Site icon ETHIO12.COM

ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ32 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

ባለፉት አምስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 32 ነጥብ 61 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ተቋሙ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እና ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ባለፉት አምስት ወራት ለሱዳንና ጅቡቲ ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 32 ነጥብ 61 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

ለሁለቱ ሀገራትም በጥቅሉ ከ580 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ኬኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ በቅርቡ በተደረገው ስምምነት መሰረት ኃይል ማቅረብ መጀመሯንም ገልጸዋል፡፡

በአምስት ወራት የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር የ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም የሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም በተወሰነ መልኩ መቀነስ ማሳየቱ በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ የጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ ኃይል ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው በቀጣይም ለሚቀርቡ ፍላጎቶች ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ መሰረተ ልማት የማስፋፋት ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል፡፡”

የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተጀመሩ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ሲጠናቀቁ በፍጥነት እያደገ ለመጣው የአገር ውስጥና የጎረቤት አገራት ኃይል ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ምላሽ መስጠት ይቻላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version