Site icon ETHIO12.COM

የፕሮፓጋንዳ ምችና የጦርነት አሻራ በትግራይ

ይህ ዘገባ የሚያሳየው ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን ነው። በአጉል የፕሮፓጋንዳ ምች የተመታ ትውልድና በዚሁ ፕሮፓጋንዳ ሰበብ ጦርነት ያሳደረው አሻራ። በትግራይ ምን ያህሉን ህዝብ እንደሚወክሉ ቢቢሲ ባይገልጽም፣ አንዳንዶች የሰላም ስምምነቱ ላይ ያላቸውን የጎፈነነ ስሜት አመልክቷል። በዘገባው የተጠቀሱት ክፍሎች የሰላም ስምምነቱ እነሱ ተዋጋንለት የሚሉትን ዓላማ አያሳካም። ግን ዳግም እንዋጋ ሲሉ አልተሰማም። ጀነራሉ ግን የሰላም ስምምነቱ ሊቀለበስ በማይችል ደረጃ ላይ እንደሆነ ይፋ መናገራቸውን ቢቢሲ ሪፖርቱን ሲያስር ገልጿል። ርዕሱ ብቻ የተቀየረውን የቢቢሲን ዘገባ ያንብቡ።

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ የበላይነትን ይዞ የቆየው ህወሓት ከማዕከላዊው መንግሥት ገለል ከተደረገ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብቶ ቆይቶ ነበር።

ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የነበረው ፖለቲካዊ ውጥረት በኮሮናቫይረስ ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ መካሄድ የነበረበት ምርጫ መራዘም እና የትግራይ ክልል ደግሞ በተናጠል ምርጫ ማካሄዱን ተከትሎ ውዝግቡን ወደ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ማድረሱ ይታወሳል።

ይህ ሁኔታ ግን ጥቅምት 23/2013 ዓ.ም. ላይ ወደ ጦርነት ተቀይሮ አገሪቱ ወደለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ገብታ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እንደተቀጠፈ ተነግሯል።

ይህ አስከፊ ጦርነት ለሁለት ዓመታት ተካሂዶ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት መሪዎች ፕሪቶሪያ ላይ የሰላም ስምምነት ተፈራረመው ከቆመ አምስተኛ ወሩን ይዟል።

በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል በተደረሰው ግጭትን በዘላቂነት የማስቆም ከተፈረመ በኋላ ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ ስምምነቱ በተለያዩ መልኮች ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

ከደም አፋሳሹ ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በአካል የተገናኙት የህወሓት መሪዎች በትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት ለመመስረት በዝግጅት ላይ ናቸው።

በሁለቱ ወገኖች በኩል በተደረሰው ስምምነት መሠረት የትግራይ ኃይል አባላት ለተሃድሶ እንዲዘጋጁ ተነግሯቸው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

በዚህ ጦርነት በትግራይ ኃይሎች በኩል ተሰልፈው ተዋጊ የነበሩ እንዲሁም የአካል ጉዳት የደረሰባቸው የትግራይ ኃይል አባላት ስለ ሰላም ስምምነቱ የተለያዩ ስሜቶችን እያንጸባረቁ ነው።

“የዐይኔን ብርሃን አጣሁ”

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንዳንድ የትግራይ ኃይል አባላት የሰላም ስምምነቱ ሲፈረም ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ እንደነበሩ እና ስለሰላም ስምምነቱ ምንም የሚያውቁት ነገር እንዳልነበረ ያስታውሳሉ።

የሰላም ስምምነቱ መፈረሙ በይፋ ሲነገርም ከባድ ድንጋጤ እና ግራ መጋባት ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል።

የ21 ዓመቱ ሃፍቶም በውጊያ ውስጥ ተመትቶ የዐይኑን ብርሃን አጥቷል፤ መንጋጋው እና አፍንጫው ላይ በደረሰበት ጉዳት የተነሳም ለመተንፈስ ይቸገራል።

በአሁኑ ወቅት በተመሳሳይ ከተጎዱ ሌሎች ጓዶቹ ጋር በከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ይናገራል።

ሃፍቶም የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነበር። በወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በተጣሉ እገዳዎች ምክንያት ከትምህርት ገበታ ተለይቶ እንደነበር ያስታውሳል። በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በተፈጸሙ ግፍና በደሎች ምክንያት መጋቢት 17/2013 ዓ.ም. ላይ ከትግራይ ኃይል ጋር መቀላቀሉን ይናገራል።

