Site icon ETHIO12.COM

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የተጠለፈው የሲኖዶስ መከፋፈል

ለዘመናት የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጽሕፈት ቤትን ከኢትዮጵያ ለማንሳት እጅግ በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል። ይቀርቡ የነበሩት ምክን ያቶች ውሃ የማይቋጥሩ ሆነው በመገኘታቸው ሁሉም ስኬት እንደናፈቃቸው መና ሆነው ቀርተዋል። ሙከራው ግን አላቆመም፤ አሁንም ቀጥሏል ሲል የዘገበው ጎልጉል ነው።

ኢትዮጵያ ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ቡድን ጋር ጦርነት የገጠመች ጊዜ ይኸው አጀንዳ ቀጠሎ ነበር። ጦርነቱ ከነበረው በርካታ ድብቅ ዓላማዎች በዋነኛነት የሚጥቀሰው ይህ እንደነበር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ይመሰክራሉ። የኢትዮጵያን ዋንኛ ጥቅሞች በመለየት መበጠስ በተለይ “ተላላኪ” በሚባሉና ” ተከፋይ ናቸው” በሚባሉ ዘንድ በተመረጡ አውዶች ላይ አነጣጥሮ ሲከናወን መቆየቱን የገባቸው በየጊዜው ሲያስታውቁ ቆይተዋል። አሁንም እያስታወቁ ነው።

በተለይ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የኅብረቱ ስብሰባ ለሁለት ዓመታት በመስተጓጎሉ በመንተራስ በዚያው ከኢትዮጵያ ምድር ተረስቶ እንዲቀር ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም። በተለይ የሰሜኑ ጦርነት በአገሪቱ “መረጋጋት የለም” ለሚለው እመክንዮ እንደ ማሳያ ተቆጥሮ ስብሰባው እንዳይካሄድ ከፍተኛ ጫና፣ ግፊት ሲደረግ በነበረበት ወቅት መንግሥት ስብሃት ነጋን፣ ጃዋር መሐመድን፣ እስክንድር ነጋን፣ በቀለ ገርባን፣ ወዘተ የመፍታትን እጅግ አናዳጅና የበርካቶችን ልብ ያሳዘነ እርምጃ በመውሰድ ነበር የታደገው። ይህ በመሆኑ እነ ስብሃት በተፈቱ በወሩ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ መካሄድ ቻለ። ይህ አካሄድ የገባቸው ከደጋፊዎች በስተቀር ጠላቶችን ስለነበር ” ለምን ተፈቱ” በሚል የራሳቸው ሰዎች ሳይቀሩ ጩኸት ማሰማታቸው የጊዜው አስገራሚ ዜና ሆኖ አልፏል።

ከሳምንት በኋላ የሚከፈተውን የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ እና ሌሎች በርካታ የፖለቲካ አጀንዳዎችን አስልቶ በድንገት በሚመስል ከተፍ ያለው የሰሞኑ የሲኖድ ውዝግብ ከዚህ ውጪ እንደማይታይ በርካታ ጠቋሚ መረጃዎች አሉ። ጉዳዩ የዕምነት በመሆኑ ዝርዝር ውስጥ መግባት ቢከብድም፣ መከፋፈሉና መከፋፈሉን ተከትሎ በውይይት እንዲፈታ የሚሞክሩትን በማራከስ ረብሻ የተመረጠውም የሲኖዶስ ችግር ሆን ብለው በሚያቀጣጥሉና ግራ የተጋቡ አባቶችን በማዋከብ መካሄዱ ነው።

በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ የሚከፈተውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ስብሰባ ተከትሎ የሚደረገው የመሪዎች ስብሰባ በርካታ ወሳኝ አጀንዳዎች ቀርበው የሚጸድቁበትና አቅጣጫ የሚያዝበት እንደሆነ የስብሰባውን አካሄድ የሚከታተሉ ለጎልጉል አስታውቀዋል።

ከፓን አፍሪካኒዝም አጀንዳ በተጨማሪ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ወንበር እንዲኖራት፣ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ዳይሬክተር የሚሾምበት፣ የነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነቶች የሚፈረምበት፣ አፍሪካዊው የቡድን አራት ጉዳይ ወሳኝ አቅጣጫ የሚቀመጥበት፣ ወዘተ በርካታ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚተላለፍበት ነው።

በተለይ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ ተመርቆ የአፍሪካ የበሸታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ትልቁን ቦታ የሚይዝ ነው። ይህ ማዕከል ሲመረቅ በወቅቱ የተገኙት አዲስ የተሾሙት የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ። ገና በሚኒስትርነት ከመሾማቸው ቅድሚያ ሰጥተው የመጀመሪያ መዳረሻቸው ያደረጉት ኢትዮጵያን እንደነበር ይታወሳል። ይህም ዋንኛው ዓላማ ማዕከሉን መርቆ መክፈት ነበር። ማዕከሉ ከጤና ተቋምነቱ ባሻገር ኢትዮጵያን ከፍተኛ የስትራቴጂ ድል የሚሰጥ በመሆኑ ዜናው ጉዳዩን ለማምከን ለሮጡ ሁሉ የሃዘን ዜና እንደሆነም ይታመናል።

