Site icon ETHIO12.COM

እየተስፋፋ የመጣውን ልመና ያስቀራል የተባለ “የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድ” አዋጅ

በፌደራል ሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀው “የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድ” ረቂቅ አዋጅ በአገር አቀፍ ደረጃ የተባባሰ የመጣውን ልመና፣ የወሲብ ንግድን ጨምሮ ሌሎች ማሕበራዊ ቀውሶችን “እንደሚፈታ” ተስፋ ተጥሎበታል።

የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ ደረጄ ታዬ ለዋዜማ እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም ልመናን ለማስቀረት በአዲስ አበባ ደረጃ እና በክልሎች ሰፊ ጅማሮዎች ተደርገው የነበሩ ቢሆንም የሕግ ማዕቀፍ ባለመዘጋጀቱ ጉዳዩ የአንድ ወቅት ሥራ ብቻ ሆኖ ቀርቷል።

ልመናን “ለማስቀረት” የሚያስችለው የሕግ ማዕቀፉ ሲጠናቀቅ በአንድ ቋት ሰዎችን መርዳት የሚያስችል ስርዓት የሚዘረጋ ሲሆን፤ ከዚህ ሥርዓት ውጪ የሚደረግ መፅዋት ሰጪም ሆነ ተቀባይ ተጠያቂ እንደሚደረጉ ተነግሯል።

ረቂቅ አዋጁ ሥራ ላይ ሲውል አሁን ያለውን የልመና መበራከት “መፍትሄ እንደሚያገኝ” በመንግስት በኩል እምነት የተጣለበት ሲሆን፤ የሐይማኖት ተቋማት ጋር በጉዳዩ ዙርያ በጋራ ለመስራት ተደጋጋሚ ውይይቶች እየተደረጉ እንደሚገኝ ተሰምቷል።

በተለይ የኢትዮጲያ መንግስት ለጎዳና ሕይወት የተዳረጉትን እንዲረዳ በተለያዮ ጊዜያት ከአለም ባንክ ድጋፍ ማግኘቱ የተነገረ ቢሆንም፣ ከችግሩ ስፋት አንፃር ዛሬም ድረስ ተመፀዋች የሆኑ ጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር በእጥፍ እየጨመረ ይገኛል።

በአዲስ አበባ 88 ሺሕ 960 በልመና ላይ የተሰማሩ ዜጎች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን፣ 50 ሺሕ ያህሉ በዋና ከተማዋ ጎዳናዎች እንደሚኖሩ በ2015 መጀመሪያ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀለት “የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድ” ልመናን ለማስቀረት ትልቅ ሚና እንዳለው ተነግሯል። ይህም ረቂቅ ሰዎች በየመንገዱ የመስጠት ልምዳቸውን የሚያስቀር ሲሆን በልመና የተሰማሩ ወገኖችንም አደብ የሚያስዝ ነውም ተብሏል።

በቅርቡ በሚጸድቀው ሕግ የአገር ውስጥና የውጪ ረጂ አካላት በአንድ ቋት ድጋፍ አድርገው ለሚያስፈልጋቸው የማሕበረሰቡ ክፍል እንዲደርስ የሚደረግበት ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑም ተነግሯል። ልመናን የሚጠላ ዜጋ ለመፍጠርም የሥነ ልቦና ግንባታና ድጋፍ የሚሰጥ የሥራ ክፍል ተቋቁሟል።

በ2015 በሚኒስቴሩ ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባው “የቤተሰብ ዲፓርትመንት” ልጆች ወደ ጎዳና ወጥተው በልመና እንዳይሰማሩ ብሎም ለሱስ እንዳይጋለጡ ቤተሰብ ላይ የሚሰራ ነው። በቀጣይም በየክልሉ፣ በዞን ብሎም እስከ ወረዳ ባሉ ቢሮዎች ክፍሉን በማቋቋም በዘርፉ ለመስራት ታቅዷል።አዋጁ በረቂቅ ደረጃ ተጠናቆ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ፍትህ ሚኒስቴር መላኩን የዋዜማ ዘገባ አመላክቷል።

Exit mobile version