Site icon ETHIO12.COM

ባለቀይ መለዮ- በቁርጠኝነትና ታማኝነት የታወቀ የውጊያ የማርሽ ቀያሪ

የኮማንዶና አየር ወለድ ጀግኖች ገድልና ጀግንነት ታሪክ ተፅፎ ለትውልድ መተላለፍ ይገባዋል- ፊልድ ማርሻል ብርሐኑ ጁላ

ኦቢኤን የካቲት 16/2015 – የኮማንዶ እና አየር ወለድ ጀግኖች ገድልና ጀግንነት ታሪክ ተፅፎ ለትውልድ መተላለፍ የሚገባው እንደሆነ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

ሃገራዊ ግዳጅ ላይ የቆዩ የኮማንዶ እና የአየር ወለድ ዕዝ አባላትና የጦር መኮንኖች በቡልቡላ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የኢፌዲሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጅላ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የቀይ መለዮ ለባሾች የላቀ ብቃት ያለው የሰራዊቱ ክፍል መሆኑን ገልፀዋል።

ኮማንዶ እና አየር ወለድ ኃይል አካላዊ ብቃቱ፣ ፅናቱ፣ ወታደራዊ ዕውቀቱና ለሀገሩ በቁርጠኝነትና ታማኝነት የታወቀ የውጊያ የማርሽ ቀያሪ፤ መለያውም የጀግኖች ምልክት ነው ብለዋል።

ባለቀይ መለዮዎች ‘የህዝብ ኩራት፣ አለኝታና መከታ የሆነ ኃይል ናችሁ’ ያሉት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፤ ወደ ፊትም የበለጠ ለማጠናከር በዕዙ ላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት እናደርጋለን ነው ያሉት።

ለዚህም በግዳጅ ላይ የነበሩ ገድሎች ምስክር ናቸው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ የኮማንዶ እና አየር ወለድ ጀግኖች ገድልና ጀግንነት ታሪክ ተፅፎ ለትውልድ መተላለፍ እንዳለበትም ገልፀዋል።

“ኢትዮጵያ አለቀላት በተባለ ጊዜ ጓደኞቻችሁን ሰውታችሁ ዋጋ ከፍላችሁና ሀገር አፅንታችሁ በመመለሳችሁ ኢትዮጵያ ታመሰግናለች” ብለዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያን ከሚቃጣባት ጥቃት ሁሉ ለማዳን ትግል ለማድረግ ዝግጅትና ብቃት ግንባታ ያስፈልጋል ብለዋል።

የመልስ ቆይታቸው ብቃታቸውን ይበልጥ አሟልተውና አጎልብታው የውጊያ ጥበብ የማዳበሪያ ጊዜ መሆን እንዳለበትም ተናገረዋል።

‘ኢትዮጵያን መጠበቅ አያልቅም፤ ግዳጅ አያልቅም’ ያሉት ፊልድማርሻሉ፣ ወታደራዊ ብቃቱን ለማረጋገጥ የሚያገለግሉ ዝግጅቶችና ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

OBN

Exit mobile version