Site icon ETHIO12.COM

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የወለጋ ጉዞ ምን ይናገራል?

መንግስት በወለጋ ዞኖች ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ለጀመራቸው ስራዎች ውጤታማነት የአካባቢው ማህበረሰብ የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ፡፡ “ሕዝባችን ሰላሙን በማረጋገጥ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር የማድረግ የጋራ ኃላፊነት አለብን” ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በነቀምት ከተማ ከምሥራቅ ወለጋ፥ ከምእራብ ወለጋ ፥ ከቄለም ወለጋ እና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ከተውጣጡ ነዋሪዎች ጋር በልማት፣ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይት መድረኩ የወለጋና አካባቢው ሰፊ የመልማት አቅም ያለው ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ይህን አቅም ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ የአካባቢው ነዋሪዎች በቀጣይ ሰላማቸውን አስጠብቀው በአብሮነት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የውይይቱ ተሳተፊዎች በበኩላቸው መንግስት በኢትዮጵያ ያጋጠሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ሳያቆሙት የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ለአብነትም ፈተናዎችን በመቋቋም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን የማገባደጃ ምዕራፍ ላይ ማድረስ መቻሉ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የልማት ስራዎች ተስተጓጉለው መቆየታቸውን ያነሱት ነዋሪዎቹ፤ መንገድን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲገነቡ ጠይቀዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርክ በመገንባት በአካባቢው ያሉ ጸጋዎችን ጥቅም ላይ ከማዋል ባሻገር ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ላይ ትኩረት እንዲደረግም ነው የጠየቁት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው በዞኑ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የመንገድና ሌሎች የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስም የአካባቢው የሠላም ሁኔታ ፈተና ሆኖ መቆየቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አኳያ ነዋሪዎቹ አብሮነታቸውን በማጠናከር መንግስት የሚያከናውናቸውን የልማት ስራዎች ሊያግዙ ይገባል ብለዋል፡፡

የፌደራል መንግስት ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የሀሳብ ልዩነትን በመወያየትና በመነጋገር መፍታት የሚቻልበትን መንገድ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ የሀገር ጥቅምን የሚያሥጠብቁ ጉዳዮች ላይ በጋራ መቆም ይገባል ብለዋል፡፡

Exit mobile version