Site icon ETHIO12.COM

ዳኞች ጥቁር ጋወን/ካባ ለምን ይለብሳሉ?

የአለባበስ ኮድ/ደንብ (Dressing Code) የመተማመን ምልክት፣ የዲሲፕሊን ምልክት እና የሙያ ምልክት ሲሆን ለባለሙያ የግለሰብ ስብዕና ክብሩ አካል ነው። የፍርድ ቤት ክብር በመጠበቅ እና የግለሰብ አኗኗር ነፃነትን በመፍቀድ መካከል ያለው ሚዛን የጠበቀ አለባበስ በደንብ ይገለጻል፡፡ የባለሙያ አካባቢ ወይም የስራ ቦታ በአጠቃላይ የአለባበስ ደንብ ለምሳሌ በቀለም፣ በስታይል እና በሌሎችም ምልክት ሊደረግበት ይችላል። የአለባበስ ደንብ የሞያ ክብር መገለጫ አካል ነው፡፡

የዳኞች እና ተሟጋቾች ( ጠበቆች፣ ዐቃቤያን ህግ እና ተከላካይ ጠበቆች) የዳኝነት ልብስ የለበሱት ልብስ ለፍርድ ቤት እና ለፍትህ ያለው ክብር እና ታማኝነት ምልክት ያሳያል።

ጥቁር ቀለም በብዙ የአለማችን ክፍል የህግ ሞያ የደንብ ልብስ በመሆን የሚያገለግል ሲሆን ጥንካሬን እና ስልጣንን የሚያመለክት ስለመሆኑ ይነገራል።

ቀደም ባለ ጊዜ ጥቁር ቀለም የተመረጠው በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ የተለያዩ ፅሁፎች ያመለክታሉ፡፡ የመጀመሪያው በዚያን ጊዜ ቀለሞች እና ማቅለሚያዎች በቀላሉ ሊገኙ ያለመቻላቸው ሲሆን ነገር ግን ‘ጥቁር ካባ’ ለመልበስ ዋናው ምክንያት ጥቁር የሀይል እና የስልጣን ቀለም ስለሆነ ነው፡፡ ጥቁር ራስን መግዛትን ስለሚወክል የህግ ባለሞያዎች ዳኞችንም ጨምሮ ለፍትህ መገዛታቸውን ለማሳየት ጥቁር ይለብሳሉ። ጥቁር ቀለም የክብር፣ የጥበብ እና የፍትህ ምልክት ስለሆነ ሁሉም የህግ ባለሞያዎች እና ዳኞች ሊከተሏቸው የሚገቡ እሴቶች እንደሆነ እና ‘ጥቁር ልብስ’ የስልጣንን፣ የእውቀትን፣ የጥንቃቄ እና የፅናት መልእክትን ያስተላልፋል ተብሎ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ‘ጥቁር ካባ’ መልበስ በህግ ባለሞያዎች መካከል የዲሲፕሊን ስሜት በመፍጠር የመብትና የፍትህ ተቆርቋሪ የመሆን ስሜትን ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል፡፡ በሌላ በኩል ጥቁር ቀለም ብርሀን የማያሳልፍ ወደ ውስጥ የማያሳይ ሲሆን ባለጉዳዮች የዳኞችን ማንነት አይተው እከሌ እንዳይሉ በወጥነት ዳኞች ተመሳሳይ ልብስ መልበሳቸው በገለልተኝነት ጉዳዮችን እንደሚያዩ ማሳያ ምልክት ነው፡፡ በሌሎች ሀገሮች ዳኞች በተጨማሪነት ዊግ ፀጉር የሚለብሱ ሲሆን ይህም በተመሳሳይ ማንነታቸው እንዳይታይ የዳኛ ምልክትነትን ብቻ ለመያዝ እና ጉዳዮችን እንደሚያዩና እንደሚወስኑ በምልክትነት ስለሚያሳይ ነው፡፡ በአንፃሩ ሀኪሞች ነጭ ልብስን በብርሁነት፣ በተስፋ እና ንፅህና በማሳያነት ይለብሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ዳኞች እና የህግ ባለሞያዎች ጥቁር ካባ ወይም ጋዎን ለምን እንደሚለብሱ በህጉ ላይ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም የዳኞች እና የህግ ባለሞያዎች የአለባበስ ስነ-ስርዓት በየፌደራል ፍርድ ቤቶች የችሎት ስርዓት መመሪያ ቁጥር 13/2014 አንቀፅ 13 ስር ሰፍሮ ይገኛል። ይኸውም ፡-

 ማንኛውም ዳኛ ችሎት ሲያስችል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ በጥቁር ካባ መደብ ላይ ከአንገት እስከ እግር ጫፍ የሚደርስ ሰማያዊ ቀለም ያለው ካባ እና አንገት ላይ የሚታሰር ነጭ ሻሻ/ከረባት፣ ከአንገት የሚጀምር ወርቃማ መነሳነስ እንዲሁም በሁሉም የካባው እጀታ ላይ ሶስት ሰማያዊ መስመሮች ያሉት፣
 የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ጥቁር ካባ መደብ ላይ ከአንገት እስከ እግር ጫፍ የሚደርስ ሰማያዊ ቀለም ያለው ካባ እና ከአንገት የሚጀምር ሁለት ወርቃማ መነሳንስ እንዲሁም በካባው እጀታ ላይ ሁለት ሰማያዊ መስመር ያለው ፣
 የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ዳኛ በጥቅር ካባ መደብ ላይ ከአንገቱ እስከ እግር ሰማያዊ ቀለም ያለው ካባ እና ከአንገት የሚጀምር አንድ ወርቃማ መነሳነስ እንዲሁም በካባው እጀታ አንድ ሰማያዊ መስመር ያለው ካባ መልበስ አለባቸው። ይህ ከላይ የተጠቀሰው በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ወጣቶች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ የቤተሰብ፣ የሴቶችና የህፃናት ችሎት ላይ ህፃናት በሚቀርቡበት ጉዳዮች ላይ ዳኖች፣ ተከራካሪዎች፣ የህግ ባለሞያዎች እንዲሁም የችሎት አስከባሪዎች እንደ አስፈላገነቱ በችሎት ካባ ላያደርጉ ይችላሉ።

ዐቃቤያነ ሕግ እና ጠበቆችም በክርክር ወቅት ጥቁር ካባ ወይም ጋዋን የሚለብሱ ሲሆን ልዩነቱ ዐቃቤ ሕግ በሚለብሰው ጥቁር ካባ ላይ ከትከሻ ጀምሩ እስከ ግርጌው ጫፍ የቁልፍ መስመሩን ተከትሎ ወደ ታች የሚወርድ ቀይ መስመር አለው። ይህ ቀይ መስመር በሰዎች ላይ የደረሰን በደል እና ጉዳት የሚያመላክት ነው። በአንጻሩ የጠበቆች ካባ ሙሉ ጥቁር ሲሆን ደረቱ ላይ አነስተኛ ነጭ ከረባት አለበት።

1984 አካባቢ ተመስርቶ የነበረው ልዩ ዐቃቤ ሕግ እና በ1975 ዓ.ም ተቋቁሞ የነበረው ልዩ ፍርድ ቤት ዳኞች በተመሳሳይ ጥቁር እና ቀይ ቀለም ያለው ካባ ይለብሱ የነበረ ሲሆን በደረታቸው ላይ ቢጫ ሪቫን ያንጠለጥሉ ነበር

Federal ministry of justice

Exit mobile version