” በህጉ መሠረት የመጣን መታዘዝ ግዴታችን ነው በሌላ በኩል ህገወጥን አካል ሠራዊቱ አይታገስም “

እንደሚታወቀው ባንዳ ባለቤት አለ፤ አባት አለው። ሀገራችን ጠንካራ ሠራዊት እንዲኖራት የሚፈልጉ ሃይሎች ሠራዊቱ በብሔርና በፖለቲካ እንዲከፋፈል ባንዳዎችን በጥቅም ይገዛሉ። ባንዳ እንደ ዕቃ ህሊናው ለመሸጥ ዝግጁ የሆነ ዜጋ ነው።ለሀገር ክብር፣ ለወገን ሠላምና ደህንነት የሚቆረቆር አይደለም ባንዳ፡፡

ለዘላቂ ሠላም የሠራዊት ግንባታ ሂደትን በተመለከተ፦ ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከመከታ መፅሄት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፡፡

መከታ ፦ የሐገራችንን ሰላም በዘላቂነት ለማስከበር የሰራዊታችን ዝግጁነት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፦ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ የነበረውን ጦርነት በሰላም ስምምነት ለመቋጨት ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎን በቀጣይ ሐገሪቱን ሌላ ጦርነት እንዳይቃጣባት የሚያደርግ ጦርነትን በሩቅ የሚያስቀርና ጦርነት ከተከፈተብንም በአጭር ጊዜና በአነስተኛ ኪሳራ መመከት የሚያስችል የዝግጁነት ስራ እየተሰራ ነው፡፡

ሠራዊታችን ከለውጡ በፊት የነበረው ዝግጁነትና አቅም አሁን ከደረሰበት ብቃትና ደረጃ ጋር በፍፁም የማይነፃፀር የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ያለው ነው፡፡ “አየር ሐይልን ብቻ ብንመለከት ዝግጁ የምትባል አንዲት ቢጫ ሄሊኮኘተር ነበረች።
የሚበሩ ጄቶች አልነበሩም። ቢበሩም የአብራሪዎች ከፍተኛ እጥረት ነበር። በምድር ሐይልም ቢሆን ኢትዮጵያን የምታክል ትላቅና ታሪካዊ ሀገር የሚመጥን ሠራዊት አልነበረም። የተወሰኑ ክፍለጦሮችና ለስም ብቻ የተደራጁ ዕዞች ነበሩ። በአስተሳሰብ ከፍተኛ ችግሮች ነበሩ።

ከሀገራዊ ጉዳይና ህዝባዊ ዓላማ ይልቅ የብሔር አጀንዳና የፓለቲካ ፓርቲ ውግንና ጉዳይ የሚያሳስበው ሠራዊት ነበር። በእነዚህ አሳሪ አስተሳሰቦች የታጠረ ሠራዊት ይዞ ሠራዊቱ ዝግጁ ነበር ማለት አይቻልም። ለአብነት ያህል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጦርነት ሲቀሰቀስ ሙሉ በሙሉ ከብሔርና ከፓርቲ አስተሳሰብ ያልተላቀቁ አባላት ከህውሐት ጋር መቀላቀላቸው ራሱን የቻለ ማሳያ ነው ።

እዚህ የቀሩትም ከአስተሳሰቡ የፀዱ ስላልነበሩ የሚያስከትሉትን ጫና ለመቀነስ ለጊዜው እንዲለዩ ተደርጓል። መከላከያ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሪፎርም አካሄዷል። ሠራዊቱን ከብሔርና ፖለቲካ አስተሳሰብ ማላቀቅ ከአንኳር አንኳር የሪፎርሙ ተግባራት ውስጥ ይጠቀሳል። በውጤቱም አንድ ዓይነት ሀገራዊ አስተሳሰብ ያለው ሠራዊት መገንባት ተችሏል።

ሪፎርሙ ለተቋማችን መከላከያ በርካታ ፀጋዎችን ይዞ መጥቷል። ከእነዚህ ውስጥ የሠራዊቱን የመኖሪያ ካምፖች መገንባት የተሻለ የስራና የሕይወት ዋስትና እንዲኖረው ማድረግ፡፡ የኑሮ ማሻሻል ሥራዎችና የአደረጃጀት ለውጦች ይጠቀሳሉ።

See also  " ከ 27 ዓመታት የልማት ዘፈንና ፉከራ በኋላ የትግራይ ህዝብ በችግር ላይ ወድቆ መገኘቱ አሳፋሪ ነው" አቶ አንዳርጋቸው

ጦርነትን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም ከተቻለ መልካም ውጤቶች እንደሚኖሩት ያለፉትን ዓመታት የሠራዊቱን ተሞክሮ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአብነት ያነሳሉ። “መከላከያ ጦርነቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሰው ሐይል፣ በአደረጃጀት፣ በትጥቅ መሠረታዊ ለውጥ አምጥቷል። እየተዋጉ ሠራዊት መገንባት ከባድ ቢሆንም ተቋሙ ግን ይህንን ማሳካት ችሏል።

ለጦርነት ዝግጁ የሆነ እዚህ ግባ የሚባል ትጥቅም ሆነ አደረጃጀት እንዲሁም አስተሳሰብ ካልነበረበት ሁኔታ ተነስቶ አሁን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። አየር ሐይል ሄሊኮኘተሮችንና ጄቶችን በእስኳድሮን ደረጃ ታጥቋል።

