Site icon ETHIO12.COM

በኛ በወታደሮች መዝገበ ቃላት እርም … ማለት …

እርም ማለት ለክብሯ ያለፉትን አደራ መርሣት ነው። ድክመትና ውርደት ማለት በዘመን አመጣሽ ችግር መረታት ጠብመንጃ በታጠቀ ጠላት ብቻ ሳይሆን ወሬ በሰነቀ ጠላት መሸነፍ በዘር ማንዘራችን የማይታወቀውን እጅ መስጠት ነው።

ፍቅር ማለት ያለጥቅም ፣ ያለስኬት ያለምቾትና ድሎት ከልብ መውደድ የሷን መሻት ለመሙላት ከራስ እንዲጎድል መፍቀድ ነው።መውጣት መውረድ ድካምን ብቻ ሳይሆን ሞትንም በፀጋ ለመቀበል የሚያስችል ተነሳሳሽነት ፅናት እና ጀግንነትን መላበስ ነው።

ጓደኝነት ማለት በደምና ሥጋ በዘርና ቋንቋ በባህልና እምነት ሳይሆን በዓላማ አንድ መሆን ነው። በፈታኝ ሰዓት አንተ ትረፍ እኔ ልለፍ የማለት ድፍረት ነው።

ወገን ስንል ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚኖር፣ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ሠንደቅና ዓርማው አድርጎ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር የሚኖር ህዝብ ማለታችን ነው። ያለልዩነት ማገልገል ከፊት ሆኖ ከየትኛውም አደጋ መከላከል ደግሞ ወደንና ፈቅደን የያዝነው እምነት ነው።

እርካታ አንደየ ሰው ግንዛቤና ፍላጎት ሊለያይ ይችላል። በእኛ ትርጉም አሰጣጥ እርካታ ማለት የሚሊዮኖች በሠላም ወጥቶ መግባት፣ ሠርቶ መብላት፣በሀገራቸው ውስጥ በፈለጉበት ቦታ ሃብት ማፍራት፣ ዘርቶ መቃም፣ ወልዶ መሣም ነው። የዜጋ ሳቅ የሀገር ፈገግታ ነው። የአባይ አይነት የትውልድ ሐውልት በብዛት መገንባት፣ የፍላጎቱ መሣካት የተትረፈረፈ እራትና መብራት እንዲኖር የራስን ድንጋይ መወርወር ነው።

ብርታት ማለት ለኛ ለተቀበሉት አደራ ብቁ ሆኖ መገኘት ቀንና ለሊት መዘጋጀት ፣የበዛ ልፋት፣ የሚቆጠር ስኬት ነው። ሁሉንም ተግዳሮት እንደ አመጣጡ መቀበል መታገል የማይጠፋ ዘመን የሚሻገር ለውጥ ማቀጣጠል ነው።

አንድነት ማለት ለአንድ የጋራ ዓላማ አንድ ዓይነት እምነት መያዝ፣ በወል ጎዳና መጓዝ፣ ካሰቡበበት መድረስ በሚጠበቅብን ልክ መኖር ለጠላት በተግባር መርዶ መንገር ህልምና ፍላጎቱን መቅበር ለወገን ድልን ማብሰር ነው።

የኛነት መገለጫ የተምሳሌትነታችን ማረጋገጫ ወደ ከፍታ መውጫ ፣ የማይጠፋ ማንነት፣ የማይከስም ውበት፣ የማይቀየር እውነት፣ የማይዛነፍ ልኬት ነው ። ብዙዎች ያልታደሉት፣ አጥብቀው የሚመኙትና የሚቀኑበት ሃብት ነው ኢትዮጵያዊነት፡፡

ኢትዮጵያዊነት ፈተና የማይጥለው፣ ብርታት ችግር ቢያንገዳግደው እንጂ የማያንበረክከው ፅናት ፣ ተንኮል የማያጓድለው ሙላት፣ ጠላት ወግቶ ቢያቆስለው እንጂ ፍፁም የማይገድለው ህያውነት ነው። ፈጥኖ ማጋገም በብርታት መቅደም ነው።

ጨለማን ተሻግሮ በብርሃን መጥለቅላቅ ፣የማውደቅን ሟርት አልፎ መተለቅ ፣ከምንጭ ይልቅ የጠራ፣ ከፀሐይ በላይ የበራ(የሚያበራ)፣ የበቀለ ያሸተ ያፈራ የጎመራ ተክል ነው። ክብር የወለደው ፣ፍቅር የገመደው ህብር ያከበረው መስዋዕትነት ያኖረው ያናረው ያሻገረው ፅላት ነው።

በሃብት የማይታመን ፣በቁስ የማይመዘን ፣በደም ፍሰት፣ በአጥት ክስካሽ፣ በሥጋ ጎማጅ ነፃነትን ያዋጀ፣ ግፍ በደል ኢፍትሃዊነትን ድል ነስቶ እኩልነትን የዋጀ፣ የበላይና የበታች አስተሳሰብን ያፈረሰ የተናቀውን ጭቁን ያነገሰ ጀግንነት ነው። ኢትዮጵያዊነት በአድዋ የተለኮሰ በካራማራ ያበራ የደም ሸማ ነው።

