Site icon ETHIO12.COM

በኤሌክትሪክ ሽያጭ 40 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ተገኘ

በተጠናቀቀው ግማሽ በጀት ዓመት ለጅቡቲ እና ሱዳን ከቀረበው የኤሌክትሪክ ሽያጭ 39 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡ ለውጭ ገበያ የተደረገው የኤሌክትሪክ ሽያጭ አፈጻጸምም 89 በመቶ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ለጅቡቲ ከተደረገ የኤሌክትሪክ ሽያጭ 19 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፤ 21 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን በተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ተናግረዋል፡፡ ከዕቅድ በላይ 8 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱንም ነው የጠቆሙት፡፡

ለሱዳን ከቀረበ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ደግሞ 24 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ፤ 18 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል ብለዋል፡፡ ወደ ኬንያ በቅርቡ ሽያጭ መጀመሩን ጠቁመው ለተወሰነ ጊዜ በሙከራ ስለሚቆይ ትክክለኛ (መደበኛ) ሽያጩ ሲረጋገጥ ለውጭ ሀገራት ከሚቀርበው ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ከፍ እንደሚል አመላክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ለኢትዮ ቴሌኮም፣ ለሳፋሪ ኮም እና ለዌብ ስፕሪክስ አይ ቲ ሶልዩሽን ተቋማት ኦፕቲካል ፋይበር በማከራየት 54 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡

የዚህ ዘርፍ አፈጻጻምም 122 በመቶ መሆኑን ነው አቶ ሞገስ የገለጹት፡፡ በሀገር ውስጥ ደግሞ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚዎች እና ለኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የ9 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የኤሌክትሪክ ሽያጭ ለማከናወን መታቀዱን አመልክተዋል፡፡

ፋና እንደዘገበው፤ ክንውኑ 8 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር መሆኑን እና የዕቀዱ 89 በመቶ መፈጸም መቻሉን አቶ ሞገስ ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version