ይህ ማዕከል በኢትዮጵያ እንዳይመሠረት በዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት የትህነግ ወኪል የሆነው ቴድሮስ አድሃኖም እጅግ ብርቱና ጠንካራ ሤራዎችን ሲጎነጉን እንደነበር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ለጎልጉል ተናግረዋል። የማዕከሉ ምሥረታ እርሱ በተቀመጠበት ቦታ እንደፈለገ በአፍሪካ ላይ እንዳይሠለጥን የሚገድበው ሲሆን ምዕራባውያኑም አፍሪካን የበሽታ መሞከሪያ እንዳያደርጓት በርካታ አፍሪካዊ ሥራዎችን በመሥራት የሚገዳደራቸው የሚሆን ነው። አፍሪካውያን የበሽታ መሞከሪያ እንዳይሆኑ ታላቅ ሚና ይጫወታል የተባለለት ይህ ተቋም አቅሙ ጎልቶ የሚወጣው አፍሪካውያን ወንድማቸውን መሞከሪያ በማድረግ ስልጣንና ሃብት የሚዝቁ ከሃጂዎችን ቅስም የሚሰብርም ነው።

ለጎልጉል መረጃውን የሰጡ ጉምቱ ዲፕሎማት እንደሚሉት ከሆነ ይህ ማዕከል አዲስ አበባ ላይ መከፈቱ የአፍሪካ ኅብረትን ከኢትዮጵያ እንዳይነቃነቅ የሚያደርግ ችካል ነው ይላሉ። ሆኖም ሙሉ ሥራውን ከመጀመሩና ዋና ዳይሬክተር ከመሾሙ በፊት በጸጥታ እጦትና አለመረጋጋት በሚል ከኢትዮጵያ እንዲነሳ የሚደረገው ሤራ እንዲህ በቀላሉ የሚያቆም አይደለም። ወቅቱን ጠብቆ የተቆሰቆሰው የሲኖዶሱ ውዝግብና የሰላማዊ ሰልፉ መተላለፍ ከዚህ ሤራ ውጪ ሊሆን እንደማይችል በርካታ ጠቋሚዎች አሉ።

የሰሞኑ ከሲኖዶስ ጋር በተያያዘ የተነሳው ውዝግብ ፈርጀ ብዙና ዓላማው ሃይማኖታዊ ብቻ እንዳልሆነ ብዙ አመላካቾች አሉ። በቤተ ክህነት አካባቢ ያለውን ወከባ ጳጳሳቱን አንዳንዴ የተወዛገበ መግለጫ ሲያስወጣቸው ይታያል። አንዳንዶችም እንደሚሉት የጫካው ሲኖዶስ ፍጹም ውጉዝ ከመአርዮስ የሆነ ቢሆንም ቤተ ክህነቱ አካባቢ ያሉት ጳጳሳት ሳያስቡት በተለያዩ ኃይሎች የፖለቲካ መጠቀሚያ ሳይሆኑ እንዳልቀረ ይናገራሉ።

ሕገወጡና የተወገዘው የወሊሶው ሲኖዶስ ግጭት ጠማቂና ጥላቻ ሰባኪ ነው ተብሎ የተወሰደው አካሄድ ቡድኑን የበለጠ የክፋት መሣሪያ እንዲሆን የሚገፋፋው እንደሚሆን እየታወቀ ይህ ቡድን በዚያው እያከረረ እንዲሄድ የሚገፋፋውን ውሳኔዎች ማስተላለፍ የይቅርታንና የንሰሐን መንገድ ያርቀዋል ይላሉ የቤተ ክህነት አካባቢ መረጃ አቀባዮቻችን። ከዚያ ሌላ ጳጳሳቱን አማክራለሁ በሚል የተወዛገቡና የተጣደፉ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት በዓላማ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሥራቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ሲሆን እሁድ ለት ደሴ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የታዩት ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መፈክሮች ስለ ቀጣዩ አቅጣጫ ብዙ የሚል እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

በቀጣይ ሳምንት ጉዳዩ መስመር እንደሚይዝ ይጠበቃል። የጠቅላይ ቤተክህነት የሕዝብ ግንኙነት ኮሎኔል ደራርቱ የዕርቅ ቡድን አባል መሆኗን እና ሥራዋንም የሚደግፈው መሆኑን በመግለጽ ያወጣው መግለጫ አንዱ ተጠቃሸ ነገር ማብረጃ ውሳኔ ነው። እንዲሁም በጾመ ነነዌ ወቅት ምዕመናን ከጥቁር መልበስ ሌላ በጸሎትና ጾም ወደ አምላካቸው ከመቅረብ ሌላ ምንም እንዳያደርጉ መነገሩ፤ እንዲሁም ለጽሎት ከሚያስፈልጉ መጽሐፍት ውጪ ሌላ ምንም መፈክር ይዞ ወደ ቤተክርስቲያን መምጣት አይፈቀድም በማለት ሲኖዶሱ እሁድ ያወጣው መግለጫ ቀጣዩ ሳምንት ብዙ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ አምላካች ነው ተብሏል።

በደኅንነቱና በአጠቃላይ የጸጥታው አካል ዘንድ በርካታ የውዝግቡ ባለቤቶችና ዓላማ እንዲሁም ሁሉንም ወገኖች በተመለከተ የተያዘ በርካታ መረጃ ያለ ሲሆን ለአገር ደኅንነትና ግጭቱን ላለማካረር በይደር እንዲቆይ እንደተደረገ እሁድ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ያወጣው መግለጫ ፍንጭ ሰጥቶ አልፎታል።

በቀጣዩ ሳምንት ሁኔታው እየበረደ እንደሚሄድ ሲታወቅ የውዝቡና የግጭቱ ባለቤቶች ሌሎች የጥፋት ሤራዎችን ጠንስሰው ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

Exit mobile version