Site icon ETHIO12.COM

ወልቃይት – የብልጽግና ውዝግብ፤ ተፈናቃይ ዜጎች የመንግስት መከራው

pp

«በቅርብ ነው የመጣሁት፣ የ10 ወራት ሕጻን ልጅ አለችኝ፣ ምንም የማቀምሳት ነገር የለኝም፣ የምንተኛው መሬት ላይ ነው፣ ጡቴን ብቻ ነው የምትስበው፣ ጡቴም ባዶ ነው፣ ምንም ነገር ላቀምሳት አልቻልሁም።»

አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ጃራ የመጠለያ ጣቢያ

የወልቃይት ጠገዴ ሁመራ … ጉዳይ ሰፊ ዋጋ የተከፈለበት እንደሆነ በቦታው ያሉ ብቻ ሳይሆኑ ታሪኩን ከነዋሪዎች አንደበት የሰሙ በቅጡ ይረዱታል። የወልቃይት ነዋሪዎች “ነጻ ወጣን” ብለው ሲመሰክሩ የተሰማው “እውን ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ሆኗል” በሚል እጅግ ምሬትና ድንጋጤን የፈጠረ ነበር። ከግድያው፣ ማፈናቀሉና አፈናው በላይ “እስክስታ አትውረዱ፣ በአማርኛ አትዝፈኑ፣ የኢትዮጵያ ባንዲራ ጥለት ያልበት ቀሚስ አትልበሱ፣ አማርኛ ጭራሽ አትማሩና አትናገሩ …” መባላቸውን ካድሬዎች ሳይሆኑ “ሰዎች” በ “ሰውኛ” ቋንቋ ሲናገሩ የተሰማ ነውና ማስተባበያ ሊቀርብበት የሚችል እንዳልሆነ ንጹህ ህሊና ያላቸው ይስማማሉ። ጎንደር ዩኒቨርስቲ አጥንቶ ያቀረበው የጅምላ ጭፍጨፋን ጨምሮ።በተመሳሳይ ባይጋነንም ወልቃት ነሳ ስትወጣና ከወጣች በሁዋላ ዝርዝሩ በግልጽ ይፋ ባይሆንም በትግራይ ተወላጆች ላይ የተፈጸመ የበቀል ፍርድ እንዳለ ሪፖርት መቅረቡም ይታወሳል።

«ያለነው ሜዳ ላይ ነው፣ የምንተኛውም ያው ከዋልንበት ላይ ነው፣ እኔ ምንም የያዝኩት ልብስ የለም፣ አንዲት የብርድ ልብስ ለአምስት ቤተሰብ ነው የምንጠቀም፣ ከእኔ የባሱ ደግሞ ምንም የማይበሉ የማይጠጡ አሉ፣ እርዳታ ምንም አልገባም፣ ተፈናቃዩ ህይወቱን እየመራ ያለው በደብረብርሀን ህዝብና በከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ብቻ ነው።»

የአማራ ክልል ተፈናቃዮች

በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሲቪል ሰዎች፣ ንብረትና ተቁማት የበላው ጦርነት ሲጠናቀቅ ይህ ከላይ የተጠቀሰው አካባቢ በአማራ ክልል ስር ግብቷል። ራያም እንደዚሁ። ሌሎችም ህዝብ ጥያቄ እያነሳባቸው ያሉ አካባቢዎች አሉ። በትግራይ በኩል ትህነግ ሰፊ ቁጥር ያላቸውን ህጻናትና አዋቂ ሳይል ማስጨረሱና አቅም ሲከዳው የቀረበለትን የሰላም ሰነድ መፈረሙ ይታወሳል። በፈረመው የሰላም ሰነድ ላይ የወልቃይት ጉዳይም አልተካተተም።

መኝታ የለም። ከላይም ከታችም ውሃ ነው። መድሃኒት የለም። በቂ ምግብ የለም። ያለፉትን ሁለት ዓመታት ያሳልፈነው በዚህ መልኩ ነው። ሁሉም ነገር ከምንሸከመው በላይ ሆነ። ከዘነበ ውሃው በሙሉ ወደ ውስጥ ስለሚገባ መተኛ የለንም። በቂ ልብስ አላገኘንም።

በሽሬ ያሉ የትግራይ ተፈናቃዮች

በደፈናው ከሰላም ስምምነቱ በሁዋላ ” የአማራና የኤርትራ ሰራዊት ይውጡ” እያለ ሲጠይቅ የነበረው ትህነግ አሁን ትግራይ ከያዘችው አካባቢ በስምምነቱ መሰረት ከፌደራል ሃይል በስተቀር ሌላ ሃይል እንደሌለ ይፋ ከሆነ በሁዋላ የአላማጣ ህዝብ “አማራ ንኝ” ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣቱን ለማስተባበል ባወጣው መግለጫ “ምዕራብ ትግራይ” ሲል የሰየመው የወልቃይት ጠገዴና ዙሪያው ያሉ የአማራ ሰራዊት እንዲወጣ ጠይቋል። ይህ ግርድፍ ገጽታ ነው።

ወልቃይት የብልጽግና ፓርቲ ውዝግብ?

