Site icon ETHIO12.COM

የዓባይ ግድብ – ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ተቋቁሞ ማሳካትን የሚያሳይ ትልቅ ድል

የዓባይ ግድብ ባለፉት ዓመታት የነበሩ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ተቋቁሞ አሁን የደረሰበት ደረጃ ኢትዮጵያ ፍላጎቷን ማሳካቷን የሚያሳይ ትልቅ ድል መሆኑን የግድቡ ተደራዳሪና ዓለም አቀፍ የሕግ ምሁሩ አምባሳደር ኢብራሂም እንድሪስ ገለጹ፡፡

አምባሳደር ኢብራሂም እንድሪስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ባለፉት 12 ዓመታት እንደ አገር ከባድ ጫናዎችንና የድርድር ሁኔታዎችን አሳልፈናል፡፡ የነበሩ ውጣ ውረዶችን አልፎ ግድቡ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱ ኢትዮጵያ ፍላጎቷን ማሳካቷን የሚያሳይ ትልቅ ድል ነው፡፡

ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ከሕዝቡ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት የእውቀት፣ የገንዘብና የሃሳብ ድምር ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበረ የጠቆሙት አምባሳደር ኢብራሂም፤ ይህም እንደ አገር የትኛውንም ፕሮጀክት ጀምሮ ለመጨረስ የሚያስችል ትልቅ አቅም እንዳለን ያሳየንበት ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ አባቶቻችን ባቆዩልን አገርና ቅርስ እንደምንኮራው ሁሉ እኛ ለልጆቻችን የምናወርሰውና ልጆቻችን የሚኮሩበት ትልቅ ሀብት ነው ብለዋል፡፡

የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት በተለይም ግብጽ የዓባይን ውሃ መጠቀም መብታችን እንደሆነ ሊገነዘቡት ይገባል ያሉት አምባሳደር ኢብራሂም፤ ምክንያቱም ውሃው የጋራ ውሃ ስለሆነ እንዳንጠቀም ሊከለክሉ የሚችሉበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የላቸውም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ግብጽ ኢትዮጵያ የድርሻዋን ውሃ እንዳትጠቀም የምትከልክልበት ዓለም አቀፋዊ ሕግ እንደሌለ ዓለም ያውቃል ያሉት ተደራዳሪው፤ ሆኖም አንዳንድ ምዕራባውያን ፍላጎታቸው ተገደን ስምምነት ውስጥ እንድንገባና የእነሱ እስረኛ ሆነን እንድንኖር ማድረግ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡ በአንድ በኩል የልማታችን ደጋፊ መሆናቸውን እየተናገሩ በሌላ በኩል ደግሞ የድርሻችንን ውሃ እንዳንጠቀም የሚያደርጉት ጫና ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1959 ግብጽና ሱዳን የዓባይን ውሃ ሙሉ በሙሉ መካፈላቸውን አስታውሰው፤ በዛን ወቅት 84 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንዳለ ታሳቢ ተደርጎ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለግብጽ፣ 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ደግሞ ለሱዳን የተሰጠ ሲሆን ቀሪውን 10 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትሩን ውሃ ደግሞ ለትነት ብለው አስቀምጠውታል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ስለዚህ ከድርሻችን ምንም ዓይነት ውሃ እንድትነኩብን አንፈቅድም ካሉ በተዘዋዋሪ የ1959ኙን ስምምነት ተቀበሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ የምታበረክተው 85 በመቶ የዓባይ ውሃ የግብጽ እንጂ የኢትዮጵያ አይደለም ማለት ስለሆነ እየታገልን ያለነው ይህንን ኢ-ፍትሃዊነት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥያቄ ውሃውን በጋራ አልምተን በፍትሐዊነት እንጠቀም የሚል ስለሆነ በዓለም አቀፍ ሕጎችም ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የለብንም ያሉት ምሁሩ፤ የግብጾች አንዱ ስጋት ኢትዮጵያ ውሃ መጠቀም ስትጀምር ሌሎችም የተፋሰሱ አገሮች መጠቀም ይጀምሩና ውሃው ላይ ያለን ቁጥጥር ይቀንሳል የሚል ነው፡፡ በግብጽ በኩል እየተስተጋባ ያለው የራስ ወዳድነት አካሄድ ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ መታሰብ ያለበት ውሃውን ከተፋሰሱ አገራት ጋር እንዴት በጋራ አልምተን እንጠቀም የሚል መሆን እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

እንደ አምባሳደር ኢብራሂም ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ያላት ዋንኛ ሀብት መሬት፣ ውሃና የሰው ኃይል ነው፡፡ የዓባይ ግድብም ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት የመጠቀም መብት እንዳላት ያረጋገጠችበት ነው፡፡ በመሆኑም ሁላችንም ግድቡን መጠበቅ፣ መንከባበብና ግንባታው ሙሉ በሙሉ እስከሚጠናቀቅ ድጋፋችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ – አዲስ ዘመን

Exit mobile version