አብን የተጀመረርው የአማራ ልዩ ሃይልን መልሶ ማደራጀት እንዲቆም አሳሰበ

አብን “አጋልጣለሁ” ሲል የአማራ ህዝብ ላይ ተፈጸመ ያለውን በደል ዘርዝሮ የተጀመረው ልዩ ሃይልን በአዲስ መንገድ በብሄራዊ የጸጥታ መዋቅሮች ውስጥ ማደራጀት እንዲቆም ጥየቀ። በሌሎች ክልሎች የተጀመረው ይህ ተግባር አስመልክቶ ያለው ነገር የለም።

የተደረገ ውይይትም ሆን ቅድመ ዝግጅት እንደሌለ አስታውቆ አብን ያወጣው መግለጫ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር፣ የክልል ጸጥታ የጸጥታ አመራሮች፣ መንግስትና የመከላከያ ኤታማዦር ሹም ከተናገሩትና ከሰጡዋቸው መግለጫዎች የተለየ ነው።

የአማራ ክልል ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት እንዳለበት፣ በቀደመው ጦርነት ሶስት ጊዜ ተወሮ ከፍተኛ ውድመትና መከራ፣ እንዲሁም ግድያ የተፈጸመበት ህዝብ እንደሆነ ያስታወቀው አብን፣ ድርጊቱ እየተፈጸመበት ያለው አግባብ ክብረ ነክ እንደሆነም አመልክቷል። በተከታታይ የማጋለጥ ስራም እሰራለሁ በሚል ዝቷል።

እስካሁን በከፍተኛ ሃላፊነት መንፈስ ነገሮችን በሰከነ መንገድ ሲመለከት መቆየቱን ያስታወቀው አብን ባወጣው ሰፊ መግለጫ መንግስት በቀጣይ እንዲተገብራቸው፣ ክልሉም በበኩሉ እንዲያከናውናቸው ያላቸውን ነጥቦች በመመሪያ መልክ አስፍሯል። አብን አንድ መከላከያ ሃይልና የጸጥታ መዋቅር በአገሪቱ መኖር እንዳለበት ከሚያምኑት መካከል እንበነበር ይታወሳል።

በወቅታዊ ጉዳይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ፣

________

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው የአቋም መግለጫ የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የክልል ልዩ ኃይሎችን ለማፍረስ ያሳለፈው ውሳኔ በሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ በእኩል ደረጃ ተፈጻሚ የማይሆን እና የውሳኔው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት መሆኑን በመገምገም ፣ መንግስት የአማራ ልዩ ኃይልን ለማፍረስ ያሳለፈው ውሳኔ ወቅቱን ያልጠበቀ ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ እና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የአማራ አካባቢዎችን እና የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተገማች እና ቀጥተኛ ለሆነ ጥቃት እና አደጋ የሚዳርግ አደገኛ ውሳኔ መሆኑን በመግለጽ ውሳኔው ተፈጻሚ እንዳይሆን ማሳሳቡ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ድርጅታችን አብን ያቀረበውን ማሳሳቢያ ወደ ጎን በማለት የፌዴራሉ መንግስት የክልሉን ልዩ ሃይል ትጥቅ ለማስፈታት በመንቀሳቀሱ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በክልሉ ልዩ ኃይል እና በፌዴራል የጸጥታ ተቋማት መካከል ከፍተኛ ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሁኗል፡፡

