አገር መከላከያ የቡድን መሳሪያዎችን ከትህነግ ተረከበ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በደንጎላት የተሰበሰቡ የመጀመሪያ ዙር የተለያዩ የቡድን መሳሪያዎችን በዛሬው ዕለት ተረከበ። መንግሥት እና ህወሃት ጥቅም 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ የማድረግ አካል የሆነው የህወሃት ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

በስምምነቱ መሰረትም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በመጀመሪያው ዙር ትጥቅ የማስፈታት ሂደት ከባድ መሣሪያዎችን በሁለተኛው ዙር ደግሞ የአየር ኃይል መሳሪያዎችን ከህወሃት መረከቡ ይታወቃል።

ባለፈው ሳምንት ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋር በትጥቅ ማስፈታት ሂደቱ ላይ ውይይት ያደረጉት የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀኔራል ደርቤ መኩሪያ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 16 የቡድን መሳሪያዎች ርክክብ እንደሚደረግ ገልጸው ነበር።

በዚሁ መሰረት በዛሬው ዕለት በደንጎላት የተሠበሠቡ የተለያዩ የቡድን መሳሪያዎች የመከላከያ ሠራዊት እና የህወሃት ተወካዮች በተገኙበት የመጀመሪያ ዙር የቡድን መሳሪያዎች ርክክብ መደረጉን ብርጋዴር ጀኔራል ደርቤ ተናግረዋል።

በቀጣይ ቀናትም በተለያዩ ካምፖች የሚገኙ የቡድን መሳሪያዎች ርክክብ እንደሚፈጸም ጠቁመዋል።

በስፍራው የተገኙት የመከላከያ ሠራዊት ተወካይ ኮሎኔል ጉደታ ኦፍካ፤ በዛሬው ዕለት ሞርታር ዲሽቃና መሰል የቡድን በርካታ የቡድን መሳሪያዎችን መረከባቸውን ገልጸዋል።

የህወሃት ተወካይ ሙሉጌታ ገብረ ክርስቶስ በበኩላቸው በስምምንቱ መሰረት የህወሃት ታጣቂዎች የቡድን መሳሪያዎችን በመፍታት ለኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እያስረከቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ተወካዮቹ አክለውም የትጥቅ ማስፍታት ሂደቱ በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ መንግስት እና ህወሃትም ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት አዎንታዊ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው ብለዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ፤ የሰላም ስምምነቱ አተገባበርም ለሀገር ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ተስፋ የሚጣልበት ሆኗል ነው ያሉት።

See also  ብርቱካን ሚደቅሳ 'መንግሥት ምርጫውን እንዲታዘቡለት ለአውሮፓ ሕብረትና ለአሜሪካ ጥሪ አቅርቧል'

Leave a Reply