Site icon ETHIO12.COM

“በ19 የፖሊስ አመራርና አባላት ላይ ከከባድ እስከ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል”

ጠዋት በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ልዩ ዞን ድንበር በተለምዶ ፊሊዶሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሰላማዊ እንቅስቃሴን የማወክ ህገ ወጥ ድርጊቶች ተስተውለዋል።

በኦሮሚያ ልዩ ዞን ክልል ውስጥ በምትገኘው ቅድስት ልደታ ቤተክርስቲያን የተሰበሰቡ ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ገብተው የታሰሩብን ሰዎች ይፈቱልን በሚል ምክንያት በድንጋይ መንገድ በመዝጋት የፀጥታ ችግር እንዲከሰት ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ምንም አይነት የታሰረም ሆነ የተያዘ ሰው እንደሌለ በመግለፅ ፖሊስ የተዘጋው መንገድ እንዲከፈት ቢያሳስባቸውም ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

ከፖሊስ በተጨማሪ የቤተክርስቲያኒቱ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ወጣቶች የታሰረ ሰው አለመኖሩን በማስረዳት መንገዱን ለማስከፈት የፀጥታ አካሉን እያገዙ በምክር እና በተግሳፅ የበኩላቸውን ጥረት ቢያደርጉም የተሰበሰቡት ሰዎች ከቦታው ለመንቀሳቀስ እና መንገዱ እንዲከፈት ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡

ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ፖሊስ በብዙ መስዋዕትነት እና በህብረተሰቡ ትብብር የተረጋገጠው የከተማችን ሰላም እንዳይደፈርስ እና በህዝቡ መሐል ውስጥ ሆነው ግጭት እንዲፈጠር ግፊት የሚያደርጉ ግለሰቦች መኖራቸውን በማረጋገጥ ፍላጎታቸው እንዳይሳካ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በወቅቱ ተዘግቶ የነበረው መንገድ እንዲከፈትና ሰላማዊ እንቅስቃሴው እንዲቀጥል የማድረግ ስራ ሰርቷል፡፡

በዚህ ወቅት ግጭቱ እንዲፈጠር በግልፅም ሆነ በስውር ሲቀሰቅሱና በተባባሪነት ሲሳተፉ በነበሩ ሃይሎች በተወረወረ ድንጋይ በ19 የፖሊስ አመራርና አባላት ላይ ከከባድ እስከ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡

ወቅታዊ ሁኔታን እንደምቹ ሁኔታን በመጠቀም የፀጥታ ሃይሉን በመተንኮስ በሚፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ ድብቅ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚሰሩ አካላትን ህብረተሰቡ ከመሃሉ ነጥሎ ሊያወጣቸው እና አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ እነዚህ አካላት የከተማችንን እና የነዋሪዎቿን ሰላም ከሚያደፈርስ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ አሳስቧል፡፡

ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም የአዲስ አበባ ፖሊስ

Exit mobile version