ኢትዮጵያ በሳውዲ ህገወጥ ተብለው በእስር ላይ የነበሩ 131 ሺህ በላይ ዜጎቿን ሰብስባ ጨረሰች

ዜናው እረፍት የሚሰጥ፣ እፎይ የሚያሰኝ ቢሆንም ዜጎችን በህገወጥ መንገድ ገንዘባቸውን እየተቀበሉ ሲሸጡና ድንበር እያሻገሩ ሲበትኗቸው የነበሩ አካላት ጉዳይ ሲታሰብ የልብ ስብራቱ ከባድ ነው።

በአዲስ አበባ ቢሮ ተክለው፣ በአገሪቱ ብሄራዊ መገናኛዎች ማስታወቂያ እያሰሩ፣ የአገሪቱን ታላላቅ ባለስልታኖችና የፍትህ አካላትን የቦርድ ሰብሳቢ እያደረጉ፣ በሚታወቁ የማስታወቂያ ሰራተኞች ጥሪ እያሰሙ ህዝብ የሞሸለቁ መኖራቸውን፣ ሙሽለቃውም በጠራራ ጸሃይ የተፈጸመና ህጋዊ ከለላ ያለው እንደነበር የሚያስታውሱ፣ በአብዛኛው ዜጎችን ወደ ሳኡዲና የተለያዩ አገራት በኤጀንሲና በድንበር ሲያሻግሩ የነበሩ አካላት ላይ ማስረጃ ተሰብስቦ ለምን ክስ እንደማይመሰረት ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው።

የሳኡዲው ጉዞ መጅሊሱን የሃብት መገበያያ ባደረጉ ሹመኞችና ደላላዎቻቸው በሆኑ የጉዞ ወኪሎች ድርድር የሚከናወን፣ ዜጎች ለጸሎት ብለው ሄደው በድህነታቸውና አማራጭ አልባ በመሆናቸው ጭምር እዛው በመቅረት ራሳቸውን ህገወጥ እንደሚያደርጉ መረጃዎች ያረጋግጣሉ። ይሁን እንጂ በደላላ ንብረታቸውን አራጣ በማበደር ፣ የእርሻ በሬዎቻቸውን በማሸጥና በማስያዝ የሚያገኙትን ብር እያግበሰበሱ በረሃ ላይ የሚያፈሷቸው ዜጎች በሶማሌና የመን ከሞትና ከአካል ክፍል ዝርፊያ ተርፈው ሳዑዲ የደረሱት ፍርድ የተጓደለባቸውና የተዘረፉ ስለመሆናቸው የአብዛኞቹ ምስክርነት ያሳያል።

ለውጡ ዕውን ከሆነ በሁዋላ 131 ሺህ የሚልቁ ብስቃይ ላይ የነበሩ ወገኖች ድምጻቸው ተሰምቶ በተከታታይ በተደረገ ምልልስ ለአገራቸው በቅተዋል። ዛሬ መንግስት እንዳስታወቀው ዜጎችን የመመለስ ሂደቱ ተጠናቋል። አብዛኞች የሚጠይቁት ንብረታቸውን ለአራጣ፣ ብራቸውን ለደላላ፣ ነብሳቸውን ለስቃይ ዳርገው የነበሩ ወገኖች ቀታይ ህይወት ነው።

ለስለጠነ ፖለቲካና የፖለቲካ ትግል ያልታደለችው ኢትዮጵያ፣ እንዲህ ያሉ ታላላቅ ርብርብ የሚሹ ጉዳዮች እያሏት በመንደር እሳቤ የሚባሉ፣ የሚያባሉና መንደርን ለስልጣን ጥቅም ተገን በማድረግ መርዝ ሲረጩና ሲያስረጩ ውለው በሚያመሹ የፈረቃ የስልጣን ሱሰኞች እየተናጠች ነው። ዛሬ በየስፍራው ተፈናቅለው የወደቁ ዜጎቻንን በመተባበር ለማንሳትና ለመደገፍ ከመሯሯጥ ይልቅ ያልተፈናቀሉትን ለማፈናቀል በየቀኑ ሴራ ማምረት ወግ እንደሆነ የገባቸውና ሃላፊነት የሚሰማቸው እየገለጹ ነው።

የሰውን ልጅ በመሸጥና በረሃ በመበተን ሃብት ያጋበሱትን በማጋለጥ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ ንብረታቸውን ተይዞና ተወርሶ ለተጎጂዎች እንዲውል ሚዲያው ትንታግ ሆኖ ሊሰራ ሲገባው፣ በግብር የረከሱ፣ በስም “አንቱ” የሚባሉ፣ ከየት እንደሚጠመቅ ግልጽ ያልሆነና ዓላማው አገርን የማያጸና አጀንዳ በማራባት ላይ መጠመዱ የነዚህን ፍትህ የጠማቸው ወገኖች በደል አባሽ አጥቶ እንዲቀር ሆኗል። ከስር የመንግስት ሚዲያዎች የዘገቡትን ያንብቡ።

See also  «ፑቲን ስልጣን ላይ መቆየት አይችሉም አሉ» ጆ ባይደን ክሬምሊን አይመከታችሁም ብሏል

በሕገወጥ መንገድ ከአገር ወጥተው በሳውዲ ዓረቢያ በእስር ላይና በማቆያ ቦታዎች በችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ወደ አገራቸው የመመለሥ ሥራ ተጠናቀቀ።

ከስደት ተመላሾችን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው የተቀበሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታና የሳውዲ ስደተኞችን ለመመለሥ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንደገለጹት፤ መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ህገወጥ ስደተኞችን የመመለሱ ተግባር ሲጀመር በሳውዲ ዓረቢያ በእስርና በማቆያ ጣቢያዎች የሚገኙ 102 ሺ ዜጎችን ለመመለስ ታቅዶ ሢሠራ ነበር።

ይሁን እንጂ ሕገወጥ ስደቱ ባለመቆሙና ወደ ኤምባሲ የሚመጡ ዜጎች ቁጥር በመጨመሩ የዛሬ ተመላሾችን ጨምሮ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የነበሩ በላይ 131ሺ የሚሆኑ ዜጎችን መመለስ መቻሉን ጠቁመዋል።

ከሳውዲ ተመላሾች ባለፈ በተለያዩ አገራት ችግር ላይ የነበሩ ስምንት ሺ ዜጎችን የመመለሥ ሥራ መሠራቱን ያስታወሱት አምባሳደር ብርቱካን፤ በዘመቻ የሚሠራው ሥራ ይጠናቀቅ እንጂ አሁንም ችግር ላይ ያሉ ዜጎችን የመመለሡ ተግባር አይቆምም ብለዋል።

የመንግሥትና የሕዝብም ፍላጎት ዜጎች በአገራቸው ሠርተው እንዲለወጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ በውጭ አገራት የሚፈጠሩ የሥራ እድሎች ካሉም በሕጋዊ መንገድ መሄድ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዜጎችን ከመመለስ ባለፈ አስፈላጊው እገዛ ተደርጎላቸው በአገራቸው ሠርተው እንዲለወጡ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር እየሠሩ መሆኑም ተጠቅሷል።

በፋንታነሽ ክንዴ EPD

Leave a Reply