ምንዱባንን ከእንቅልፍ ቀስቃሽ፣ የተበደሉትን እንባ አባሽ፣ አይቻሉም የተባሉትን ጎልያዶች ደምሳሽ፣ የሐቅ ውቅያኖስ ፣የእምነት ተራራ የፅናት ጎተራ፣ የሆነ የከፍታ አብነትና የግዝፈት ልኬት ነው። ቢናገሩት የማያሳፍር ቁምነገ፤ ቢለብሱት የሚያስከብር፣ በሸንጎ የሚያነግስ በአደባባይ የሚለበስ ውድ ካባ ነው።

ቅዱስ ዓላማ ነው። ብዙሃን ዓርማቸው የሚያደርጉት ሠንደቅ ዓላማ ፣የተለየ ቀለም፣ ሚመስጥ ትርጉም ፣የረቀቀ ቅኔ ፣የመጠቀ ዜማ ፣የከፍታ ማማ ፣የክብር ሠገነት ፣ ከሩቅም ሆነ ከቅርብ የሚታይ ሐውልት የሚሰማ ገድል ነው ። ብዙ ውበት እልፍ እውነት የተለየ ድምቀት ነው። ኢትዮጵያዊነት

በውስብስብ ፈተና ያለመንበርከክ በድካም ያለመበገር፣ በፀጋ ያለማፈር፣ በድል ያለመፈከር ፣ከሃያላን ጋር መዋደቅ ለአሸነፉት ምርኮኛ ማዘንና በሰብአዊነት መዘመን ለጨነቀው መጨነቅ ፣ ሞገስ የሚያላብስ አንድ ቦታ የማይቆም ለትውልድ የሚወረስ የታረቀ ዲሲኘሊን የታረመ ስነምግበር ነው። ኢትዮጵያዊነት።

በሚገባው ልክ እንክብካቤ፣ ወደ ተዋበ መስክ የሚያሻግር ግንዛቤ፣ የወል የሆነ ለወል የሚጠቅም አማራጭ እሳቤ፣ የሚያስፈልገው በእጅ ያለ ወርቅ ነው። መርጦ አድማጭ ጆሮ የኢትዮጵያን ልክ ሚመጥን ተፈጥሮ የሚጠይቅ ውድ ነገር ነው።

በቀን ሃያ አራት ሠዓታት፣ በሣምንት ሰባትና በወር 30 ቀናት፣ በዓመት 12 ወራት፣ ክረምትና በጋ ቀንና ለሊት ጠላት የማይተኛለት፣ ፍላፃ የሚለቅበት ጦር የሚወረውርበት፣ በመሣሪያ ብቻ ሳይሆን በወሬ የሚወጋት፣ በውሸት ያለውን አቅም ሁሉ ተጠቅሞ በአሉባልታ የሚያናገው መሆን የሌለበት ዓለት ብዙ ጠላት ያለው ብዙም አንድም የሆነ ማንነት ነው። ኢትዮጵያዊነት!

ለቀላልም ሆነ ከባድ በሽታዎች መፍትሔው ወይም ፈዋሽ መድሐኒቱ አንድ የሆነ ጤንነት ነው። በአንድነት የሚታከም በአብሮነት የሚፈወስ ጤና በህብረት የሚተከልና የሚያድግ ችግኝ ነው።

ጠላትን ለይቶ ያለማወቅ ቸለልተኝነት የሚያጠቃን ፣ግን ደግሞ በሁሉም ዘርፎች የከበረው አጥር እንዳይደፈር፣ የከረመው ፍቅር እንዳይሸረሸር፣ አስቀድሞ መጠንቀቅ፣ መታጠቅ መፋለምና ድል ማድረግ በልዩነት ውስጥ ያለን ውበት ሲወርድ ሲወራረድ የመጣን ታላቅ እውነትና እምነት መጠበቅ ግድ የሚለን ህዝቦች ባለታሪክ ባለ ሠንደቅ የጥቁር ፈርጦች ነን።

ሺህ ሚሊዮን ምክንያት ቢደረደር ፣ብዙ የሚያም ችግርና እንቅፋት ቢኖር ከአንድነትና ህብረት ውጭ አማራጭ የሌለን ውስጣዊና ውጫዊ የቅርብና የሩቅ የሚፈትነን ግን ደግሞ የማይጥለን ጥቁር አልማዞች። ለኢትዮጵያውያን “ድር ቢያብር አንበሳ ያሥር፤ ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሐኒቱ፣ አንድነት ሐይል ነው” ከተባለው ከሚባለው በላይ ህብረት፣ መደማመጥ፣ መነጋገር መመካከር፣ በወል ማቀድ በጋራ መሻገር ግድ የሚለን።

“የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ” ከተባለው በላይ ስክነት ከስሜት ይልቅ ምክንያታዊነት ስክነት ስክነት አሁንም ስክነት የሚያስፈልገን የነፃነት አርበኞች ነን ።

ኢትዮጵያዊነት አደራ አለመብላት፣ ውለታ አለመርሳት፣ ታማኝነት፣ ከእኔ በላይ ሀገሬንና ህዝቤን ማለት፣ ከግለኝነት ስግብግብነት እና ሌብነት መራቅና ለዓላማ መኖር ለነፃነት መሞት የከታቢው እምነት ነው።

ኢትዮጵያዊት በተሰለፉበት ዘርፍ ሁሉ መብቃት መትጋት በተግባር ደግሞ ወታደር መሆን እራስን አሳልፎ መስጠት በሀገር ከፍታ በህዝብ እርካታ ውስጥ ስኬትን መመልከት ነው።

ፈይሳ ናኔቻ የኢፌዴሪ መከላከያ መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም

Exit mobile version