Site icon ETHIO12.COM

መንግስት በባለሃብቶችና ፖለቲከኞች የተዘረጋውን ሰንሰለት ተከትሎ እርምጃ መጀምሩን ገለጸ፣ ሲኖዶስ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጠ

“ሕጋዊና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመናድ፣ በአቋራጭ በማንኛውም ዓይነት ጉልበትና ሁከት እኩይ የፖለቲካ ፍላጎትን መሳካት አይቻልም” ሲል መንግስት ህግ የማስከበር ስራ መጀመሩን አሳወቀ። ስም ሳይጠቅስ “የመሥዋዕትነት ሰልፍ አዘጋጅ ” ያላቸው ክፍሎች አደረጃጀትና ድጋፍ አድራጊዎችን ሰንሰለት እንደደረሰበት አመለከተ። ቅዱስ ሲኖዶስ ቅደም ሁኔታ ያላቸውን ዘርዝሮ ለመነጋገር መዘጋጀቱን፣ ካልሆነ ግን ያለ ማንም ከላካይ “የራሴ” ባለው አደባባይ ሰልፍ እንደሚያደርግ አመልክቷል።

“የመሥዋዕትነት ሰልፍ አዘጋጅ ” በሚል ከባለ ሀብቶች፣ ከፖለቲከኞች እና ከ”መንፈሳውያን የወጣት አደረጃጀቶች” የተውጣጣ ቡድን ከማዕከል እስከ ታች መዋቀሩን መንግሥት እንደደረሰበት ገልጾ ባለው መረጃ መሰረት ለህግ የማቅረብ እርምጃ መጀመሩን ይፋ አድርጓል። በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን በአሃዝና በማንነት አልገለጸም። ሲኖዶስ ባወጣው የመቃወሚያ መግለጫ “የተያዙ ይፈቱ” ሲል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።

ኦ.ኤም.ኤን ከፍተኛ የባንክ እዳ ያለባቸውንና እዳ ባለመክፈል መዝገብ ተካተው ምርመራ እየተደረገባቸው ካሉት ውስጥ አካቶ በአማራ ክልል ረብሻውን በገንዘብ ይመራሉ ያላቸውን በስም ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ሰፊ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።

ለተከታታይ አራት ዓመታት ያለማሳለስ መንግስትን በመተቸት የሚታወቀው ሶስት መቶ ስልሳ የሚባለው የዩቲዩብ አውድ ደግሞ “የቅዱስ ሲኖዶስ የሰማእታት ጥሪ” በሚል ሰልፉ እንዲካሄድና ከልካይ ሊኖረው እንደማይገባ፣ ” ጊዜው አሁን ነው” በሚል ጥሪ ሲያደርግ አምሽቷል።

“የአፍሪካ አንድነት ስብሰባ አለ መገጣጠም” በሚል ስብሰባውን ማምከኛና ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ እንደሚያሻ፣ ይህን ዕድል ማሳለፍ እንደማይገባ የሚናገሩ ” ሰላማዊ ሰልፉ ይህን ግንዛቤ ውስጥ ባምስገባት መታቀዱን” እያስተዋወቁና እንደማይቀርበት እያመለከቱ ነው። ሲኖዶስም ቅድመ ሁኔታዎች በሚል የተቀመጡት ነጥቦች በሁለት ቀናት ውስጥ የማይፈጸሙ ከሆነ ሰልፉን ሊያስቀር የሚችል ሃይል እንደሌለ ገልጿል። የሰልፉን አካሄድ አስመልክቶ መረጃ እንደሚሰጥም ተመልክቷል። አንዳንድ የሲኖዶስ አባቶች ለመነጋገር ፈቃደኛ እንደሆኑና ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንደሚያከብሩ ገልጸው ከቀናት በፊት በየኔታ ቲዩብ መናገራቸው ይታወሳል።

” ነፃና ሰላማዊ ትግሉ ይቀጥላል። ነፃነት በነፃ፣ በብላሽ አይገኝም። በችርቻሮ ከሚገሉን በጅምላ ቢፈጁን ይሻላል” ሲል ጥሪ ያቀረበውና ከአስተባባሪዎቹ አንዱ እንደሆነ የሚናገረው ዘመድኩን ዘመዴ፣ ሲጀምር ” “…ሲሪላንካ በምን ትዝ አለኝ በማረርያም…!” ብሎ ሲሆን፣ ሕዝብ ቤተመንግስት እንዲወር ያዘዘው ” “…አረመኔ ከሃዲዎቹ እነ ዳንኤል ክብርት፣ አቢይ አህመድ፣ ሽመልስ አብዲሳ፣ ይልቃል ከፍአለ፣ ደመቀ መኮንን፣ አዳነች አቢቤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ አይደሉም…” የሚል ታግ አስሮ ነው።

