Site icon ETHIO12.COM

የክልል የሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊዎች ” ተጀምሯል”

ወጥ የሆነ አገራዊ የጸጥታና ደህንነት ኃይል እንዲኖር የሚያደርገውን ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ስራ –

ወጥ የሆነ አገራዊ የጸጥታና ደህንነት ኃይል እንዲኖር የሚያደርገውን ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ስራ መጀመራቸውን የክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊዎች ተናገሩ።

የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ስራ የአገርን ሰላምና ደህንነት የሚያስጠብቅ እንጂ ትጥቅ የማስፈታትና የመበተን ዓላማ እንደሌለውም ገልጸዋል።

የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት እየተከናወነ የሚገኘውን ስራ አስመልክቶ የፌደራልና የክልል የጸጥታ ዘርፍ የስራ ኃላፊዎች ውይይት አካሄደዋል።

በውይይቱም የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የክልል ሰላም፣ ደህንነትና የሚሊሻ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የሚሊሻና የልዩ ኃይል አዛዦች በተገኙበት ተካሂዷል።

የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት እየተከናወነ የሚገኘውን ስራ አስመልክቶም የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የሶማሌና የአፋር ክልል የሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊዎች ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የአገርን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ወጥ የሆነ ጸጥታ መዋቅር እንዲኖር ለማድረግ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት የሚያስችል ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።

ወጥ የሆነ አገራዊ የጸጥታና ደህንነት ኃይል እንዲኖር በማድረግ ልዩ ኃይሉን መልሶ ለማደራጀት በክልሎች መካከል መተማመን መደረሱንም ተናግረዋል።

ልዩ ኃይሎች የአገርን ሉዓላዊነትና የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ታሪክ የማይዘነጋው አኩሪ ድል መሆኑን አንስተዋል።

ልዩ ኃይሉን መልሶ ለማደራጀት እየተካሄደ የሚገኘው ስራም በጥናት ላይ የተመሰረተና የአገርን ዘላቂ ሰላም ማስቀጠል የሚያስችል ጸጥታ መዋቅር ለመፍጠር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሁሉም ዜጎች እምነት የሚያሳድሩበት የጸጥታ መዋቅር ለመገንባት የመልሶ ማደራጀት ተግባሩ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስታውቀዋል።

በሕገ-መንግስቱም ጠንካራ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ፌደራል ፖሊስና የክልል መደበኛ ፖሊስ እንዲኖር የተደነገገ መሆኑን አንስተው የልዩ ኃይል አደረጃጀት ግን ጥያቄ ሲያስነሳ መቆየቱን ተናግረዋል።

የመለዮ ለባሽ መብዛት አንዱ የሌላውን ኃላፊነት በመጋፋት ዜጎች በእኩል አገልግሎት እንዳያገኙ በማድረግ በጸጥታ ሥራው ላይ እንቅፋት ሲፈጥር መቆየቱን ገልጸዋል።

በክልል ልዩ ኃይሎች ላይ እየተደረገ ያለው የመልሶ ማደራጀት ስራም “ለተወለድኩበት ብሔር ነው የቆምኩት የሚለውን እሳቤ በማስተካከል” ኢትዮጵያውያን በእኩል የሚተማመኑበት የጸጥታ አካል ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ስራው መጠራጠርን በማስቀረት ዜጎች የሚተማመኑበትን ኃይል ለመገንባት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል አራርሳ መርዳሳ በበኩላቸው የልዩ ኃይል አባላት እንደ የፍላጎታቸው መከላከያ ሰራዊቱን፣ ፌዴራል ፖሊስን እንዲሁም በመደበኛ ፖሊስን እንዲቀላቀሉ መደረጉ ሕዝቡን የበለጠ ለማገልገል እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ውሳኔው ሰፊ ውይይት የተደረገበት መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የሶማሌ ክልል ጸጥታ ዘርፍ ቢሮ ኃላፊ ጦይብ አሕመድ ልዩ ኃይሉን መልሶ በማደራጀት ሕጋዊ መልክ የማስያዝ ስራው ጉልህ አገራዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አሊ ዲኒ፤ መልሶ የማደራጀት ስራው የልዩ ኃይሉን አባላት መብትና ጥቅም ባከበረ መንገድ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው የተናገሩት።