ውጥረቱን ተከትሎ ድርጅታችን መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ያለ በቂ ዝግጅት ፣ ውይይት ፣ የጋራ መግባባት እና መተማመን በድንገት እና ያለበቂ የጸጥታ ዋስትና የፌዴራል መንግስት የክልሉን ልዩ ኃይል ለማፍረስ ያሳለፈው ውሳኔ እና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየሄደበት ያለው መንገድ ሃላፊነት የጎደለው እና ዳፋው በአማራ ክልል ብቻ ሳይወሰን በሃገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አለመረጋጋት የሚፈጥር ፣ ክልሉን እና ሀገራችን ኢትዮጵያን ወደ ሌላ የቀውስ አዙሪት የሚከት አደገኛ አካሄድ መሆኑን በማስጠንቀቅ ፣ የፌዴራሉ መንግስት ውሳኔውን በአፋጣኝ እንዲቀለብስ እና ከአማራ ክልል መንግስት እና ከክልሉ ሕዝብ ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት እና ምክክር እንዲደረግ እና የክልሉን እና የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ መልኩ ውሳኔው እንዲከለስ ፣ የልዩ ኃይሉ ቀጣይ እጣ ፈንታ ከአማራ ሕዝብ፣ ከክልሉ ልዩ ኃይል አመራሮች እና ከመላው የሠራዊቱ አባላት ጋር በሚደረግ ውይይት እና የጋራ መግባባት ብቻ ውሳኔ ላይ እንዲደረስበት ማሳሳባችን ይታወቃል፡፡

ይሁንና የፌዴራሉ መንግስት ከሕግ አግባብ ውጭ የገዥው ፓርቲን ውሳኔ ለማስፈጸም የገፋበት በመሆኑ ፣ በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ ሕዝባዊ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ ድርጅታችን አብን እስካሁን ድረስ ለሀገራዊ አንድነት እና ሰላም ሲባል ጉዳዩን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሲከታተል ቆይቷል። ይሁንና መንግስት ችግሩን በሰከነ መንገድ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ከዕለት ወደ ዕለት የለየለት የኃይል ፣ የአፈና እና የማደናገር አማራጭ እየገባ መሆኑን ፖርቲያችን ተረድቷል። መንግስት ችግሩን በሰከነ መንገድ ፣ በውይይት ፣ በጋራ መግባባት እና በመተማመን የመፍታት ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም በስህተት ላይ ሌላ ስህተት እየደረበ እና ችግሩን በአፈና እና በጉልበት ለመፍታት ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፖርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ከዛሬ ጀምሮ ለችግሩ ዘላቂ እልባት እስከሚሰጥ ድረስ መንግስት እና ግብረ-አበሮቹ በአማራ ልዩ ኃይል ፣ በፋኖ እና በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚነዟቸውን የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎች በይፋና በተከታታይ የሚያጋልጥ መሆኑን ለማሳወቅ ይወዳል።

See also  ልዩ ዜና - "ሁለት መቶ ለአንድ" አዲሱ "ሸኔ" በአማራ ክልል

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ፋኖ የሀገር እና የሕዝብ የሰላም ዘብና ዋስትና እንጂ የፀጥታ ስጋት ምንጭ ሆነው አያውቁም። ሀገር የማዳን ተልዕኮዎችን በከፍተኛ ብቃት የፈጸሙ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አስተማማኝ ጋሻ እና ደጀን ሆነውና ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለው ሀገር የመታደግ ጉልኅ ታሪክ የሰሩ የሀገር መከታዎች ናቸው፡፡ ለዚህ መላው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራሮችና አባላት ህያው ምስክሮች ናቸው። መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንም በክብር የሚያወሱት ወገናዊ የታሪክ ሃቅ ነው። ይሁንና የፌዴራሉ መንግስት ለልዩ ኃይሉ ክብር እና ውለታ በማይመጥን እና ፍጹም ክብረ-ነክ በሆነ ሁኔታ የልዩ ኃይሉን አመራር ከሠራዊቱ በመነጠል እና ስንቅ ፣ ሎጂስቲክ እና ደሞዝ በመከልከል ጭምር ልዩ ኃይሉን ለመበተን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህም የክልሉ መንግስት የሚቆጣጠረውን እና የሚመራውን ኃይል በመበተን ፣ በእዝ የማይመራ እና መንግስት የማይቆጣጠረውን ኃይል ለመፍጠር እና ክልሉን ወደ ቀውስ እና ትርምስ ለመውሰድ የሚደረግ ጥረት ሆኖ የሚቆጠር ነው፡፡

