ETHIO12.COM

ትህነግ በስምምነቱ መሰረት ከባድ መሳሪያዎችና ተተዃሽች ማስረከቡን አስታወቀ

በፌዴራል መንግስት እና በትህነግ አመራሮች መካከል በደቡብ አፍሪካ እና በኬኒያ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ በትላንትናው ዕለት የመጀመሪያ ዙር ከባድ መሳሪያና ተተኳሽ ርክክብ መፈጸሙን የትግራይ ቲቪ በምስል አስደግፎ ይፋ አድርጓል። ርክክቡ ከመቀሌ ከተማ 36 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አጉላ ካምፕ የተከናወነ ሲሆን በርክክቡ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ ታዛቢዎች ተገኝተዋል።

በቀጣናው የተሰማራው የሰራዊት አመራር ሌተናል ኮሎኔል አለሜ ታደለ በመንግስት እና የትህነግ አመራሮች መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት የተለያዩ ዓይነት ከባድ መሳሪያዎች መረከባቸውን ገልፀዋል፡፡

ትህነግ ለመከላከያ ሰራዊት ያስረከባቸው የመሳሪያ ዓይነቶችም ብረት ለበስ ታንኮች፣ የተለያዩ ሚሊ ሜትር መድፎች፣ ሮኬቶች፣ ዙዎች፣ ሞርተሮች እና ፐምፐን ያጠቃለለ መሆኑን ሌተናል ኮሎኔል አለሜ ታደለ ተናግረዋል፡፡

የርክክብ ሥነ ሥርዓቱን ለመታዘብ የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ አረካካቢ ኮሚቴዎች የተገኙ ሲሆን ከአረካካቢዎች መካከል ብርጋዴር ጄኔራል አድዋ ልቡካን ፒተር በሁለቱም ወገኖች በኩል እየተደረገ ያለው የከባድ መሳሪያ ርክክብ የተጀመረውን የሰላም ጉዞ የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ይህንኑ ርክክብ አስመልክቶ አቶ ጌታቸው ረዳ ” እውነት ነው እያስረከብን ነው” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በኢፌዴሪ መንግስትና በትህነግ መካከል የተደረሰው ሰላምን የማስፈን ተግባር ዓለምን የሚያስደንቅ ስለሆነ ለመላው ህዝብና ስምምነቱን ተግባራዊ እያደረጉ ላሉ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

አላስፈላጊ በነበረው ጦርነት ሚሊዮን የሚልቅ ህይወት መጥፋቱ ከትግራይ ወገን መረጃው ያላቸው እየገለጹ ነው። ከሁበድምሩ ከፍተኛ ዕልቂት ያስመዘገበው ይህ ጦርነት በሰላም እንዲቋጭ መደረጉን ተከትሎ የተጠያቂነት ጉዳይ እየተነሳበት ነው።

https://videos.files.wordpress.com/LXs67m1r/vid_20230111_193536_616.mp4
Exit mobile version