Site icon ETHIO12.COM

ከምዕራብ ጎንደር ዞን 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር እና ማሾ ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል

በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር እርሻ ለምቶ የተሰበሰበ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የሰሊጥ፣ አኩሪ አተር እና ማሾ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያ የቅባት እህሎችና ጥራጥሬ ግብይት ባለሙያ አቶ ጌታቸው ኃይሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በመኽር ወቅቱ የውጭ ገበያን ታሳቢ በማድረግ የተመረተ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ ነው።

በዞኑ ዘንድሮ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን አስታውሰው፣ እስካሁን 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ለማቅረብ መቻሉን ገልፀዋል።

ቀሪውን ምርት እስከ ሚያዚያ ወር 2015 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በማቅረብ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑንም አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል።

ለማዕከላዊ ገበያ ከቀረበው ምርት መካከል 304 ሺህ ኩንታል ሰሊጥ፣ ከ788 ሺህ ኩንታል በላይ አኩሪ አተር እና 14 ሺህ ኩንታል የማሾ ምርት መሆኑንም ተናግረዋል።

“ከቀረበው ምርት 868 ሺህ ኩንታሉ አምራችና አስመራች በገቡት የእርሻ ውል ስምምነት መሰረት ግዥ ተፈጽሟል” ብለዋል።

አቶ ጌታቸው እንዳሉት ሰሊጥና አኩሪ አተሩ ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ ያለው በዞኑ በሚገኙ 36 አንደኛ ደረጃ የገበያ ማዕከላት እና ከ500 በላይ አቅራቢ ነጋዴዎች አማካኝነት ነው።

በተጨማሪም 83 አስመጭና ላኪዎች ከአርሶ አደሮች ምርቱን በማሰባሰብ ቀጥታ ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ለገበያ የቀረበው ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ብልጫ እንዳለው ባለሙያው ጠቁመዋል።

ዘንድሮ በግብይቱ ላይ የተሳተፉ ባለሃብቶችና ድርጅቶች ቁጥር መጨመር እና የአኩሪ አተር ምርት ከፍተኛ መሆኑን ለጭማሪው በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የታቀደውን የምርት መጠን ለማሳካት ግብይቱ በፍጥነትና ቀልጣፋ በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በመተማ ወረዳ ሰሊጥ አቅራቢ የሆኑት አቶ ሁሴን አህመድ ዘንድሮ ከ6ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ከአምራች አርሶ አደሮች በመግዛት ወደኢትዮጵያ ምርት ገበያ እያስገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮ የሰሊጥ ምርት ቢቀንስም ጥራት ያለው ምርት የተገኘ በመሆኑ ከአምራቾች በኩንታል ከ9 ሺህ 200 እስከ 10 ሺህ ብር በሆነ ዋጋ በመግዛት ለማዕከላዊ ገበያ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሰሊጥ በተጨማሪ አኩሪ አተር ከአርሶ አደሮች በኩንታል ከ2 ሺህ 600 እስከ 3 ሺህ 100 ድረስ እየገዙ መሆኑንና እስካሁንም ከ5 ሺህ ኩንታል በላይ ገዝተው ማቅረባቸውንም አመልክተዋል።

የእርሻ ውል የያዙ ባለሃብቶችና የንግድ ድርጅቶች ተወካይ አቶ መላኩ ትዛዙ እንዳሉት፣ ከአርሶ አደሮች ጋር ውል በመውሰድ 12 ሺህ ኩንታል ሰሊጥና 16 ሺህ ኩንታል አኩሪ አተር መግዛታቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ በመኽር ወቅቱ ከለማው መሬት 3 ሚሊዮን ኩንታል የሰሊጥ፣ የአኩሪ አተር እና ማሾ ምርት መሰብሰቡም ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

EPA

Exit mobile version