Site icon ETHIO12.COM

ኦሮሚያ – 1ሺህ 21 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት ተሸጋገሩ

ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች የስራ ባህልን የለወጠ ውጤት ያመጡ ናቸው

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች የስራ ባህልን የለወጠ ውጤት ያመጡ ናቸው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

“የኢንተርፕራይዞች ልማትና ሽግግር ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ሐሳብ 13ኛው የኦሮሚያ ክልል የኢንተርፕራይዞች ሽግግር መርሐግብር በአዳማ ተካሂዷል።

ለ13ኛ ዙር በተካሄደው መርሐግብር በክልሉ 1ሺህ 21 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት ተሸጋግረዋል።

በሽግግር መርሐግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደገለፁት ኢንተርፕራይዞች የቁጠባ ባህላቸውን በማጎልበት ዛሬ ራሳቸውን የለወጡ ተቋማት ሆነዋል።

ኢንተርፕራይዞች በሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጥ እንዲመጣና ምርት በእሴት ሰንሰለት ውስጥ እንዲያልፍ በማድረግ ረገድም የጎላ ድርሻ እንዳላቸው አንስተው በዘርፉ የሚስተዋለውን ህገ ወጥነት ማስወገድ፣ ያልዳበረውን የቁጠባ ባህል ማጎልበት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘና ገበያ መሪ የሆነ አሰራር ማረጋገጥ ደግሞ ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ መሰራት የሚገቧቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

ኢንተርፕራይዞች ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለሚደረገው ኢኮኖሚያዊ ሽግግር መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውንም ጠቅሰው፤ ዛሬ የተሻገሩ ኢንተርፕራይዞች ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ረዥም ጉዞ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው በኢንተርፕራይዞች እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የገቢ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችሉና ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በጎጆ ኢንዱስትሪ የሚመረቱ ምርቶች የወጪ ምርትን ደረጃ የሚመጥኑ መሆናቸውን በጉብኝቱ ማረጋገጣቸውን እና በክልሉ የሚከናወነው የስራ ዕድል ፈጠራ ከክህሎት ጋር በማስተሳሰር እየተከናወነ መሆኑ ለሌሎች ክልሎች ልምድ የሚሆን ነው ብለዋል።

ሚኒስቴሩ የክልሉን ውጤታማ አካሄድ ለማበረታታት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ያስቀጥላል ያሉት ሚኒስትሯ በሁሉም ክልሎችም በተመሳሳይ ስራዎች መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የዜጎች የስራ ባህል እንዲለወጥና የንግድ ስራ ክህሎት እንዲዳብር በሂሳብና ኦዲት እንዲሁም በሙያዊ ክህሎት የማብቃት ስራ መሰራቱን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የስራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አቶ ማቲያስ ሰቦቃ ናቸው።

በዚህም ዛሬ ወደ መካከለኛ ባለሃብት የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች በ46 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ጠቅላላ የመነሻ ካፒታል ወደ ስራ በመግባት ዛሬ ላይ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ካፕታል ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልጸዋል።

ኢንተርፕራይዞቹ ከ15 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠሩ በመሆናቸው በቀጣይም የህብረተሰቡ የቁጠባ ባህል እንዲጎለብትና የተወሰደው ብድር በጊዜው እንዲመለስ በትኩረት ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version