“ማን ነው?” ጥያቄ “ክፈት” መልስ – በፖሊስ መለያ የተፈጸመ ወንጀል

ቀኑ የካቲት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር። ብሩህ፣ ፍክት ያለ ቀን። ብዙ ሰው ማልዶ ወደ ጉዳዩ ለመድረስ ጠደፍ ጠደፍ እያለ የሚንቀሳቀስበት ማለዳ። ሁሴን አህመድ ኦይል ሊቢያ፣ የመኪና ዘይት እና ቅባቶች ማከፋፈያ ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችም በጠዋቱ ነው የሥራ ገበታቸው ላይ የተገኙት። እንደወትሯቸው አስፈላጊውን የሥራ ዝግጅት አድርገው ደንበኞቻቸውን እየተጠባበቁ ነው።

በዕለቱ ከወትሮው የተለየ እንቅስቃሴ ባይኖርም ረፈድፈድ ሲል ግን ስድስት የሚሆኑ ሰዎች ወደ ድርጀቱ ገቡ። የሰዎቹ በአንዴ መምጣት ግርምታን ቢፈጥርም ቀልጣፎቹ የድርጅቱ ሠራተኞች ግን የተለመደው ትህትና በተሞላበት አቀራረብ ግር ብለው የገቡትን ተገልጋዮች ተቀብለው ማስተናገድ ጀመሩ።

ሰዎቹ ግን በትህትና የተቀበሏቸውን ሠራተኞች መስተንግዶ ከመሻት ይልቅ ዓይናቸው እዚህም እዚያም ይቅበዘበዝ ነበር። እጃቸውም ይሄንንም ያንንም እያነሳ ይጥላል፤ እዚህም እዚያም በመርገጥ ትንሽ ወከባ የሚመስል ነገር ከፈጠሩ በኋላ ምንም ዓይነት ነገር ሳይገዙ ድርጅቱን ለቀው በሰላም ይወጣሉ።

በተጠንቀቅ ሥራቸውን ሲሠሩ የነበሩት የድርጅቱ ሠራተኞች በሁኔታው ግራ ቢጋቡም ሰዎቹ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳያደርሱ በመውጣታቸው ተረጋግተው የዕለቱ ሥራቸውን መሥራት ጀመሩ።

በአቶ አባይነህ ወርቁ እየተመራ ሁሴን አህመድ ኦይል ሊቢያ የመኪና ዘይት እና ቅባቶች ማከፋፈያ ድርጅት ውስጥ የገባው ቡድን ለዝግጅት በቂ የሆነ መረጃ መያዙን እንዳረጋገጠ ነበር ድርጅቱን ለቆ የወጣው። በወከባና በማደናገር መካከል መውጫ መግቢያውን በተገቢው መልኩ እንዲያጠኑ ተልዕኮ የወሰዱት ገብረ አበሮች ተገቢውን መረጃ ማግኘታቸውን ካረጋገጡ በኋላ በዓይን ጥቅሻ ምልክት ሰጥተው ወደ መሰብሰቢያ ቦታቸው አቀኑ።

የዘራፊው ቡድን ዝግጅት

ገና በጠዋቱ ዝግጅቱን የጀመረው በአቶ አባይነህ የሚመራው የዘረፋ ቡድን ሁሴን አህመድ ኦይል ሊቢያ የመኪና ዘይት እና ቅባቶች ማከፋፈያ ድርጅት ውስጥ ግብቶ ለዘረፋው የሚሆን መረጃ ካሰባሰበ በኋላ ማን ምን ማደረግ እንዳለበት የሥራ ክፍፍል ለማደረግ በድብቅ ወደ ተዘጋጀው መሰብሰቢያ ቦታ ያቀናል።

መግቢያ መውጫውን፤ የቱ ጋር ዋጋ የሚያወጡ ዕቃዎች እንደተቀመጡና፤ በምን ሰዓት ዘረፋው ቢፈፀም ከስጋት ነፃ ይሆናል የሚለውን ተከፋፍሎ ያጠናው የዘረፋ ቡድን ሁሉንም ጥናት በአንድ በማድረግ የሥራ ድርሻ ክፍፍል ያደርጋል።

See also  በደቡብ ክልል የእርስ በርስ ግጭት በማስነሳት ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ከ35 በላይ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

ለዚህ ድርጊትም መቀላጠፍ መኪና ማግኘት የግድ ስለነበር በማታ፣ በራሱ በቡድኑ አባላት ሊሾፈር የሚችል የመኪና ኪራይ ፈልገው ያዘጋጃሉ። ድንገት ችግር ቢፈጠር እንኳን ለማስፈራራት፤ ባስ ካለም ሰው ለማጥፋት የሚያስችል የጦር መሣሪያም ተዘጋጀ። በምሽት ሊካሄድ ለታሰበው ዘረፋ ማንም እንቅፋት እንዳይሆን ከአልባሳት አንስቶ በቂ እንቅልፍ እስከመተኛት ድረስ ያሉ ቅድመ ሁኔታዎች ተጠናቀው የምሽቱን መግፋት በጉጉት ይጠባበቁ ጀመር።