ሃፍቶም፣ ጦርነቱ ከትግራይ ተነስቶ ወደ አጎራባች ክልሎች ተዛምቶ የትግራይ ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሱ በነበሩበት ወቅት በጋሸና አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰበት።

“ነሐሴ 13/2013 የዐይን እና የአፍንጫ ጉዳት ደረሰብኝ። አሁን ማየት አልችልም። ቀኝ ዐይኔ ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል። የግራ ዐይኔ ለተወሰነ ጊዜ መብራትን እና የፀሐይ ብርሃንን ማየት ትችል ነበር፣ እንደበፊቱ ሙሉ በሙሉ አላይም” በማለት የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶች አቅርቦት ስለሌለ ሕክምና ለማግኘት ገና በተስፋ እየተጠባበቀ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጿል።

ሆስፒታል ውስጥ በነበረበት ወቅት የሰላም ስምምነቱ መፈረሙን የሰማው ሃፍቶም፣ ሕዝቡን በየዕለቱ ከሚደርስበት ስቃይ ለሚታደግ፣ የተራበው እርዳታ እንዲያገኝ ስለሚያግዝ ለስምምነቱ በጎ አመለካከት አለው።

ነገር ግን ስምምነቱ የተሟላ ሊሆን የሚችለው “በተደረገው ስምምነት መሠረት የውጭ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ ከትግራይ ሲወጡና የተፈናቀለው ሕዝብ ወደ ቀየው ሲመለስ ነው” ይላል።

ሃፍቶም ወደፊት የዐይን ብርሃኑ በሕክምና ተመልሶለት፣ በኮቪድ ወረርሽን እና በጦርነት ምክንያት ወዳቋረጠው የትምህርት ገበታ ለመመለስ ጽኑ ፍላጎት አለው።

በትግራይ ክልል የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ባለሙያ ሆኖ ያገለግል የነበረው ፀጋይ ገብረመድህን ደግሞ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ነበር የትግራይ ኃይሎችን የተቀላቀለው።

ፀጋይ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ደቡብ አፍሪካ ላይ የሰላም ስምምነት መፈራረሙን ሲሰማ የተደበላለቀ ስሜት እንደተሰማው ይናገራል።

“ጦርነት አውዳሚ ነው። ስምምነቱ ሰላማዊውን ሕዝብ ከሞት፣ ከጉዳት እና ከመፈናቀል ፋታ የሚሰጠው በመሆኑ ትንሽ ተደስቻለሁ። ነገር ግን የሰላም ስምምነቱ ትግሉ ከተነሳበት ዓላማ አንፃር ሲታይ በጣም የሚያሳምም ነው” ይላል።

ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ከሁሉም ወገን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች መሞታቸውን ዘገባዎች ይጠቁማሉ። ሌሎች ሺዎች ደግሞ አካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

“ስለስምምነቱ የምናውቀው ነገር አልነበረም”

የትግራይ ጦርነት በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ሲቀሰቀስ የ35 ዓመቱ ሸዊት ከአሜሪካ መጥቶ በጦርነቱ መሳተፉን ይናገራል።

“የመኖር እና ያለመኖር ጉዳይ በመሆኑ ለመታገል መጣሁ” የሚለው ሸዊት በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች በጦርነቱ ውስጥ መሳተፉን በመግለጽ፣ ስለ ስምምነቱ ሠራዊቱ የሚያውቀው ነገር ስላልነበረ በሠራዊቱ ውስጥ “መጥፎ ስሜት ተፈጥሮ እንደነበር” ሸዊት ለቢቢሲ ትግርኛ ገልጿል።

ጨምሮም “ይህ ስምምነት አሁን ሳይሆን ከሁለት ዓመት በፊት መፈጸም የነበረበት ነው” በማለት ደስታ እንዳልተሰማው ይናገራል።

“የትግራይ ሕዝብ ሰላም ይፈልጋል፤ ለሰላም ብለንም ታግለናል፤ መስዋዕትነትም ከፍለናል። ከሁለት ዓመት በፊት ነገሮች መስተካከል እየቻሉ በጥቂት መሪዎች ችግር ምክንያት መስዋዕትነት ከፈልን።

“በረሃብ፣ በመድኃኒት እጦት እና በጭፍጨፋ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አጣን። አሁን የህወሓት ይሁኑ የብልጽግና መሪዎች መጥተው ምንም እንዳልተፈጠረ ዕርቅ ሲፈጽሙ በጣም ያስቆጣል” ሲል ይተቻል።

