የኤርትራ የጦር ጀነራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች ጉብኝት “ወጣቶች መቼ ወደ መሪነት ያድጋሉ” የሚል የግርምት ጥያቄ አስነሳ

በጀነራል አብርሃ ካሳ የተመራ የኤርትራ የጦር ጀነራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች ልዑካን ቡድን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ሲጎበኙ በተላለፈ ቪዲዮና የምስል መረጃ ወጣቶች አለመታየታቸው በኤርትራ ፖለቲካ ተተኪው ሃይል መቼ ወደ አመራርነት ለማብቃት ሃሳብ ስለመኖሩ ጥርጥር እንዳላቸው ታዛቢዎች አመልከቱ።

የቡድን መሪውን ጀነራል አብርሃን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ዕድሚያቸው የገፋ የጦር መኮንኖቹ ትህነግ ሃይሉ ከተደመሰሰና ለሰላም እጁን ከሰጠ በሁዋላ የተደረገ ይፋዊ የስራ ጉብኘት እንደሆነ ታውቋል። የኤርትራ የጦር መኮንኖች እጅግ ዘመናዊ እንደሆነ በሚነገርለት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጉብኝት ማድረጋቸው ከመገለጹ ውጭ የልዑክ ቡድኑ አዲስ አበባ መገኘት ዋና ምክንያት አልተገለጸም።

የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከመንግስት ጋር መነጋገራቸውን እንደሚያውቁ የገለጹ እንዳሉት የኮንትሮባንድ ንግድ አንዱ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል። የጸጥታ ጉዳይን አስመልክቶ፣ በተለይም በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ ሰላም በሚሰፍንበት መልኩ ውይይት መደረጉም ተገልጿል። ይሁን እንጂ ዝርዝር ጉዳይ ለመግለጽ የመረጃው ሰዎች ለጊዜው አልወደዱም።

ኤርትራ ከትህነግ ጋር በተደረገ ውጊያ ተሳትፎዋንና ለተከዳው ሰራዊት ከለላ መስጠቷ እንደ ውለታ የሚመዘገብና የሚረሳ እንዳልሆነ ኢትዮጵያ ማስታወቋ አይዘነጋም። በተመሳሳይ በጦርነቱ ወቅት የኤርትራ ጦር ያጋዘውን መሳሪያ ለመመለስ ማቅማማቱ በርካቶችን ደስ እንዳላሰኘ በወቅቱ አስተያየት ሲሰጥበት እንደነበር ይታወሳል። ይህ ጉዳይ በዚህ ውይይት ይነሳ አይነሳ ግልጽ አይደለም። በኤርትራ በኩል ከትህነግ ጋር የተደረገውን ስምምነት በጫና የተደረገ እንደሆነ በመግለጽ ብዙም ደስተኛ እንዳልሆኑ ማስታውቃቸውም አይዘነጋም። በዚህ ውይይት የባድመ ጉዳይ ስለመነሳቱ የታወቀ ነገር የለም።

ከፍተኛ የተባሉት የኤርትራ መኮንኖች አዲስ አበባ መግባታቸውን ተከትሎ የወጡት መረጃዎች ከጉብኝቱ በላይ ዜና መሆናቸውን የጠቆሙና በስፍራ የነበሩ እንዳሉት ወጣት መኮንኖች በቡድኑ ውስጥ አይታዩም። በአንጋፋ መሪ የምትመራው ኤርትራ መቼና እንዴት ወጣት መሪዎችን ወደ ስልጣን እንደምታመጣ ለመገመት እጅግ እንደሚያስቸግርና በጉብኝቱ ወቅት ለነበሩ ይህ ጥያቄ ከምንም በላይ አስገራሚ እንደነበር ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በኤርትራ ባለስልጣናት እድሜ ደረጃ የሚገኝ አንድም ባለስልጣን የለም። ከሻዕቢያ ጋር በህብረት ደርግን ከጣሉት የትህነግ መሪዎች ውስጥም አሁን ላይ ምን አልባትም በትግራይ ካልሆነ በቀር በፌደራል ደረጃ በስም የሚጠቀስ በየትኛውም የሃላፊነት ደረጃ የሚገኝ እንደሌለም ታዛቢዎቹ አስታውቀዋል።

See also  ወደ አማራ ክልል የገባውን አሸባሪውን ህወሃት ለመደምሰስ ዝግጅት ተጠናቋል

የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ለልዑካን ቡድኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ያደረጉ ሲሆን ኢመደአ ባለፉት አመታት የሃገሪቱን የሳይበር ደህንነት በመጠበቅ የሰራቸውን ስራዎች እና በምርምር እና ልማት የታጠቃቸውን ምርት እና አገልግሎት ማስጎብኝተአቸውን ኢፕድ ነው የዘገበው።

ኢመደአ የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነት በመጠበቅ እንዲሁም ሃገራዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን በማረጋገጥ ለሃገራዊ ሰላም፣ ልማት እና ዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጉልህ ሚናን እየተጫወተ እንደሆነ አቶ ሰለሞን ሶካ ለልዑካን ቡድኑ አብራርተዋል፡፡ በቀጣይም ዘላቂ ሃገራዊ እና ቀጠናዊ ብልጽግናን በማረጋገጥ ሂደት ኢመደአ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ከቀጠናው ሃገራት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ሰለሞን ሶካ ገልጸዋል፡፡

የኤርትራ የጦር ጀነራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን በማረጋገጥ በኩል በቴክኖሎጂ ፣ በሰው ሃይል እና በአሰራር ረገድ የደረሰችበት ደረጃ ጠቃሚ ልምድ ያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል

በተለይም ታዳጊዎችን የሳይበር ታለንት ልማት ማዕከል በማደራጀት እና በሳይበሩ ዘርፍ የነገ ሃገር ተረካቢ ታዳጊ እንዲሆኑ እየሰራ ያለው ሥራ አበረታች ነው ብለዋል::

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ እንደ ወዳጅ ሃገር እና ህዝብ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም የኢትዮጵያን ልምድ በመውሰድ በቴክኖሎጂ እና በሳይበር ደህንነት ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አሉ ሲሉ አስተያየታቸውን መስጠታቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

Leave a Reply