Site icon ETHIO12.COM

ኢሉ አባቦራ ውስጥ ነብይ ነኝ ያለው የሃይማኖት ሰባኪ በመድፈርና ጽንስ በማቋረጥ ተፈረደበት

በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባ ቦራ ዞን ሁሩሙ ወረዳ እራሱን ነብይ እያለ የሚጠራ የሃይማኖት ሰባኪ በአስገድዶ መድፈር፣ በጽንስ ማቋረጥ እና በግብረሰዶም ድርጊት ወንጀሎች የስምንት ዓመት እስር ተፈረደበት።  

ተፈሪ አሰፋ የተባለው ተከሳሽ የቀረቡበትን ክሶች በመቃውም ሁለት ጠበቃ ቀጥሮ ቢከራከርም፣ በቀረበበት የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ጥፋተኝነቱ በመረጋገጡ እስር እንደተፈረደበት የወረዳው ዐቃቤ ሕግ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዐቃቢ ሕግ ተገኑ ብርሃኑ ወንጀሎቹ በተበዳይ ሴቶች ላይ የተፈጸመው “ሃይማኖትን ተገን በማድረግ ነው” ብለዋል።

በአካባቢው “ነብይ” በሚል ስያሜ በስፋት የሚታወቀው ይህ የሃማኖት ሰባኪ ጾታዊ ጥቃት ፈጽሞብናል ብለው ጥቆማ የሰጡ ሴቶች ቁጥር 11 መሆኑን የገለጹት ዐቃቤ ሕጉ፤ በቀረቡበት ወንጀሎች ጥፋተኛ በመሆኑ በ8 ዓመት ከአምስት ወር ጽኑ እስራት እና በ4ሺህ ብር እንዲቀጣ የወረዳው ፍርድ ቤት እንደበየነበት አስረድተዋል።

“በአጠቃላይ 11 ሴቶች ናቸው አቤቱታ ያቀረቡት፤ አብዛኞቹን አገባችኋለሁ እያለ የተዋቸው ናቸው” ብለዋል።

ግለሰቡ የቀረቡበትን ክሶች ተከትሎ እጁን ለፖሊስ ከሰጠ በኋላ ጉዳዩ ላይ ምርመራ ሲደርግ ቆይቷል። ነብይ ነኝ የሚለው ግለሰብ ጥፋተኛ ከተባለባቸው ወንጀሎች መካከል አንዱ በሁለት ሴቶች ላይ ጽንስ ማቋረጥ መሆኑን ዐቃቤ ሕጉ ያስረዳሉ።

ጽንሳቸው እንዲቋረጥ ካደረጋቸው ሴቶች መካከል ደግሞ አንዷ ገና የ14 ዓመት ታዳጊ መሆኗንም ገልጸዋል።

“ይህችን ታዳጊ አገባሻለሁ ብሎ አታለላት። በአምልኮ ስፍራም ታዳጊዋን ከምዕመናን መካከል አስነስቶ፤ ‘ፈጣሪ ተናግሮኛል። ያዋረዱሽን አዋርጄ በትልቅ ቦታ አስምጥሻለሁ ብሎኛል’ ሲል ተናግሯት ነበር” በማለት ይገልጻሉ።

እራሱን ነብይ ብሎ የሚጠራው ግለሰብ ታዳጊዋ መጸነሷን ካወቀ በኋላ ወላጆቿ ጋር እየደወለ ጽንሱ እንዲቋረጥ ሲወተውት ነበር ብለዋል ዐቃቤ ሕጉ። 

“ጽንስ እንዲቋረጥ የሚያደርገው ጽንስ የሚያቋርጥ መድኃኒት በመጠቀም ነው . . . ይህችን ታዳጊ መድኃኒቱ ለጽንሱ እድገት ጠቃሚ ነው ብሎ አታልሎ እንድትወሰድ አድርጓታል።”

ይህም በአገሪቱ የወንጀል ሕግ መሠረት ሰዎችን በማታለል ጽንስ እንዲቋረጥ ማድረግ ከ3 እስከ 10 ዓመት ጽኑ እስራት ያስቀጣል በማለት ዐቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።

ይህ ተከሳሽ ጥፋተኛ የተባለበት ሌላኛው ክስ ደግሞ ሴቶች ላይ ከመራቢያ አካል ውጪ ወሲብ ፈጽሟል የሚለው ነው።

“ከተፈጥሯዊ መንገድ ውጪ ወሲብ ፈጽሞብናል” ያሉ ሴቶች ቁጥር 3 መሆናቸውን ዐቃቤ ሕግ ተገኑ ተናግረዋል።

እራሱን ነብይ ብሎ የሚጠራው ግለሰብ ይህን ተግባር ሲፈጽም በሞባይል ስልኩ ድርጊቱን ይቀርጽ እንደነበረ ገልጸው በስልኩ ላይ የተገኘው ተንቀሳቃስ ምስል እንደ ማስረጃ ሆኖ እንደቀረበበት ጨምረው አስረድተዋል።

ግለሰቡ የቀረቡበት ክሶችን አልፈጸምኩም በማለት የተከራከረ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረቡበት የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን የተመለከተው ፍርድ ቤት ማክሰኞ ጥር 02/2015 ዓ.ም. ጥፋተኛ መሆኑን በማረጋገጥ የስምንት ዓመት ጽኑ እስራት ተፈርዶበታል።

BBC AMHARIC

Exit mobile version