ሸዊት ስምምነቱ መሬት ላይ ያለውን ነገር ያገናዘበ እንዳልሆነ ይናገራል።

“አገራችንን ለመጠበቅ ታገልን። ትጥቃችሁን ትፈታላችሁ ሲሉን አዘንን። የኤርትራ ጦር እና ሌሎች ኃይሎች ጠቅልለው ትግራይን ሳይለቁ ትጥቅ ለማስፈታት መጣደፋቸው የሥልጣን ጥማትን የሚያሳይ ነው” ሲል የህወሓት መሪዎችን ይወቅሳል።

ከመጋቢት 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ወራት የዘለቀው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት የተኩስ አቁም ተጥሶ ነሐሴ ወር ላይ ውጊያው መልሶ ከተቀሰቀሰ በኋላ የትግራይ ኃይሎች ከበርካታ አካባቢዎች ተገፍተው ነበር።

ስምምነቱ በፕሪቶሪያ በተፈረመበት ወቅት የትግራይ ኃይሎች እንደ ሽሬ፣ አክሱም፣ አድዋ እና አላማጣ ከመሳሰሉ ከተሞች ወጥተው የመንግሥት እና የአጋሮቹ ሠራዊት መቀለን ለመቆጣጠር እየገሰገሱ ነበር።

“ሥልጣናቸውን ለማስጠበቅ ያደረጉት ነው”

የትግራይ ኃይሎች አባል ክብሮም ዘወሊ የፕሪቶሪያ ስምምነት ከመፈረሙ ከሁለት ሳምንት በፊት ጥቅምት 09/2015 ዓ.ም. በኮረም አካባቢ በሰቆጣ መንገድ ላይ እግሩን ተመታ።

“ትግራይ የራሷን የፖለቲካ ዕጣ ፈንታ እንድትወስን እና በግሌ ደግሞ ለትግራይ ነፃነት ነው የታገልኩት” ይላል ክብሮም።

በአሁኑ ወቅት በሁለት ምርኩዝ ተደግፎ ካልሆነ በስተቀር መሬት መርገጥ አይችልም። በመንግሥት ተቋማት ሕክምና ማግኘት ስላልቻለ ቤተሰቦቹ በግል ህክምና እያሳከሙት ይገኛል።

“ስምምነት ላይ መደረሱን ስሰማ በጣም ደነገጥኩ። ከባድ ጦርነት ውስጥ ተገብቶ፣ በትግራይ ውስጥ ለተፈጸመው ግፍ እና በደል ተጠያቂነት ሳይኖር የሰላም ስምምነት ይደረጋል የሚል ግምት አልነበረኝም።

“ስምምነት መደረጉ ከተገለጸ በኋላ በአንድ በኩል ሕዝቡ ከድሮን እና ከከባድ የጦር መሳሪያ ድብደባ ያርፍ ይሆን የሚል የተደበላለቀ ስሜት ተፈጠረብኝ። ነገር ግን የሰላም ስምምነት መደረጉ ካልቀረ ይሄ ሁሉ ኪሳራ ከመድረሱ በፊት መሆን ነበረበት የሚል ቅሬታ አለኝ” ይላል።

በትግራይ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ምክንያት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በረሃብ እና በግድያ መሞታቸውን የቤልጂየሙ ጌንት ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያመለክታል።

ከክልሉ ውጭም በትግራይ ተወላጆች ላይ ሰፊ እስራት እና ግፍ እንደተፈጸመ የመብት ተሟጋቾች መግለጻቸው ይታወሳል።

ሸዊት ቢተው “ሠራዊቱ የጦርነት ፍላጎት የለውም። ሰላም አስፍኖ ወደ መደበኛ ኑሮው መመለስ ነው የሚፈልገው” ይላል።

እሱ ግን ለምንድነው በጥቂት ሰዎች ስህተት ይህን ያህል መስዋዕትነት የከፈልነው? ይህ ሁሉ አገር የሚተካ ትውልድ ለምን ተሰዋ? እኛስ እንደ የትግራይ ተወላጅ ከዚህ ጦርነት ምን አተረፍን የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሳል።

“የትግራይ መሪዎች ለዚህ መልስ የላቸውም። ከአንድ ጦርነት ምን ተጠቀምን ለሚለው መልስ መስጠት ካልቻሉ ደግሞ በከንቱ ነው ይህን ሁሉ መስዋእትነት የከፈልነው ማለት ነው” የሚል አቋም አለው።

