የመንግሥትም ሆነ የግል ቀጣሪ ድርጅቶች ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ሠራተኞቻቸውን እና አዲስ ሠራተኞችን ከመቅጠራቸው በፊት የተቀጣሪዎቹን የትምህርት ማስረጃዎች ሕጋዊነት እና ትክክለኛነት መረጋገጥ እንደሚገባቸው የኢፌዴሪ ትምህርት እና ሥልጠና ባለሥልጣን አሳሰበ።
ተገልጋዮች ወይም ሕጋዊ ወኪሎች የማረጋገጫ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ባለሥልጣኑ ከመሔዳቸው በፊት የሚከተሉትን መስፈርቶች በማሟላት አገልግሎቱን ማግኝት እንደሚችሉም ገልጿል።
መስፈርቶቹም፦
1. በጀርባው ላይ የኮሌጁ ኃላፊ እና ሬጅስትራር ፊርማ እና ማህተም ያለበት ኦሪጅናል ዲግሪ ከኮፒ ጋር በማያያዝ፤
2. በጀርባው ላይ የኮሌጁ ኃላፊ እና ሬጅስትራር ፊርማ እና ማህተም ያለበት ኦሪጅናል ትራንስክሪፕት/Student Copy/ ከኮፒ ጋር በማያያዝ፤
3. ዲግሪውን ለመማር በመግቢያነት የተያዘ ኦሪጅናል ዲፕሎማ ወይም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሰርቲፊኬት ከኮፒ ጋር በማያያዝ፤
4. ዲግሪውን ለመማር በመግቢያነት የተያዘው የ12ኛ ክፍል ሰርተፊኬት ከሆነ በትምህርት ምዘናዎች እና ፈተናዎች አገልግሎት ድርጅት ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ ከኮፒ ጋር በማያያዝ፤
5. ዲግሪውን ለመማር በመግቢያነት የተያዘው ዲፕሎማ ከሆነ ዲፕሎማው በተገኘበት ክልል የቴክኒክ እና ሙያ ኤጀንሲ ወይም የዞን/የከተማ መስተዳደር የሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ እንዲሁም የደረጃ 4 ብቃት ማረጋገጫ(COC) ካገኙበት ማዕከል የተረጋገጠ መሆን አለበት ከኮፒ ጋር በማያያዝ እና
6. የስም ለውጥ ካለ የፍርድቤት ውሳኔ ከኮፒ ጋር በማያያዝ ናቸው።
ዘገባ EBC