እንዳይደርስ የለም የታቀደው እቅድ መፈፀሚያ ሰዓት ደረስ። ተራ በተራ ከጎሬያቸው የወጡት የዘረፋ ቡድኑ አባላት ቀን ላይ ወደ አዘጋጇቸው ሁለት አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች አቀኑ። ልክ በሥራ መደባቸው መሠረት በየመኪኖቻቸው ተጭነው ለዘረፋ ወደ ተዘጋጀው ድርጅት አቀኑ።

በጥናት የተካሄደው ዘረፋ

ቀን ሲዘጋጅ የዋለውና በአቶ አባይነህ የሚመራው ቡድን ቦታው ደርሷል። የዕለቱ ተረኛ የነበሩት የጥበቃ ሠራተኞች አገር ሰላም ብለው እንደወትሯቸው ወዲያ ወዲህ ይላሉ። በሞባይል የተከፈተው የሬዲዮ ፕሮግራምን ተመስጠው እየሰሙ፤ የዕለት ግዳጃቸውን እየተወጡ የነበሩት የጥበቃ ሠራተኞች ጠንከር ባለ ምት በሩ ሲንኳኳ ሰሙ። በዚህ ሰዓት ሊያውም በኃይል ማን ሊያነኳኳ ይችላል የሚለውን ለመመልከት ሬዲዮውን ዘግተው ወደ በሩ ቀረብ አሉ።

«ማነው ….» አሉ ጠንከር ባለ ድምፅ።

«ፖሊሶች ነን …» የሚል ምላሽ ተሰማ።

«ምን ፈልጋችሁ ነው?» አሉ ጥበቃው በጥርጣሬ።

«ሌባ ገብቷል፤ ፖሊሶች ነን፤ ክፈት።» አሉት ከውጭ በትእዛዝ። ምንም ዓይነት የሚያሰጋ እንቅስቃሴ ያልሰሙት ጥበቃ በሩን ቀስ አድርገው ከፍተው ወደ ውጭ ተመለከቱ። እውነትም የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ናቸው። ልባቸው ረጋ አለ። በሩን በሰፊው ከፈቱት።

ሁለት የጭነት አይሱዙ መኪና ይዘው በመምጣት የፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሰው ሽጉጥ በእጃቸው በመያዝ ወደ ውስጥ የገቡት ዘራፊዎች የጥበቃ ሠራተኛውን በማነቅ ዘረፋቸውን ይጀምራሉ።

ድርጊቱ የተፈፀመው የካቲት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት 7፡10 ሲሆን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 04፣ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነበር። የግል ተበዳይ ሁሴን አህመድ ኦይል ሊቢያ የመኪና ዘይት እና ቅባቶች ማከፋፈያ ድርጅት ውስጥ የሚገኘውን 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ለመውሰድ ሁለት አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ይዘው የመጡት የዘረፋ ቡድን፤ ለጊዜው ያልተያዘ ተጠርጣሪ የድርጅቱን አጥር ዘሎ ወደ ውስጥ ሲገባ ተከሳሹ እና ሌላ አንድ ለጊዜው ያልተያዘ ተጠርጣሪ የፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሰው፣ ሽጉጥ በእጃቸው በመያዝ ወደ ድርጅቱ ግቢ የገባውን ተጠርጣሪ ተከትለው በመምጣት የድርጅቱን ጥበቃ ሠራተኛ «ሌባ ገብቷል፤ ፖሊሶች ነን፤ በር ክፈትልን።» በማለት እንዲከፍትላቸው አድርገዋል።

See also  "ስምምነቱን የጣሰ ማዕቀብ ይጠብቀዋል" አሜሪካ

ከዚያም በኋላ ከሌሎች ግብረ-አበሮቻቸው ጋር ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ አንደኛው ግብረ-አበር አንዱን የዐቃቤ ሕግ ምስክርን በሁለት እጁ አንቆ ሲይዝ ሌላኛው ያልተያዘው ተጠርጣሪ የጥበቃውን ዓይን በእጆቹ ሸፍኖ በመያዝ መሬት ላይ ጥለው ራሱን እንዲሰት ያደርጉታል።

ሌሎች ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች ጥበቃውን በመያዝ ዓይኑን ሸፍነው መሬት ላይ በመጣል ንብረቱን ለመውሰድ እንዲያመቻቸው መከላከል እንዳይችሉ በማድረግ ላይ እያሉ የጥበቃ ተራውን ጨርሶ በሌላኛው የድርጅቱ በር የጥበቃ ማማ ላይ የተኛው ጥበቃ ከእንቅልፉ በመንቃት የቆርቆሮውን በር በኃይል ሲከፍተው ተከሳሹና ግብረ-አበሮቹ ሌላ ጥበቃ እንዳለ አይተው የወንጀል ድርጊቱን እስከመጨረሻው ለመከታተል ሳይችሉ ሸሽተው ሄዱ።