የአማራ ሕዝብ ከመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበርና ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል የትሕነግ-ኢሕአዴግን አገዛዝ ከስልጣን አስወግዶ ያመጣውን ለውጥ ለሀገራዊ አንድነት ፣ ነፃነት ፣ ፍትኅ እና ለዴሞክራሲ ገቢራዊ ቀናኢነት በሌላቸው የፖለቲካ እጆች ተነጥቋል። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ወደማያባራ የነውጥ እና የግጭት፣ የአፈና እና የዘር ፍጂት ምዕራፍ እየተሸጋገሩ ይገኛሉ። መንግስት ዝቅተኛ የሆነውን ለሕይወት እና ንብረት ከለላ የመስጠት ግዴታውን ለመወጣት አቅም ወይም ፍላጎት እንደሌለው ከበቂ በላይ ማሳያዎች ተከስተዋል። በተለይም የአማራ ሕዝብ ከየትኛውም ዘመን በላይ ሰላሙን ፣ ሕይወቱን፣ ማንነቱን እና ንብረቱን በገፍና በይፋ እየተነጠቀ ያለበት ወቅት ነው። ሕዝባችን ይሄን ዘግናኝ ግፍ እና መስዋእትነት ተሸክሞ የቀጠለው ምናልባት ወደፊት እውነተኛ ፍትኅ ፣ እኩልነት እና ዴሞክራሲ የሰፈነበት ሥርአት ይፈጠራል የሚል ተስፋ ሰንቆ ነበር።

ድርጅታችን አብን መዋቅራዊ እና ሕገ-መንግስታዊ ሽግግር እንዲደረግ እና በሥራ ላይ ያለው ሃሳዊ የፌዴራል አወቃቀር በእውነተኛ ፌዴራላዊ የአስተዳደር ሥርአት እንዲተካ እና የሀገራችን አንድነት እና ሉአላዊነት ፣ የዜጎች እና የሕዝብ መብትና ነፃነት እንዲከበር ለማስቻል የበኩሉን ኃላፊነት ለመወጣት ያለመታከት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ነገር ግን ይህ ተስፋና ግምት በየቅጣጫው እና በየደረጃው ተሸርሽሮ በአሁኑ ሰዓት የመጨረሻው ዝቅታ (rock bottom) ላይ የደረሰ መሆኑ አይካድም።

See also  በወልቃይት መከላከያን በመጎንተል ለቆ እንዲወጣ፣ የአጻፋ ምላሽ እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑ ተሰማ፤

ሀገራዊ በጎ ቱርፋት ያጎናፅፋል የተባለለት “የለውጥ ምዕራፍ” ሰቆቃና ስጋት የነገሰበት ሆኗል። የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጥላቻ አዙሪት በማስወጣት በነፃነትና በእኩልነት ለማስተዳደር በአደባባይ ቃል ገብተው የነበሩ “የለውጥ አመራሮችም” የዘር አንጓዎችን ተከትለው ከነጎዱ ሰንብተዋል። የአማራ ሕዝብም ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) እያለ የሚጠራው ቡድን በከፈተበት መጠነ ሰፊ ባለ ሶስት ዙር የወረራ ጦርነት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ደርሶበታል። በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት እና የዘር ማፅዳት ወንጀሎች ተፈፅመውበታል ፤ አሁንም ቢሆን በከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ውስጥ ይገኛል። እነዚህ መጠነ-ሰፊ እና ተደጋጋሚ የሆኑ የዘር ጥቃቶች በዋናነት የሚፈፀሙት በሽብር ኃይሎች ቢሆንም በመንግስታዊው መዋቅር እና ባለስልጣናት ቸልተኝነት ፣ ይሁንታ ፣ ፈቃድ እና እገዛ ጭምር እንደሚፈፀሙ በግልፅ ይታወቃል።