ከላይ ብዙም ሳይብራራ የቀረበው ግርድፍ መረጃ እንዳለ ሆኖ የብልጽግና ፓርቲ እገሌ ከዕገሌ ሳይል ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ስፍራቸው እንዲመለሱ ሙሉ በሙሉ ተስማምቶ ነበር። ስምምነቱ ብሄር ላይቶ ባያስቀምጥም በኦነግ ሸኔ አማካይነት ከኦሮሚያ የተፈላቀሉና በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ በአወዛጋቢዎቹ ስፍራዎች ሲኖሩ የነበሩ ተፈናቃይ የትግራይ ተወላጆች ነበሩ ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲደረግላቸው ፓርቲው በአንድ ድምጽ ያለ ልዩነት የተስማማው። ግን ተግባራዊነቱ ላይ አልሆነም። ይልቁኑም ይህን ጉዳይ ሚስጢር አድርገው በሌላ ጉዳይ መሻኮትን የመረጡት የኦሮሚያና አማራ ብልጽግና ጸብም የሚቀዳው ከዚህ ላይ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ይገልጻሉ።

አማራ ክልል ከወልቃይት ጠገዴ የተፈላቀሉና በህግ የማይፈልጉ የትግራይ ተወላጆችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመለስ ምን እንደከበደው ግልጽ ባያስቀምጥም ፍላጎት ያለው አይመስልም። የወልቃይትን ጉዳይ ይዘው ሲታገሉ የነበሩት ኮሎኔል ደመቀ “እኛ ከትግራይ ህዝብ ጋር አብሮ የመኖር ችግር የለብንም” ሲሉ ተቃውሟቸውና ትግላቸው የማንነትና ከአማራ ክልል ጋር ተዋህዶ መኖር ወይም ” አማራ ነን” የሚል ብቻ እንደሆነ ማመልከታቸው አይዘነጋም።

በፓርቲ ደረጃ የተደረገው ስምምነት ተግባራዊ ያልሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው አንኳር ነጥብ ሲነሳ፣ አማራ ክልል ” የወሰን ማስተካከል ተደርጎ በህግ ወልቃይት ጠገዴና አካባቢው ቀድሞ ይረጋገጥልኝ” የሚል አቋም እንደሚያራምድና ይህንኑ አሳቡን ይዞ በደብረዘይቱ የመጨረሻው የብልጽግና ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ማንጸባረቁን ስምተናል።

ይህ አካሄድ ከህግም ሆነ ከህገመንግስት አንጻር በሂደትና በጥንቃቄ የሚታይ እንደሆነ ተጠቅሶ ቅድሚያ ህዝብ እንዲሆን በቀርበው መከራከሪያ ላይ ስምምነት ባለመደረሱ ጉዳይ ለቀታይ ውይይት ተዛውሯል።

ኦሮሚያ ከክልሉ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው እንደሚመልስ ቢስማም በሚፈለገው ደረጃ አለማከናወኑ አማራ ክልል በገባው ቃል መሰረት ባለማከናወኑና የተነሳ “ሁሉም ተፈናቃይ እኩል ተፈናቃይ ነው፤ ማንም ዜጋ በፍለገበት የአገሪቱ ክፍል ተዛውሮ እንዲኖር የሚፈቅድ ህገ መንግስት ባለበት አገር ትግሬዎች አይምጡብን ማለት አይቻልም” የሚል ጥብቅ መከራከሪያ ከኦሮሞ የብልጽግና አመራሮች ዘንዳ መነሳቱ ምስክሮች አጫውተውናል።

በትግራይ በኩል ተፈናቃዮችን ይዞ የመነገድ ወይም እርዳታ የመሰብሰብ እንዲሁም የፖለቲካ አጀንዳ ላለማጣት የሚደረግ ፍላጎት መኖሩ፣ በአማራ ክልል ቅድሚያ ይዞታዎቹ “የኔ ሆነው ይጽኑ” የሚል አቋም መያዙ ህዝቡን መከራ ላይ ጥሎታል።

ተፈናቃዮች የፌደራ መንግስት መከራው

ገዢው ፓርቲ ብልጽግና እንደመሆኑ የፓርቲው ስምምነት የመንግስት ነው። ሆኖም ግን የፓርቲ ስምምነት አንዳንድ ጊዜ በተወሰኑ ግሩፖች ወይም የተለየ ፍላጎት ባላቸው መካለል በሚፈጠር አለመግባባት ሲጣስ ይታያል። ይህንኑ ቀዳዳ የተለያዩ ሚዲያዎችና የዩቲዩብ ተንታኝ ነን የሚሉ ከራስቸው ፍላጎት አንጻር እይንቦረቀቁ ስለሚያጦዙት በመካከሉ ህዝብ መፍትሄ እንዳያገኝ ደንቃራ ሆኖበታል።

