Site icon ETHIO12.COM

የክልል ልዩ ሃይል መዋቅር ማክተሙ በይፋ ታወጀ – “የክልል ልዩ ሃይል የሚባል መዋቅር የለም”

“ከዛሬ ጀምሮ ” አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “ከዛሬ ለምሮ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት የሌለ መሆኑን አስታውቃለሁ። አሁን ኢትዮጵያ ሰላሟ አስተማማኝ የሚሆንበት እመርታ ላይ ናት”

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ እንዳሉት፣ የክልል ልዩ ሃይሎችን በፌዴራልና የክልል የጸጥታ ተቋማት መልሶ የማደራጀት ስራ የመከላከያ ጀነራሎች፣ ፌዴራል ፖሊስ እና የክልል የስራ ሃላፊዎች በተገኙ ተገምግሞ በቀረበ ሪፖርት መነሻ ነው ስራው መጠናቀቁ ይፋ የተደረገው። ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በቂ ዝግጅት የተደረገበት በመሆኑ ስራው በቅልጥፍና እንደሚከናወን ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የክልል ልዩ ሃይሎች እንደገና በመደራጀታቸው የኢትዮጵያን ሰላም የሚያረጋግጥ ህብረ ብሄራዊ ጠንካራ የጸጥታ ተቋም እንደሚገነባ አመልክተዋል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ሰሞኑንን ሱዳን መረራ ፈጸመች፣ የትህነግ ጦር ዲሽቃ ተኮሰ፣ ወደፊት ተጠጋ እየተባለ የሚረጨው ወሬ ቅጥፈት እንደሆነም እግረመንገዳቸውን አመልክተዋል። “የሱዳን ጦር አንድም እርምጃ ቀድሞ ከነበረበት አልተንቀሳቀሰም፣ የትግራይ ታጣቂም የተነቃነቀበት አግባብ የለም” ብለዋል።

የክልል ልዩ ኃይሎች አደረጃጀት ህጋዊ አለመሆን፣ በክልሎች መካከል እንደ ስጋት መተያየት እንዲሁም ችግሮችን በሃይል ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴ አደረጃጀቱን ለመቀየር አስገድዷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክልሎች መልሶ የማደራጀት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው “ከዛሬ ጀምሮ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀትና መዋቅር የለም” ብለዋል።

በመሆኑም የጸጥታ መዋቅሩ መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስና የክልል ፖሊስ ሲሆን በክልል ልዩ ኃይሎች ስም ተልዕኮም ሆነ ግዳጅ የሚቀበል ኃይል አይኖርም ሲሉ አረጋግጠዋል።

ከዚህ በኋላ በመረጡት አደረጃጀት መሰረት ሁሉንም ወደ ተመደቡበት የማጓጓዝና ወደ ስልጠና የማስገባት ስራ እንደሚከናወን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስታውቀዋል።

Exit mobile version