በሌላ በኩልና በዋናነት የአማራ ሕዝብ ወደ ሀገሩ መዲና አዲስ አበባ በነፃነት መግባትና መውጣት የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በአጠቃላይ በአዲስ አበባና አጎራባች አካባቢዎች፣ በተለይም ሸገር ከተማ ተብሎ በተዋቀረው አካባቢ በሚኖረው ሕዝብ ላይ የመንግስት አካላት በማንነት እየለዩ መኖሪያ ቤቶችን በማፍረስና ንብረቶችን በመዝረፍ በርካታ ቤተሰቦችን ሜዳ ላይ እየበተኑት ይገኛል። ሕዝባችን ሀገር አልባና መንግስት አልባ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የአማራ ሕዝብ በዋናነት በትሕነግ እና በኦነግ-ሸኔ ከተከፈቱበት የጥፋት ዘመቻዎች በተጨማሪ በትሕነግ የተሰማራውና ድጋፍ በሚደረግልላቸው የውስጥ ሽብርተኞች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። በአሁኑ ወቅት የአማራ ሕዝብ ከላይ በተጠቀሱት የሽብር ኃይሎች በኩል የሚፈፀሙበት ጥቃቶች የቀጠሉ ሲሆን ወደፊትም ተጨባጭ ስጋቱ እንደሚቀጥል መገመት አያዳግትም። የአማራ ሕዝብ በጦርነቱ ምክንያት ከደረሰበት ጉዳት ገና አላገገመም። ለኅልውና ዘመቻ በነፍስወከፍ ሀገራዊ ጥሪ የተደረገለት ሕዝብ ድህረ ጦርነት ይህ ነው የሚባል የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ አልተደረገለትም። የአማራን ሕዝብ መልሶ ማቋቋም የችሮታ እና የግብረሰናይ ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል።

ስለሆነም ከላይ በዝርዝር የገለፅናቸውን ተጨባጭ የሆኑ ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ፖርቲያችን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ የአማራ ልዩ ኃይልን ለማፍረስ እና ትጥቅ ለማስፈታት ያሳለፈው ውሳኔ እና የሚያደርገው እንቅስቃሴ ኃላፊነት የጎደለውና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ድጋሜ ማሳወቅ ይፈልጋል። ቀደም ሲል በዝርዝር እንደገለፅነው የብልፅግና ፖርቲ ሥራ አስፈፃሚ የአማራ ልዩ ኃይልን ለማፍረስና ትጥቅ ለማስፈታት ያሳለፈው ውሳኔ መሬት ላይ ያለውን ሃቅ ያላገናዘበ ፣ መርኅ አልባ ፣ አድሏዊ እና አምባገነናዊ ነው፡፡ ውሳኔውና የአፈፃፀም ሂደቱ በሕግ አግባብ የተመራ ፣ መርኅ ተኮር እንደሆነ ፣ ውይይት እንደተደረገበት እና መግባባት የተደረሰበት እንደሆነ ለማስመሰል የሚቀርቡ አስተያየቶች በአጠቃላይ ሃሰት ናቸው።

1. የአማራ ልዩ ኃይል አመራሮች፣ አባላት እና በአጠቃላይ የአማራ ሕዝብ አልተወያየም፣ ፍፁም የሚያውቀው ነገር አልነበረም።

2. በየአካባቢው ተመድበው ስምሪት ላይ የነበሩ የአማራ ልዩ ኃይል አደረጃጀቶችና አባላት ስለጉዳዩ ምንም አይነት መረጃ አልነበራቸውም። በስምሪት እና በካምፖች ውስጥ ባሉበት ወቅት እንደጠላት ተቆጥረው በኃይል እና በከበባ ትጥቃቸውን የመቀማትና የመበተን ሙከራ ተደርጓል። ሰሞኑን በአማራ ልዩ ኃይል ላይ የተፈፀመው ድርጊት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ትሕነግ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ ላይ ከፈፀመው ከበባና ጥቃት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ክብረ ነክ አዋራጅ ድርጊት ነው።

See also  "የአሜሪካ በኢትዮጵያ ተላላኪ መንግሥት የመመስረት ፍላጎት ከሽፏል"አንዳርጋቸው ጽጌ

3. የአማራን ሕዝብ ተወቃሽ የማድረጉ ጥረት በየመድረኩ ቀጥሏል። በሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት ፊት ሳየቀር ለትሕነግ ጠበቃ ሆነው የአማራን ህዝብ ለመዝለፍ የሚዳዳቸው የመንግስት ባለስልጣናትን ተመልክተናል።