ምድር ሐይል በሰው ሃይል የተጠናከረ፣ በዕውቀት ያደገ፣ በክህሎት የዳበረና በስነ ልቦና ዝግጁነት የላቀ ሆኖ ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ ተደራጅቷል።

ዘመኑ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ እንዲሁም ከባቢያዊና ዓለም ዓቀፋዊ ሁኔታዎችን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መከላከያ በቀጣይነት ለመንገባት የአሥር ዓመት ስትራቴጂካዊ እቅድ ተዘጋጅቶ በመተግበር ላይ ይገኛል። በዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ ታሪካችን በርካታ ሂደቶች ታልፈዋል። በደርግ ዘመን ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ተብሎ ግዙፍ ሠራዊት መገንባቱ ይታወሳል።

ይሁንና በብዛትም ሆነ በጥራት አሁን ያለውን የኢፌዲሪ መከላከያን የሚያክል ሃይል አልተገነባምና በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን የሚያሰጋት ሐይል የለም”ይላሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፡፡

መከታ ፦ “የሠራዊታችን ውስጣዊ አንድነትና የተልዕኮ ግልፀኝነት በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል ?

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ፦ ሠራዊታችንን ለመከፋፈል፣ ከተልዕኮውና ከቆመለት ዓለማ እንዲወጣ ለማድረግ የሚቃጡ ሙከራዎች ቢታዩም ይሕ ፈፅሞ የሚሳካ አይደለም፣ ሙከራውን የሚያደርገት ወገኖችም የሰራዊታችንን ውስጣዊ ሁኔታ ካለመገንዘብ የሚያካሒዱት ሙከራ ነው፡፡

ሠራዊቱ የሀገሩን ዳር ድንበርና ሉዓላዊ ክብር ለመጠበቅ በብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማው ፊት ቃል የገባ ፤የብሔር አጀንዳና የፖለቲካ ወገንተኝነትን አራግፎ የጣለ፤ በወርቃማ እሴቶች የተገነባና እሴቶቹን ወደ እምነት የቀየረ ሀይል ነውና ለአፍራሽ ኘሮፓጋንዳ ሰለባ የሚያደርገው ስብዕና የለውም።

በግለሰብ ደረጃ ሠለባ የሚሆን እንኳን ቢኖር ሠራዊቱ የሚያርምበትና ችግሩ ሥር ሳይሰድ ፈጥኖ የሚያስተካክልበት አሠራር አለው ሠራዊቱ እንዲፈርስ የሚፈልጉት የሀገራችን ቀንደኛ ጠላቶችና ባንዳዎች ናቸው።

እንደሚታወቀው ባንዳ ባለቤት አለ፤ አባት አለው። ሀገራችን ጠንካራ ሠራዊት እንዲኖራት የሚፈልጉ ሃይሎች ሠራዊቱ በብሔርና በፖለቲካ እንዲከፋፈል ባንዳዎችን በጥቅም ይገዛሉ። ባንዳ እንደ ዕቃ ህሊናው ለመሸጥ ዝግጁ የሆነ ዜጋ ነው።ለሀገር ክብር፣ ለወገን ሠላምና ደህንነት የሚቆረቆር አይደለም ባንዳ፡፡

See also  ኦሮሚያ ፖሊስ ምስራቅ ሸዋ ዞን የተፈጸመውን ግድያ እያጣራ መሆኑን ገለጸ-

“የኢትዮጵያ ጠላቶች ሠራዊታችን ተከፋፍሎ እንዲዳከም ከመሥራት በተጨማሪም ሠራዊቱን ከመንግስት ጋር ለማጋጨትም የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ይታያሉ::በነውጥ ሐገረ መንግስቱን አፍርሰው ስልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ ወገኖች ለዚሕ ዕኩይ ዓላማቸው እንድንተባበራቸው ይፈልጋሉ::እኛ ግን ይሕ መንገድ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት ሕዝብን ወደ ማያቋርጥ ዕልቂት የሚያስገባ ስለሆነ አንተባበርም::ይልቁንም ሙከራውን በፅናት እንመክተዋለን፡፡

ሠራዊቱ የሚተባበረው ህጋዊ አካሄድን ከሚከተል ጋር ብቻ ነው። ተልዕኳችን በህገመንግስቱ መሠረት የተቋቋመን መንግስት ማገልገል ነው ። ከዚህ ውጭ የመጣን ሐይል እንመክታለን። ለአፍራሽ ኘሮፓንጋንዳ ጆሮ አንሠጥም። ከብሔር አስተሳሰብና ፖለቲካ ውግንና ነፃ የሆነ ሠራዊት ገንብተናል።

ህገመንግስቱ ስልጣን የሚያዝበትን አግባብ ግልፅ አድርጎታል። የፖለቲካ ውድድር የሚደረግበትን አግባብና መንግስት የሚቀየርበትን አሠራር አስቀምጧል። በህጉ መሠረት የመጣን መታዘዝ ግዴታችን ነው። በሌላ በኩል ህገወጥን አካል ሠራዊቱ አይታገስም”፡፡

በጦር ሐይሎች ጠቅላይ መምሪያ በየሦስት ወሩ የሚታተመው መከታ መፅሔት ቁጥር 1 ዕትም የተወሰደ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚያዚያ 14 ቀን 2015 ዓ.ም

Leave a Reply