ETHIO12.COM

መንግስት እምነትና ብሄር ተገን ተደርጎ ምን ለመፈጸም እንደታሰበ “ደርሼበታለሁ፤ አልታገስም” አለ

“እምነትና ብሔርን ተገን አድርገው ግጭት ለመፍጠር የሚያስቡ፣ ሀገር ለማፍረስ በተለያዩ መንገዶች ሞክረው ያልተሳካላቸው ኃይሎች፣ ችግሩ እንዲባባስና በሰላም እንዳይፈታ ለማድረግ እየሠሩ መሆኑ ተደርሶበታል። መንግሥት ይሄንን ፈጽሞ አይታገስም” ይላል የመንግስት ኮሙኒኬሽን መግለጫ በስተመጨረሻው።

“ችግሩን ለማባባስና በሕዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር፣ ብሎም ሀገርን ወደ ፈተና ለማስገባት በሚጥሩ አካላት ላይ መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን እንደሚሠራ በዚሁ አጋጣሚ ያሳውቃል” በማለትም ያክላል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ይህን መግለጫ ያሰራጨው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ያቀረበውን የተቃውሞ ጥሪ ተከትሎ ሲሆን በመግለጫው ችግሩ በሰላም እንዲፈታ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ በማስታወቅ ነው።

ዛሬ ማለዳ በደሴ በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ ” ወደ ቤተመቅደሳችን ከገባህ፣ ወደ ቤተመንግስትህ እንመጣለን” የሚል መፈክር መሰማቱ ጉዳዩ የፖለቲከኞች እጅ እንዳለበት የሚያመላክት እንደሆነ በሌላው ወገን የሆኑ እየገለጹ ሲሆን፣ በድጋፍና በክራትም ይህንኑ በማሰራጨት ሌሎችም እንዲነሱ ለቅሰቀሳ የሚጠቀሙበት ታያተዋል።

ለጊዜው ክልሎች ዝምታን መርጠዋል። ቤተክርስቲያን ያወጀችው የጥቁር መልበስና የሶስት ቀን የነነዌን ጾም በየክልሉ ምን እንደምታና ምላሽ እንዳለው ለማወቅ አልተቻለም። የመንግስት መግለጫ ከታች እንዳለ ቀርቧል።

በወቅታዊ ጉዳይ ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን የተሰጠ መግለጫ

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ በውስጣዊ አሠራር መፈታት እንዳለበት መንግሥት ያምናል።

ሀገራዊ ተቋማት አንድነታቸውንና ጥንካሬያቸውን ጠብቀው እንዲዘልቁ ከዚህ በፊትም ሆነ ችግሮች በተፈጠሩ ጊዜ ሁሉ መንግሥት የሚጠበቅበትን ሲወጣ ቆይቷል። ይሄንን ጥረቱን አሁንም አጠናክሮ ይቀጥላል።

የተቋማቱን አንድነት የሚፈታተኑ ችግሮች ከውስጥ ሲነሡ በውይይትና በውስጣዊ አሠራር እንዲፈቱ ድጋፍ ሲያደርግ ነበር። በተጨባጭም ውጤት አምጥቷል።

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በቤተ ክርስቲያኒቱ አሠራር መሠረት እንዲፈታ ሁሉም አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል።

የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሁለቱን ወገኖች በማቀራረብ ችግሩ በሰከነ መንገድ እንዲፈታ ማድረግ አለባቸው።

አማኞች ችግሩን ከማወሳሰብና ለሌሎች አካላት መጠቀሚያ ከመሆን በመታቀብ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ ይገባል። የጸጥታ አካላት የየአካባቢውን ሕዝብና የእምነት ተቋማት ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ግዴታቸው ነው። ግጭት የሚያባብሱ አካላትንም ሥርዓት ማስያዝ አለባቸው።

የሚዲያ አካላት ችግሩን የሚያባብሱ ነገሮችን ከማቅረብ መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል። እንዲሁም መላው ሕዝብ ለችግሩ መፈታት የሚጠበቅበትን እንዲያደርግ መንግሥት ያሳስባል።

በሌላ በኩል እምነትና ብሔርን ተገን አድርገው ግጭት ለመፍጠር የሚያስቡ፣ ሀገር ለማፍረስ በተለያዩ መንገዶች ሞክረው ያልተሳካላቸው ኃይሎች፣ ችግሩ እንዲባባስና እንዳይፈታ ለማድረግ እየሠሩ መሆኑ ተደርሶበታል። መንግሥት ይሄንን ፈጽሞ አይታገሥም።

ችግሩን ለማባባስና በሕዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር፣ ብሎም ሀገርን ወደ ፈተና ለማስገባት በሚጥሩ አካላት ላይ መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን እንደሚሠራ በዚሁ አጋጣሚ ያሳውቃል።

ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Exit mobile version