Site icon ETHIO12.COM

“…የዜሮ ድምር ፖለቲካዊ ሽብር ውጤት ወንጀል ነው” አብን


የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል በነበሩት አቶ ግርማ የሽጥላ ላይ የተፈጸመውን የግድያ ጥቃት በጽኑ ያወግዛል ፣ ጥልቅ ሃዘኑን ይገልጻል ፣ ለቤተሰቦቻቸው ፣ ለስራ ባልደረቦቻቸው እና ለመላው የሃገራችን ሕዝብ መጽናናትን ይመኛል።

የክልሉ መንግስት አመራሮች ላይ ተደጋግሞ እየተፈጸመ ያለው የግድያ ጥቃት ክልሉን የቀውስ ማዕከል የሚያደርግ ፣ የሃገራችንን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል የዜሮ ድምር ፖለቲካዊ ሽብር ውጤት በመሆኑ ድርጅታችን አብን በጽኑ የሚያወግዘው ወንጀል ነው።

ፓርቲያችን አብን ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል አመራሮች ላይ የተፈጸመው የግድያ ወንጀል ተሸፋፍኖ መቅረቱ እና ተጠያቂነት አለመስፈኑ ፣ በክልሉ አመራሮች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ተባብሶ እንዲቀጥል ምክንያት መሆኑን ያምናል። አሁንም ድርጊቱ አግባብ ባላቸው ተቋማት ሳይጣራ እና አጥቂዎቹ እና አጥፊዎቹ ተለይተው ሳይታወቁ ፣ ከጥቃቱ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኝት ሲባል በአደባባይ የሚደረጉ ፍረጃዎችን እና መግለጫዎችን ድርጅታችን አብን በጽኑ የሚያወግዝ ሲሆን ፣ ግድያው አግባብ ባላቸው ተቋማት በልዩ ትኩረት እንዲጣራ ፣ በድርጊቱ የተሳተፉ ተዋንያን በሙሉ እንዲለዩ እና አጥቂዎቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ ድርጅታችን አብን ጥሪውን ያስተላልፋል።

በመጨረሻም መላው የአማራ ሕዝብ እና ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በተፈጠረው ጥቃት ሳትረበሹ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ አንድነታችሁን እና ሰላማችሁን እንድትጠብቁ ድርጅታችን አብን ጥሪውን እያስተላለፈ ፣ በድጋሜ ለሟች አቶ ግርማ የሽጥላ ነብሳቸውን በአጸደ ገነት እንዲያኖርልን ፣ ለቤተሰቦቻቸው እና ለመላው የሃገራችን ሕዝብ መጽናናትን እንመኛለን።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

Exit mobile version