በፓርቲው የመጨረሻ ስብሰባ ሕዝብ እናስቀድምና ሌላውን ጉዳይ በሰከነ መንገድ እናስኪደው። ለዚሁ ተግባር የተቋቋሙ አካላት የድንበርና የይገባኛል ጉዳይን ለአንዴና ለመጨረሻ እልባት ለመስጠት እየሰሩበት ነው። ይህንን ሁላችሁም የምታውቁት ነው። እነሱን በትዕግስት መጠበቅ ይገባል የሚል አቋም በመያዝ የመንግስትን ችግር በመዘርዘር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

አሁን ላይ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአማራና ትግሬ ተፈናቃዮች አሉ። እነዚህ ሁሉ የመንግስት መከራው ናቸው። በዘር ላይ የተተከለው አወቃቀር ሲያከማቸው የኖረው ችግር ሞልቶ የፈሰሰባት ኢትዮጵያ ለዜጎቿ አልተመቸችም። በዚህም የችግሩ ምንጭ የሆነውን ህገመንግስት እንኳን ለመቀየር አንድ ፊደል ለመንካት የማይችለው መንግስት እንዴት ለህዝብ ስቃይ መፍትሄ ያብጅ? እንዴት ዘላቂ ስልት ይንደፍ? ቀድሞ እንዲቆለፍ ተደርጎ የተዘጋጀውና መንግስትና ህዝብን ቀፍድዶ የያዘው ህገመንግስትም ሆነ የወሰንና የማንነት ጥያቄ እንዲፈቱ የተመሰረቱት ተቋማት ስራቸውን እንዳይሰሩና ፈጥነው ወደ ውጤት እንዳይሄዱ እንቅፋቱ ብዙ ነው።

መንግስትን የሚቃወሙ አብረው ተቋማቱን ስለሚደበድቡና መልሰው ወቃሽ ሆነው ስለሚቀርቡ ጨዋታው ሁሉ ባለህበት እርገጥ እንዲሆን ማድረጉን ከዕርቅ ኮሚሽን የወጡ ቅሬታዎች ያስረዳሉ። ይህ ኮሚሽን ህገ መንግስት እስከመቀየር የሚደርስ ስልጣን ተረክቦ ተጓዥ ተሳታፊዎችን እያበዛ ቢንቀሳቀስም፣ ግልጽ አላማቸው የማይታወቅ፣ የብሄር ፖለቲካን እንደማይወዱ በሚናገሩ ነገር ግን በብሄር ስር ተወትፈው የሚዘምሩ መከራው ሆነውበታል።

እስከወዲያኛው የሚዘልቅ መፍትሄ እስኪበጅ “ሰላምዊ ዜጎችን” ወደ ነበሩበት መልሶ ማስፈር ህልም የሆነባት ኢትዮጵያ የክልል ፓርቲዎች ጡናቸውን እያሳዩ ህዝቡን በቁም እየገለደሉት ነው።

ለዓመት ወይም ከዛ በላይ ቤተሰብ ይዘው በየዱሩና በረንዳው የሚነከራተቱ ዜጎችን የማያከብሩ፣ እኩል የማያቅፉ፣ “የኔ ብሄር ወደ ነበረበት ይመልስ፣ ሌላው እንደተበተነ ይቅር” የሚል አቋም የሚያዝባት ኢትዮጵያ እንዴት ነው አንድነቷ እውን የሚሆነው? ትግሬ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን አንድነት ምንድን ነው? አማራ ተፈናቅሎ መደመር ምንድን ነው? ኦሮሞ በስም እየተሰደበ እኩልነት ምኑ ጋር ነው? በሶማሌ ክልል አማርኛ የሚባል ነገር እየተፈለገ እንዲጠፋ እየተደረገ ምኑ ነው አካታችነት? ብዙ አስተያየት የሚሰጡ አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንግዲህ እነዚህን በስም አብረው ያሉ፣ በግብር የሚለያዩትን ነው ሰብስበው አገር የሚመሩት።

አሁን ላይ እንደሚሰማው መንግስት በሁሉም ላይ ቃላቸውን የማያከብሩና ዜጎችን አክብረው ወደ ነበሩበት የማይመለሱ ከሆነ እርምጃ እንደሚወስድ ነው። ዜጎች በየጫካው መከራቸውን እያዩ የሚኖሩበት ጊዜ እንዲያበቃ ቆፍጠን ያለ አቋም እንደተያዘ ተሰምቷል። ይህንኑ አቋም ከህዝብ ይልቅ ጠበንጃ ይዘው ዝርፊያና ግድያ ላይ ለተሰማሩ በመወገን ለማሰናከል ከወዲሁ ለጉዳዩ ሌላ መልክ በማስያዝ ጩከት መጀመሩ እየተሰማ ነው። እውነት ለሃቅ እንሰራለን የሚሉ ካሉ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው እንዳይመለሱ አስቀድመው ዘመቻ የጀመሩትን ” ተፈናቃዮች የየት አገር ዜጎች ናቸው? ማንስ ያስብላቸው?” በሚል መጠየቅ የዜግነት ግዴታ ይሆናል።

Exit mobile version