በተለያዩ አካላት “ልዩ ኃይሉ ሊበተን ነው፤ ሊፈርስ ነው፤ ትጥቅ ሊፈታ ነው” በሚል የሚነዛው አሉባልታም ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የመልሶ ማደራጀት ተግባሩም የልዩ ኃይል አባላት እንደ ፍላጎታቸው መከላከያ ሰራዊትን፣ ፌደራል ፖሊስን እንዲሁም መደበኛ ፖሊስን ተቀላቅለው የአገርን ሰላምና ደኅንነት የሚያስጠብቁበት እድል መመቻቸቱን ተናግረዋል።

በአደረጃጀቱ ፈቃደኛ ሳይሆን ወደ መደበኛ ሕይወቴ እመለሳለሁ የሚል የልዩ ኃይል አባል ካለም ድጋፍ ተደርጎለት ማኅበራዊ ህይወቱን እንዲቀጥል ይደረጋልም ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንዳሉት መልሶ የማደራጀት ስራው ለሕዝብ አገልግሎት መስዋዕትነት ሲከፍሉ የነበሩ የልዩ ኃይል አባላትን ለተጨማሪ ተልእኮ ከማዘጋጀት ያለፈ ዓላማ የለውም ነው ያሉት።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል አራርሳ መርዳሳ የልዩ ሀይል አባላት ለማደራጃት በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ውይይት አድርገን መግባባት ላይ ደርሰናል ወደ ስራ እየገባን ነው ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ጸጥታ ዘርፍ ቢሮ ኃላፊ ጦይብ አሕመድ በበኩላቸው እንዳሉት፤መልሶ የማደራጀት ስራው ትጥቅ የማስፈታት ዓላማ የለውም።

የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አሊ ዳኒ የልዩ ኃይል አባላት እንደ የፍላጎታቸው የጸጥታ ኃይሉን ተቀላቅለው በቅርቡ ሕብረተሰቡን ለማገልገል መልሶ ማደራጀት ስራው ሰፊ ዕድል ይፈጠራል ብለዋል።

የመልሶ ማደራጀት ስራውም ዜጎችን በእኩልነት ማገልገል የሚችል የጸጥታ ተቋም እንዲኖር ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሆኑን ኢትዮጵያዊያን ሊገነዘቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሕብረተሰቡም ለሚነዙ አሉባልታዎች ጆሮ ባለመስጠት የመልሶ ማደራጀት ተግባሩ ለበጠ አገራዊ ሰላምና ደህንነት ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን መረዳት እንዳለበት ገልጸዋል።

በመልሶ ማደራጀት ተግባሩም የልዩ ኃይል አባላት ስልጠና ወስደው በተዘጋጁ የጸጥታ አደረጃጀቶች መዋቅሮች እንደየፍላጎታቸው መግባት እንደሚችሉም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንደ የሙያቸው ስልጠና ይወስዳል፤ ከዚያም ፍላጎትን መሰረት በማድረግ በኋላ ወደ ተለያዩ የጸጥታ ዘርፍ መዋቅሮች ውስጥ ይገባሉ ብለዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል አራርሳ መርዳሳ ሕዝቡ ሰላም አግኝቶ ወደ ልማት ፊቱን እንዲያዞር በጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ በመሆኑ ሕዝቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የሶማሌ ክልል ጸጥታ ዘርፍ ቢሮ ኃላፊ ጦይብ አሕመድ ሕዝቡ የሚፈልገው ሰላም ነው፤ አሁን ላይ እየተደረገ ያለውን ይህንን ለማጽናት ነው።

የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አሊ ዳኒ ልዩ ኃይል ሕጋዊ መሰረት ስለሌለው ወደ ሕጋዊ ተቋም መልሰን ለማደራጀት ያለመ ነው ብለዋል።

የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ፣ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ስራ የአገርን ሰላምና ደህንነት የሚያስጠብቅ እንጂ ትጥቅ የማስፈታትና የመበተን ዓላማ እንደሌለው መግለጻቸው ይታወቃል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫም፤ ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ስራው ወጥ የሆነ ጠንካራ አገራዊ የጸጥታ ኃይል መገንባትን ዓላማው ያደረገ መሆኑን መግለጻቸውም እንዲሁ።

የልዩ ኃይል አባላቱ ሶስት አማራጮች አሏቸው፤ የመጀመሪያው ወደ መከላከያ ሰራዊት መቀላቀል፣ ሁለተኛው ደግሞ ባሉበት ክልል የፖሊስ ኃይል መግባት እንዲሁም ወደ መደበኛ ኑሮ መመለስ ነው ብለዋል።

(ኢዜአ)

Exit mobile version