4. ሌሎች ክልሎች ነባራዊ የሰላም ሁኔታቸውን ታሳቢ እያደረጉ መወሰን ይችላሉ። ሆኖም የአማራ ልዩ ኃይል አሁን ትጥቁን የማይፈታባቸው የራሱ በቂ ምክንያቶች እንዳሉት ከላይ በዝርዝር አስረድተናል። ከአውድ ውጭ ለማነፃፀር መሞከር በራሱ ሚዛን አልባነት ነው።

5. ከላይ የተገለፀው እንደተጠበቀ ሆኖ የትሕነግ ኃይል በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት ትጥቁን አልፈታም፤ እንዲያውም ተጨማሪ ኃይል እየመለመለ እና እያሰለጠነ፣ እያስታጠቀ እና የውጊያ ልምምዶችን እያደረገ አዲስ የጦርነት ዝግጅት ላይ መሆኑን መንግስት ጠንቅቆ ያውቃል። ዝግጅቱ የሚደረገው በትግራይ ውስጥ እና ከትግራይ ውጭ በጎረቤት አገር ሱዳን ጭምር ነው። ስለሆነም በመንግስት በኩል ከዚህ በተቃራኒ ትሕነግ ትጥቅ እንደፈታና በአካባቢው የሰላም ድባብ እንደሰፈነ የሚወራው ሀሰት ነው።

6. በፌዴራል መንግስቱ ይሁንታ የተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግስቱ የራያና የወልቃይት የአማራ አካባቢዎችን ክረምት ሳይገባ እንደሚያስረክባቸው በትግርኛ ቋንቋ በሰጡት ቃለ መጠይቅ በይፋ ገልፀዋል። በርካታ የትግራይ ፖለቲከኞች አጋጣሚውን በመጠቀም ድጋሜ ወረራ ለመክፈት የሚታወቅ ውይይትና ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። በመጨረሻ ይህ ጉዳይ ከፍተኛ አለመረጋጋት የሚፈጥር እና ሌላ የቀውስ አዙሪት ውስጥ የሚያስገባን አደገኛ አካሄድ በመሆኑ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ለገዥው የብልፅግና ፓርቲ ፣ ለፌዴራሉ መንግስት ፣ ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንዲሁም ለሁሉም የክልል መስተዳደሮች በጥብቅ ለማሳሳብ ይወዳል፡፡

በመሆኑም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የሚከተሉትን ጥሪዎች ያስተላልፋል:-

ሀ. የፌዴራሉ መንግስት ውሳኔውን እንደሰረዘ በአደባባይ እንዲገልጽ እና የአማራ ልዩ ኃይል አባላት እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ካምፓቻቸው እና ወደ ግዳጅ ቦታቸው እንዲመለሱ በይፋ ጥሪ እንዲያደርግ፤

ለ. በፌዴራል መንግስቱ ውሳኔ እና ትዕዛዝ ከሥራ ውጭ የሆኑት የአማራ ልዩ ኃይል የብርጌድ እና የክፍለ ጦር አዛዞዦች ወደምድብ ቦታቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ፤

ሐ. የአማራ ክልል መንግስት ለልዩ ኃይሉ አስፈላጊ የሆኑ ስንቅ እና ሎጂስቲክ እንዲያቀርብ እና ደሞዝ እንዲከፍል፤

መ. በካምፕ እና በግዳጅ ቦታችሁ ላይ የምትገኙ ውድ የአማራ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አመራሮች እና አባላት ሠራዊቱ እንዲበተን የሚደረጉ ጥረቶችን እና የፕሮፖጋንዳ ጥቃቶችን በመቋቋም በተለመደው ሥነ-ምግባር ፣ ዲስፕሊን እና ጨዋነት ከህዝባችሁ ጎን እንድትቆሙ፤

ሠ. የአማራ ሕዝብ በያካባቢው ላሉት የልዩ ኃይል አባላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል።

አብን ጉዳዩን በቅርበት እና በንቃት እየተከታተለው መሆኑን እና በቀጣይም ሁኔታዎችን እየገመገመ ተከታታይ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ መሆኑን እየገለጸ መላው የአማራ ሕዝብ እና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከሀገር ወዳዱ የአማራ ልዩ ኃይል ጎን እንድትቆሙ የከበረ ጥሪውን ያቀርብላችኋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ

ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም

Leave a Reply