Site icon ETHIO12.COM

የታዳጊዉ ወጣት በጎነት -በህግ ማስከበር ዘመቻ

ታዳጊዉ ወጣት ተመስገን ጥጋቡ ይባላል፡፡ተወልዶ ያደገዉ በሰቆጣ ከተማ ነዉ፡፡አባቱ መቶ አለቃ ጥጋቡ አማረ ይባላል የመከላከያ ሰራዊት አባል ሲሆን ለሀገሩ ሰላም መከበር ሲል መስዋእትነት ከፍሏል፡፡ እናቱ ወይዘሮ በላይነሽ ዳዊት ትባላለች ህፃን እያለ በህይወት እንዳጣት ታዳጊዉ ወጣት ተመስገን ተናግሯል፡፡

አባቱ መቶ አለቃ ጥጋቡ አማረ የመከላከያ ሰራዊት አባል ሆኖ ሀገሩን ሲያገለግል ከቆየ በኋላ በህግ ማስከበር ዘመቻዉ ወቅት መቀሌ ላይ ተሰዉቷል፡፡ታዳጊዉ ወጣትም ኑሮዉን ከሰቆጣ ወደ ቆቦ ከተማ ለማደረግ ተገዷል፡፡

ነሀሴ ወር 2014 ዓ.ም በተከፈተዉ ጦርነት ቆቦ ከተማ የነበረዉ ታዳጊዉ ወጣት ተመስገን ከመከላከያ ሰራዊታችን ጋር በመሆን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በበጎነት የበኩሉን አስተዋፆ ተወጥቷል፡፡

በዉጊያ ላይ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸዉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተሎ ህክምና ማግኘት እንዲችሉ በድንገት ያገኘዉን አምቡላንስ በመጠቀም ወደ ወልዲያ ቁስለኛ የማመላለስ ስራ የሰራ ሀገር ወዳድ ታዳጊ ነዉ፡፡

ታዳጊዉ ወጣት ተመስገን በሰቆጣ ከተማ ተወልዶ ያደገ ሲሆን እናቱ በልጅነቱ ስለሞተችበት ባላቸዉ አቅም ተንከባክበዉ ያሳደጉት አያቱ ናቸዉ፡፡ ቀጥሎም ወደ ሰሜን ወሎዋ ቆቦ ከተማ በመሄድ ከሰዉ ተጠግቶ የጋራጅ ስራ ላይ እንደተሰማራ እና ለአራት ዓመታት እንደቆየ በአንደበቱ ገልፆልኛል፡፡

ተመሰገን ምንም እነኳ መንጃ ፍቃድ ባይኖረዉም በጋራጅ ሙያ ስራዉ ያገኘዉን ሙያዊ አቅም ተጠቅሞ መኪና ማሽከርከር ችሏል፡፡አሁንም ድረስ መኪና ማሽከርከር ቢችልም ተመስገን መንጃ ፍቃድ የለዉም፡፡ በቀጣይ ቢሳኩልኝ ካላቸዉ መሰረታዊ ቁምነገሮች መካከል መንጃ ፍቃድ በእጁ መያዝ አንዱ ነዉ፡፡

ይህ ታዳጊ ሀገር ወዳድ ወጣት የአባቱን ፈለግ ተከትሎ ለሀገሩ ማድረግ ያለበትን በጎ ነገር በመልካም ስራዉ ጀምሯል፡፡ ነገ ከዚህ በላይ ሀገሩን እንደሚጠቅምስ ማን ያዉቃል ?

ወጣት ተመስገን የቆሰሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ከቆቦ እና አካባቢዉ ተነስቶ ወደ ወልዲያ ሆስፒታል በመዉሰድ በህግ ማስከበር ዘመቻዉ የበኩሉን ሀገራዊ አስተዋፆ አብርክቷል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት አባለቱም ለሀገር ሰላም ሲል አባቱ በጦር ሜዳ ቢሰዋም እኛ አለንልህ በሚለዉ ህዝባዊነታቸዉ ወጣቱ አንድ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ከእኛ ጋር ትሆናለህ በማለት ከእነርሱ ጋር እንዲሆን አድርገዋል አሁንም አብሯቸዉ አለ፡፡

ወጣት ተመስገን የአስራ ስምንት ዓመት ወጣት ሲሆን በኢኮኖሚ እጥረት ወይንም በአቅም ማነስ መክንያት የትምህርት ደረጃዉን ከሰባተኛ ክፍል በላይ ማሳደግ አልቻለም፡፡

ወጣቱ ታዳጊ አሁን ላይ ሁለት ነገሮች ቢሳኩልኝ ሲል በአንደበቱ አጫዉቶኛል፡፡ የመጀመሪያዉ መንጃ ፍቃድ መያዝ ቀጥሎም በትምህርቱ መግፋት ነዉ፡፡ይህ ሃሳቡም ሊሳካለት እንደሚችል አምናለሁ፡፡

እናም እንዲህ በለጋነት ዕድሜያቸዉ ህይወትን ለታደጉ ለሀገራቸዉ ሰላም ለመከላከያ ሰራዊታችን የተልዕኮ አፈፃፀም ስኬት በቅን ልቦና ለታተሩ ለሀገራቸዉ ሰላም እና ዕድገት ዕዉን መሆን ወደ ኋላ ላማይሉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ምስጋና ይገባቸዉ ቸር እንሁን፡፡

ውብሸት ቸኮል – የኢፌዴሪ መከላከያ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም
ፎቶግራፍ ደስአለዉ ፈንታዉ

Exit mobile version