የአማራ ክልል ባለስልጣን በህገወጥ ታጣቂዎች ተገደሉ፤ ቀደም ሲል “የስብዕና ግድያ ተፈጽሞብህ ነበር”

“አስቀድሞ የስብዕና ግድያ ተፈጽሞባቸዋል” የተባሉት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ለጊዜው ባልታወቁ ታጣቂዎች ተገደሉ። አምስት ሰዎች አብረው ህይወታቸው አልፏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ የክልሉ መንግስት ቀድመው ሃዘናቸውን የገለጹ ሲሆን የአብን ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ “ወንድሜ ነፍስህ በሰላም ትረፍ! ከአካላዊ ሞትህ በፊት ሰፊ የስብዕና ግድያ ተፈጽሞብህ ነበር” ሲሉ ሃዘናቸውን በቁጥብ ቅላት ገልጸዋል። አቶ በለጠ ሚኒስትር ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በዚህ መልክ ሃዘናቸውን በመግለጻቸው ጽሁፉን በጻፉበት ማህበራዊ ገጻቸው ግርጌ ክፉኛ ተዘልፈዋል።

“በጣም ያሳዝናል እዛ ክልል እርስበርስ መገዳደል እንደ ጀግንነት ነው የሚያዩት። እስከ ዛሬ የአብይ አሽከር ተላላኪ ነው ይገደል ሲሉ ሲቀሰቅሱ እንዳልነበር ዛሬ ተገልብጠው አብይ ነው የገደለው ይላሉ” ሲሉም የግርምት አስተያየት የሰጡ ይገኙበታል።

አቶ ግርማ የሺ ጥላ በቅርቡ ከተፈጠረው አለምግባባት ጋር በተያያዘ ተለይተው ሲወነጀሉና በተከታታይ የስብዕና ማጉደፍ ሲካሄድባቸው እንደነበር በተለያዩ ተመጋጋቢ የዩቲዩብ ገጾችና ማህበራዊ አውዶች ምስክር ናቸው።

አቶ በለጠ “ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ” ሲሉም ጠይቀዋል። ክልሉ ባወጣው መግለጫ ድርጊቱን አውግዞ ከአሁን በሁዋላ ምህረት እንደማያደርግ አስታውቋል። በዚህ መሰሉ ግድያ የሚገኝ አንዳችም ትርፍ እንደሌለ አመልክቷል።

የጥፋት ኃይሎች ከዚህ በላይ ዓላማ ያላቸው እና ክልሉን የማፍረስ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ በኋላ የክልሉ መንግሥት እንደማይታገስ እና ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ እናረጋግጣለን፡፡

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ

በዛሬው ዕለት ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በተከበሩ አቶ ግርማ የሺጥላ፣ በግል ጥበቃዎቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው ላይ የመንግሥትና የድርጅት ሥራዎችን በአካባቢው ላይ ሠርተው ከመሃል ሜዳ ወደ ደብረ ብርሃን እየመጡ በነበረበት ሰዓት መንዝ ጓሳ ላይ በታጠቁ ኢ-መደበኛ ኃይሎች ጥቃት ተፈጽሟል፡፡

በዚህም አቶ ግርማ የሺጥላን ጨምሮ እስካሁን በደረሰን መረጃ የአምስት ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ በደረሰው ልብ ሰባሪ ጥቃት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰማውን መሪር ሐዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጻል፡፡

See also  «የኢትዮጵያ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለውጥ ባያገኝ ኖሮ ሀገሪቱ ወዳልተፈለገ ሁኔታ የምትሄድበት አጋጣሚ ይፈጠር ነበር» ዶክተር ነመራ ገበየሁ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር

እንዲህ አይነት አጥፊዎች እያደረሱት ያለው መረን የለቀቀ የሽብር ድርጊት ክልሉን እየመራ ያለውን መንግሥትና መላውን ሕዝብ የበለጠ ሊያጠናክር እንጂ በጥፋት ሃይሎች ሴራና ፍላጎት የሚሳካ ምንም አይነት ተልዕኮ የለም፡፡

ስለሆነም ይህንን የሽብር ሥራ እየሠሩ ያሉ እንዲህ አይነት ኃይሎች ላይ የክልሉ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል፡፡ የጥቃቱን አድራሾችም ለሕግ ያቀርባል፡፡ ማንኛውም በእንደዚህ አይነት ድርጊት የተሳተፉ ኀይሎችንንና ተባባሪዎችን ሁሉ ከያሉበት ለሕግ በማቅረብ አስፈላጊው ፍትሕ እዲረጋገጥ ይደረጋል፡፡

በመሆኑም መላው የክልላችን ሕዝብ የተፈጠረውን የሽብር ድርጊት ከማውገዝ ጀምሮ ወንጀለኞች ለሕግ ቀርበው ፍትሕ እንዲረጋገጥ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግና እንዲረጋጋ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የጥፋት ኃይሎች ከዚህ በላይ ዓላማ ያላቸው እና ክልሉን የማፍረስ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ በኋላ የክልሉ መንግሥት እንደማይታገስ እና ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ እናረጋግጣለን፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም
ባሕር ዳር

Leave a Reply