Site icon ETHIO12.COM

የብሔራዊ የመረጃ ደህንነት ም/ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ ዘጠኝ ተከሳሾች ከእስር ተፈቱ

በእነ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ ሥር ጉዳያቸው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ሲታይ የነበሩት የቀድሞ የብሔራዊ የመረጃ ደህንነት ም/ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ ዘጠኝ ተከሳሾች ከእስር መለቀቃቸው ተገለጸ፡፡

ላለፉት አራት ዓመታት በእስር ላይ የቆዩት የቀድሞ የብሔራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ያሬድ ዘሪሁን እና በደህንነት ተቋሙ ውስጥ የሥራ ሐላፊ የነበሩት አማኑኤል ኪሮስን ጨምሮ፤ ዘጠኝ ተከሳሾች በትናንትናው ዕለት ከእስር መፈታታቸውን ከቤተሰቦቻቸው አረጋግጫለሁ ሲል ቪኦኤ ዘግቧል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ባለፈው ሐሙስ ዕለት ዘጠኙ ተከሳሾች ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት ከአራት ወር እስር እንዲቀጡ ወስኖባቸው የነበረ ሲሆን፤ ከዘጠኙ ተከሳሾች ሦስቱ የእስር ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸው በዕለቱ እንዲፈቱ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

የደህንነት ተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር ያሬድ ዘሪሁንን ጨምሮ ሰባቱ ተከሳሾችም ከተያዙበት ከጥቅምት 30 ቀን 2011 ጀምሮ ከአራት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ታስረው በመቆየታቸው፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ በአመክሮ እንደሚፈቱ ከጠበቆቻቸው አንዱ ክፍላይ መሓሪ ሐሙስ ዕለት መናገራቸውን ቪኦኤ በዘገባው አስታውሷል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታሕሳስ 7/2015 በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ በሰጠበት ጊዜ፣ መዓሾ ኪዳነ እና ተሾመ ሀይሌ የተባሉ ኹለት ተከሳሾች ከአራት ዓመት ክርክር በኋላ በነፃ መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡

በትናንትናው ዕለት ከእስር የተፈቱት ተከሳሾቹ ቀደም ሲል በሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩ ሲሆን፤ በኋላ ላይ ጉዳያቸው ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጋር እንደሚያያዝ በመገለፁ፤ የመነሻ ክሳቸው ተቀይሮ በወንጀል ሕግ እንዲከላከሉ መደረጉን የህግ አማካሪው ክፍላይ መሐሪ ጠቅሰዋል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ከአምስት ወራት በፊት ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታይ በነበሩት የቀድሞ የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ፤ በእስር ላይ ሆነው ሲከራከሩ በቆዩትና የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ እንደማይችሉ በገለጹ ተከሳሾች ላይ ከ 18 ዓመት እስከ ዘጠኝ ወር የእስር የቅጣት ውሳኔ ማሳለፉም ይታወሳል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8

Exit mobile version