“…ጥቁር ለብሳችኋል ተብለው ወደ አፋር በረሃ የጫናችኋቸውን ልጆች በአስቸኳይ ፍቱ። እስከነገ ድረስ ጠዋት ድረስ ጊዜ ሰጥተናችኋል። የእሁዱ ሰልፍ ቢቀለበስ የኦርቶዶክስ መጥፊያዋ እንደሆነ ከወዲሁ ይታወቅ። ከዚያ በኋላ ስድአደግ ባለጌ ክፍት አፎቹን አቢይ አህመድ፣ አዳነች አቢቤ፣ ሽመልስ አብዲሳን አንችላቸውም። እሁድ ቁርጥ ነው። ወሳኝም ነው። እኛ ሰላማዊነታችንን በሚገባ ለዓለም ያሳየን የጨዋይቱ ልጆች ነን” ሲልም ዘመዴ ገልጿል። ይህንን ካለ በሁዋላ በሌላ ፖስት ” እኔንም ብሆን አትስሙ። ቅዱስ ሲኖዶስን ብቻ ስሙ” ብሏል።

ከጅምሩ ችግሩን ዓለም ዓቀፍ ይዘት ለማስያዝ ግብጽ ስብሰባ ከመጠራቱ ጀምሮ፣ የተለያዩ እጆ እንዳሉበት ሲገለጽ ቢቆይም መንግስት በግልጽ ባለሃብቶችና ፖለቲከኞች እንዳሉበት ይፋ ያደረገው አመጽ፣ ነገሩን እንዳያወሳስበው ስጋት ፈጥሯል። ሁለቱም አካላት በየፊናቸው ያወጡትን መግለጫ ያንብቡ።

በወቅታዊ ጉዳዮች ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን የተሰጠ መግለጫ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በውስጥ አሠራር እንዲፈታ መንግሥት አቋም መያዙ ይታወቃል።

ለዚህምም የሀገር ሽማግሌዎችና የሚመለከታቸዉ ሁሉ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በሕገ መንግሥታችን መንግሥታዊ ሃይማኖትም ሆነ ሃይማኖታዊ መንግሥት ሊኖር እንደማይችል ተደንግጓል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው ልዩነትም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዉስጣዊ አሠራርና ከዚያም ካለፈ በፍትሐ ብሔር ዳኝነት የሚታይ ነው። አስፈጻሚው አካልም በፍርድ ቤት ሲወሰን ብቻ የማስፈጸም ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አጋጣሚዉን ለእኩይ የፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም የሚንቀሳቀሱ አካላት እየተገለጡ መሆኑን መንግሥት በልዩ ልዩ መንገዶች አረጋግጧል።

“የመሥዋዕትነት ሰልፍ አዘጋጅ ” በሚል ከባለ ሀብቶች፣ ከፖለቲከኞች እና ከ”መንፈሳውያን የወጣት አደረጃጀቶች” የተውጣጣ ቡድን ከማዕከል እስከ ታች መዋቀሩን መንግሥት ደርሶበታል።

አጋጣሚዉን በትጥቅ በተደገፈ ሁከት መንግሥትን የመነቅነቅ ፍላጎት ያለው ይህ ቡድን ወጣቶችን እየመለመለ ማሠማራት መጀመሩን፣ ለዓላማዉ በልዩ ልዩ መንገዶች ገንዘብ በመሰብሰብ እያሠራጨ መሆኑንና በሕገ ወጥ መንገድ ከታጠቁ ኃይሎች ጋርም ግንኙነት እየፈጠረ መሆኑን መንግሥት አረጋግጧል።

ለዚሁ እኩይ ዓላማ አስቀድሞ አስቦበት ያደራጁት የሚዲያ ቡድን ሥራዉን መጀመሩም ተረጋግጧል፡፡

በዚህ የክትትል ሂደት ድምጽ ያላቸውና የሌላቸው መሣሪያዎች ይዘው ሁከት የሚፈጥሩ አካላት በሥምሪት ላይ እያሉ ተይዘዋል። የቤተ ክርስቲያንን ደወል ላልተገባ ዓላማ በመጠቀምሕዝብን ለብጥብጥ የሚዳርጉ ቡድኖችም ታይተዋል።

በየአካባቢው ወጣቶችን ለግጭት የሚመለምሉና የሚያሠማሩ አካላት ተደርሶባቸዋል። የፖለቲካ ዓላማቸውን በሃይማኖት ሽፋን ለማስፈጸም የሚሞክሩ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመጠቀም የሰዎችንና የእምነት ተቋማትን መብቶች በመጣስ የመንግሥትን መልካም ስም ለማጥፋት የሚፈልጉ ሥውር እጆች እንዳሉም ታዉቋል።

በአጠቃላይ የተፈጠረውን ችግር ከመፍታት ይልቅ ችግሩን ለግልፅ የፖለቲካ ዓላማ ማሳኪያ አድርገዉ ወደ መጠቀም ተሸጋግሯል። ይህ ደግሞ የሀገርን ሰላም፣ ደኅንነት እና ልማት የሚጎዳ ነው። በመሆኑም በዚህ ተግባር ሆን ብለው የተሠማሩትን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለሕግ የማቅረብ ተግባር ተጀምሯል።

ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ከዚህ በኋላ መንግሥት ቀደም ሲል ሲገልፅ እንደ ነበረዉ ጉዳዩ ቀይ መሥመር ያለፈ ሆኖ በማግኘቱ፣ “የመሥዋዕትነት ሰልፍ” ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ የሌለ በመሆኑ ሀገራዊ መረጋጋትን ለመፍጠርና የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ሲባል መንግሥት ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ ዉስጥ የሚገባ መሆኑን ከወዲሁ ያሳዉቃል።

በዚህ አጋጣሚ ባለማወቅና በቅንነት የጥፋት ኃይሎችን የምትከተሉ ሁሉ መንገዱ ወደ ከፋ ጥፋት እንደሚወስዳችሁ ተረድታችሁ ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ መንግሥት ያሳስባል። መላዉ ህዝባችንም እንደቀደመዉ ሁሉ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር አካባቢዉንና ሰላሙን እንዲጠብቅ መንግስት ጥሪ ያቀርባል፡፡

ሕጋዊና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመናድ፣ በአቋራጭ በማንኛውም ዓይነት ጉልበትና ሁከት እኩይ የፖለቲካ ፍላጎትን መሳካት አይቻልም።

የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ/ም

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ

ቅዱስ ሲኖዶስ በበኩሉ ካወጣው ሰፊ መግለጫ ዋናው ጉይ ከዚህ በታች ያለው ነው

ይህ በንዲህ እንዳለ ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ ትላንት ምሽት የመንግሥት ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ” ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ ” ን አስመልክቶ የተሰጠው የሰልፍ ክልከላ እንደማይቀበል ይፋ አድርጓል።
” መንግሥት አሁንም ችግሩን ለመፍታት ሳይሆን ቤተክርስቲያኒቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ለማውደምና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት የታወጀ አዋጅ መሆኑን በጽኑ እንድናምን አድርጎናል ” ሲሉም ከመንግስት ጋር የተካረሩበትን ደረጃ አሳውቀዋል።

መንግስት ከአጉል እልከኝነቱ ትቶ ሲኖዶሱ “ሕገ ወጦች” ከሚላቸው ግለሰቦች ጋር በመተባበር በአደባባይ እየፈጸመ ያለውን የሕግ ጥሰት ዛሬን ጨምሮ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ውስጥ እንዲያቆምና ሕግ እና ሥርዓትን እንዲያስከብር በኃይል የወረራቸውን መንበረ ጵጵስና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለቆ ለቤተክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መዋቅር እንዲያስረክብ ጠይቋል። ተወረሩ የተባሉትን አጥቢያ ቤተክርስቲያኖች ግን በስምና በቦታ አልዘረዘረም።
– ያለአግባብ ያሠራቸውን ካህናት እና ምእመናን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቅ፣
– ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ለፈፀመው በደል በአደባባይ ይቅርታ እንዲጠይቅ፤
– በካህናት እና ምእመናን ላይ ለደረሰው ሞት እና የአካል ጉዳት ተገቢውን ካሳ እንዲክስ እና የወደሙ ንብረቶቿን እንዲጠግን
– ቅዱስ ሲኖዶስ መንግሥት በዚሁ አካሄድ ሕግ እየጣሰና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር እና ልእልና እያዋረደ የሚቀጥል ከሆነ ቤተ ክርስቲያን መብቷን ለማስከበር እስከአሁን ድረስ ፍጹም ሰላማዊ የሆነውን እንቅስቃሴዋን አድማሱን በማስፋት በየካቲት 5/2015 ዓ/ም ለማድረግ ያቀደችውንና ያሳወቀችውን ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ያለማንም ከልካይነት በራሷ አደባባይ የምታከናውን መሆኑን አሳውቋል። በመግለጫው የራሷ የተባለው የመስቀል አደባባይ ነው።
– መንግሥት ድርሻው ሰልፉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ብቻ መሆኑን ያሳሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ ” ዛሬም ቢሆን መንግሥት ቆም ብሎ በማሰብ ከእኛ ከአባቶች ጋር ሃይማኖታዊ ፣ ቀኖናዊ እና መንፈሳዊ የአስተዳደር ሥርዓታችንን ባልጣሰ መልኩ ለመነጋገር እና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት ካደረገ በውይይት ለመፍታት መንፈሳዊ በራችን ክፍት መሆኑን እናሳውቃለን ” ብሏል።
ከዚህ ውጭ ግን በሁለቱ አባቶች መካከል የተፈጠረ ችግር እየተባለ የሚነገረው ፖለቲካዊ ጨዋታ የመንግሥት እንጂ በሀገሪቱ ሕጋዊ ሰውነት የሌላቸውና ከቤተ ክርስቲያን የተለዩ ግለሰቦች ጋር ማነጻጸር ሕገ መንግሥታዊም ሆነ ሞራላዊ የሕግ መሠረት የለውም ሲል አስገንዝቧል።
ቅዱስ ሲኖዶስ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ በህገመንግስቱ የተደነገገ መሰረታዊ መብት መሆኑን ገልጾ ቤተክርስቲያን የጠራችውን ሰላማዊ እና ሕጋዊ የሆነ የመብት ጥያቄ የማፈን ሂደትን በጥብቅ እንቃወማለን ብሏል።

Exit mobile version