በማስከተልም “ይህ ሁሉ ተከስቶ ምንም እንዳልተፈጠረ ሲደሰቱ ስናያቸው ያስደሰታቸው ሰላሙ አይደለም፤ የሥልጣን ጥማት እና የግል ፍላጎታቸው እንጂ። ስለዚህ የህወሓት መሪዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያደረጉት ስምምነት የራሳቸውን ሥልጣን ለማስጠበቅ ነው” ሲል ይተቻል።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በወቅቱ “እኛ ትጥቅ አንስተን ሕዝባችንን ለማዳን የምንችልበትን ዕድል አይተን ተዋጋን። ከነትጥቃችን ሕዝባችን የሚጠፋበት ሁኔታ ሲፈጠር፣ ይህንን ማስወገድ ስለሚገባን በሰላማዊ መንገድ ሕዝቡን በምናድንበት ሁኔታ ወደ ሰላም የማንመጣበት ምክንያት የለም” ብለው ነበር።

ህወሓት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከ27 ዓመታት በበላይነት ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት ትግራይ ውስጥ ተቃዋሚዎችን በማሰር እና በማፈን ፖለቲካዊ ሥልጣኑን ጨብጦ ቆይቷል በሚል ይወቀሳል።

በክልሉ የሕዝቡን ፍላጎት የሚያሟላ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እድገት አላረጋገጠም ተብሎም ሲወቀስም ቆይቷል።

“የሚጠበቀውን ውጤት ያስገኘ አይደለም”

ስምኦን (ስሙ የተቀየረ) ከትግራይ ጦርነት በፊት በኢትዮጵያ እና በተለያዩ አገራት ከቴክኖሎጂ ጋር በሚያያዙ እና የቴሌኮሙኒኬሽን ሥራዎችን ይሰራ ነበር።

ጦርነቱ ትግራይ ውስጥ ከተካሄደው ምርጫ ጋር የሚያያዝና ወደ ነፃነት የሚያመራ ነው የሚል እምነት እንደነበረው የሚናገረው ስምኦን፣ በዚህም የትግራይን ኃይሎችን ተቀላቀሎ በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፏል። የሰላም ስምምነቱ የትግሉን አላማ የሚያሳካ ነው ብሎ እንደማይቀበለው ይናገራል።

“የጦርነቱ አካሄድ እና በከተማ እና በገጠር የተፈጸመው ግፍ እኔ እና አብዛኛው በትግራይ ኃይል ውስጥ ያለ ወጣት ትግራይ ነፃ አገር እንድትሆን ምኞት ያለውና ይህንንም ምኞት ለማሳካት የታገለ ይመስለኛል። ስለዚህ አብዛኛው የሠራዊቱ አባል የሰላም ስምምነቱ ይህን ምኞት ያራዝመዋል የሚል ስጋት አለኝ” ይላል።

የትግራይ ወጣቶች ለጊዜያዊ እርዳታ ወደ በረሃዎች አልወጡም የሚለው ፀጋይ ገብረመድህን “የትግራይ ወጣት ለነፃነት፣ ለህልውና፣ እና ማንነነቱን ፈልጎ ነው የወጣው” በማለት የሰላም ስምምነት ይህንን ፍላጎት የሚያሟላ አይደለም በማለት ደስተኛ አለመሆኑን ይገልጻል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሰላም ስምምነቱ ጦርነቱን በማስቆም የሕዝቡን ስቃይ የሚያበቃ በመሆኑ በአዎንታዊ ውሳኔነት የሚመለከቱ በርካታ ሰዎች አሉ።

ከወራት በፊት የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እየሆነ ሲሆን፣ አሁንም የሚቀሩ ነገሮች እንዳሉ በሁለቱም ወገኖች እየተነገረ ነው።

ከእነዚህም መካከል በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም፣ ከፌደራሉ ሠራዊት ውጪ የሚገኙ ኃይሎች ከትግራይ ሙሉ ለሙሉ መውጣት፣ የህወሓት ተዋጊዎችን ተሃድሶ እና መልሶ መቋቋም ይጠቀሳሉ።

ከህወሓት ከፍተኛ የጦር አዛዦች መካከል አንዱ የሆኑት ጄኔራል ምግበይ በአንድ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ይህ ሰላም የትግሉ ፍሬ መሆኑን በመጠቆም “ጥያቄያዎቻችን እና ፍላጎቶቻችን በሰላማዊ መንገድ እንድንፈጽም ያስችለናል፤ መደናቀፍ የለበትም” ሲሉ ተደምጠዋል።

በተጨማሪም የትግራይ ኃይል አዛዥ እና በክልሉ የጊዜያዊ መንግሥት ለማዋቀር የተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረዳ የሰላሙ ሂደት የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ መድረሱን ለመገናኛ ብዙኃን አረጋግጠው ነበር።

Exit mobile version