ምንም እንኳን ቡድኑ ያሰበውን ቢያደርግም ወንጀል ፈፃሚዎቹ ከድርጅቱ በተደረገ ጥቆማ መሠረት ክትትል ይደረግባቸዋል። ፖሊስም አስፈላጊውን አሰሳ በማድረግ ዋናውን ወንጀል አድራጊ በቁጥጥር ስር በመዋል (ምንም እንኳን ዘረፋውን አቋርጠው የሄዱ እና ድርጊቱም የተቋረጠ ቢሆንም) በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ከባድ ውንብድና ሙከራ በወንጀል ሊከሰሱ ችለዋል።

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሽ ካልተያዙ ግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን ሁለት አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ይዘው በመምጣት የፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሰው፤ ሽጉጥ በእጃቸው በመያዝ ሌባ ገብቷል፣ ፖሊሶች ነን፣ በር ክፈትልን በማለት የድርጅት ጥበቃውን እንዲከፍትላቸው በማድረግ፤ ንብረቶችን ለመዝረፍ የውንብድና ሙከራ ወንጀል የፈፀመው አባይነህ ወርቁ የተባለው ተከሳሽ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ወንጀል ሕግ አንቀጽ 27/1/፣ 32/1/ሀ/፣ እና 671/1/ለ/ ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ክስ ቀርቦበታል፡፡

የፍርድ ቤት ክርክር

ከላይ የተጠቀሰውንና የካቲት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት 7፡10 የተፈፀመውን የወንጀል ድርጊት በመፈፀም ከሌሎች ግብረ-አበሮቹ ጋር ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ አንደኛው ግብረ-አበር አንዱን የዐቃቤ ሕግ ምስክርን በሁለት እጁ አንቆ ሲይዝ ሌላኛው ያልተያዘው ተጠርጣሪ የጥበቃውን ዓይን በእጆቹ ሸፍኖ በመያዝ መሬት ላይ ሲጥሉት ሌሎች ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች ጥበቃውን በመያዝ ዓይኑን ሸፍነው መሬት ላይ በመጣል ንብረቱን ለመውሰድ እንዲያመቻቸው መከላከል እንዳይችሉ በማድረግ ላይ እያሉ የጥበቃ ተራውን ጨርሶ በሌላኛው የድርጅቱ በር የጥበቃ ማማ ላይ ተኝቶ የነበረው ከእንቅልፉ በመንቃት የጥበቃ ማማውን የቆርቆሮ በር በኃይል ሲከፍተው ተከሳሹና ግብረ-አበሮቹ ሌላ ጥበቃ እንዳለ አይተው የወንጀል ድርጊቱን እስከመጨረሻው ለመከታተል ሳይችሉ ሸሽተው የሄዱ እና ድርጊቱም የተቋረጠ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀመው የከባድ ውንብድና ሙከራ ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል፡፡

See also  ለባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የተዘረጋ የኤሌክትሪክ ሽቦ የሰረቁ በጽኑ እስራት ተቀጡ

ተከሳሹ ክሱ በችሎት ተነቦለት የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምኩም ያለ ሲሆን አቃቤ ሕግም ተከሳሹ ክዶ የተከራከረ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የሚያስረዱ የሕግ ምስክሮቻችን ስላሉ ይሰሙልኝ በማለት 5 የሰው ምስክሮችን አቅርቦ ያሰማ ሲሆን የአቃቤ ሕግ ምስክሮችና ማስረጃዎችም በተከሳሹ ላይ በክሱ መሠረት ያስረዱ በመሆኑ ተከሳሽ በቀረበበት ክስ እንዲከላከል የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቀጠሮ በተሰጠው መሠረት 2 የመከላከያ ምስክሮች አቅርቦ ቢያሰማም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን ሊያስተባብል ባለመቻሉ ተከሳሹ ይከላከል በተባለበት ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ ነህ ብሎታል፡፡

 ውሳኔ

 ጉዳዩን የተመለከተውም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም መጋቢት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት ተከሳሹ ከዚህ ቀደም በ26/04/04 ዓ.ም በ8 ወር እስራት፤ እንዲሁም፣ በቀን 8/5/2007 ዓ.ም በ7 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት ሲሆን፤ ይህም ተከሳሽ በተደጋጋሚ ወንጀል ፈፅሟል የሚያስብል በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ 2 የቅጣት ማክበጃ ያቀረበበት ሲሆን፤ ተከሳሽ በበኩሉ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑ እና ሌሎች 4 የቅጣት ማቅለያ ተይዞለት፣ እንዲሁም ወንጀሉ በሙከራ የቀረ በመሆኑ በቅጣት እርከን 33 ስር ቅጣቱ ተሻሽሎ በ5 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2015

Leave a Reply