላም በኩል በወቅቱ የተበታተነ የማኀበረሰብ ገንዘብ ተሰባስቦ ቁም ነገር የሚሠራበት ጊዜ መጣ ተብሎ ተስፋን አጭሮ ነበር።

በጊዜው ከህዝብ ገንዘብ ሰብስቦ ለመሥራት ያልተቋቋመ የአሲዮን ማኀበር የለም። የአክሲዮን ማኀበሮች በሁሉም የአገልግሎትና የኢንደስትሪ ዘርፎች ሥር ተቋቁመው ነበር።

በትራንስፖርት ዘርፍ እነአሊያንስ፤ በስኳር ዘርፍ ደግሞ እነ ሕብር ስኳር ይጠቀሳሉ። የኮንስትራክሽን ኩባንያ አቋቁመው የተበጣበጡ ፍርድ ቤት ድረስ የሄዱ ጎምቱ ጎምቱ ዶ/ር ኢንጂነሮችም የሚረሱ አይደለም። ጀነራል ሆስፒታል እናቋቁማለን ብለው የዲያስፖራን ዶላር ቅርጥፍ አድርገው የበሉ “ቢዝነስ ማኖች” እንዲሁ ብዙ ናቸው።

ማተሚያ ቤት ለመክፈት፣ እርሻ ለመሞከር፣ ግዙፍ ሱፐር ማርኬቶችን ለማቋቋም ያልተነሳ፣ ላይ ታች ያላለ ሰው እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ፈልጎ ለማጣት ያስቸግራል።

በወቅቱ የምርጫ 97 ግርግር ሰከን ካለ በኃላ በሚሊኒየም ዋዜማና ማግስት ወሬው ሁሉ “አክሲዮን…አክሲዮን…. አክሲዮን” ብቻ ነበር። የቲቪና ራዲዮ የአየር ሰአት፣ የጋዜጣና መጽሔት ገፆች በነዚሁ አደራጆች ማስታወቂያ የተሸፈነ ነበር። የሚዲያ ተቋማቱ አሪፍ ቢዝነስም እያገኙ ነበር።

የማህበረሰብ ገንዘብ ተሰባስቦ ተአምር እንደሚሰራ ምልክቶችም ታይተው ነበር። ለአብነት ያህል ዘቢደር ቢራ፣ ራያ ቢራ፣ ሃበሻ ቢራ፣ አክሰስ ሪል ስቴት፣ ሃኮማል ሪል ስቴት፣ ሃበሻ ሲሚንቶ ተቋቁመውም ነበር። የቢራ ፉብሪካዎቹ (ዘቢደርና ራያ) ቃላቸውን ጠብቀው ሥራ ቢጀምሩም በኢትዮጵያ የቢራ ገበያ ውስጥ አብላጫ ድርሻ ባለው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ተዋጡ። አክሰስ ሪል ስቴት ባለአክሲዮኖቹንም ሆነ ደንበኞቹን እንባ አራጭቶ -ጥጉን ያዘ። ሃኮማል አለ?

ሀበሻ ሲሚንቶ በውጭ ኩባንያ ተይዞ የነበረውን አክሲዮን በኢትዮጵያ ተጠቃሽ ባለሃብቶች አንዱ የሆኑት አቶ ጌቱ ገለቴ ገዝተውታል። ጌትአስ ኢንተርናሽናል በሃበሻ ሲሚንቶ የአምበሳውን ድርሻ በመያዙ የብዙሃኑ ባለአክሲዮኖች ዕጣ ፈንታ በቀጣይ አብረን የምናየው ይሆናል።

በሺዎች በሚቆጠሩ ባለአክሲዮኖች ትብብር የተቋቋመው ሃበሻ ቢራም መጨረሻው በኩባንያው ብዙ አክሲዮን ባላቸው የውጪ ባለሀብቶች ተሰልቅጦ ሊበላ መሆኑ እየተሰማ ነው።

ባንኮች፣ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ጨምሮ በግሉ ዘርፍ ብቻ ከአንድ ሺህ በላይ የአክሲዮን ኩባንያዎች ተቋቁመዋል። ከነዚህ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ጥቂት ናቸው። አብዛኛዎቹ የህዝቡን ገንዘብ አደፋፍተው ሩጫቸውን ጨርሰዋል። ያሉትም በተገቢው የመንግስት ጥበቃና ክብካቤ ስለማይደረግላቸው ጫጭተዋል።

የአክሲዮን ገበያው እንዲህ መሆኑ ያሳዝናል። መንግስት የህዝብን ሃብት መጠበቅ አለመቻሉ ያስተዛዝባል። ለባንክ እና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክን የአዘዘ መንግስት፣ የንግድ እና የአምራች አክሲዮን ኩባንያዎችን የሚቆጣጠር ጠንካራ ተቋም ለምን መመስረት እንደተሳነው ግራ ያጋባል።

ዋነኛው የአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጭ በዜጎች እጅ ያለ ገንዘብ ነው። ይህ ገንዘብ በቁጠባ፣ በአክሲዮን መሰባሰብ ሲችል ትልቅ አቅም ይፈጥራል። ለፍትሃዊ የሃብት ድርሻም ትልቅ ሚና ስለሚኖረው ለዘርፉ አጽንኦት መስጠት ያሻል።

ንግድ ሚኒስቴር ይሰማል!?

WZ news / #Wudineh Zenebe

Exit mobile version