Site icon ETHIO12.COM

ከአቶ ግርማ ግድያ ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ክስ ሊመሰረት ነው

የአቶ ግርማ የሺጥላንና አብረዋቸው የነበሩ ስድስት ጠባቂዎች ከመገደላቸው ስድስት ቀናት በፊት በተለይ እሳቸውን ማዕከል አድርጎ በተዘጋጀ ፕሮግራም ሊወገዱ እንደሚገባ መገለጹ በይፋ መረጃ የተያዘ ስለሆነና የአሜሪካ መንግስት የሽብር ተግባርን ስለማይቀበል ክስ ለመስረት ንግግር መጀመሩ ተሰማ።

የአማራ ብልጽግና ጽ/ቤት ሀላፊ ግርማ የሺጥላ በትውልድ ቀያቸው የማህበረሰብ የሰላምና የልማት ጥያቄዎች ተቀብሎ ለመፍታት ሲያወያዩ ቆይተው፣ እገረ መንገዳቸውን ዘመድ አዝማድ ጠይቀው ከቤተሰቦቸውና ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በስድስት ተሸከርካሪዎች ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ መንገድ ላይ አድፍጠው በጠበቁ ታጣቂዎች መገደላቸው፣ ልጃቸውና ሚስታቸው መትረፋቸውን የመንግስት ሚዲያዎች አስታውቀዋል።

አቶ ግርማ በ300 የዩቲዩብ ገጽ “ክልስ ነው ። ግማሽ ኦሮሞ ነው። እናቱ አማራ አባቱ ኦሮሞ ናቸው” በሚል አጥንታቸው ተቆጥሮ የስነልቦና ጠርዝ ማስያዣ ዝግጅት ሲደረግባቸው ነበር። የአማራ ህዝብ እንዲህ ያሉትን ማስወገድ እንዳለበትም በገሃድ ተነግሯል። ከተገደሉ በሁዋላም በዚህ ጣቢያ ” የሃዝን መግለጫ ባህላችን ቢሆንም ለሱ የሚሆን የለኝም” የሚል መልዕክት ተላልፏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው አሜሪካን አገር የሽብር ክስ ለመመስረት እንቅስቃሴ መጀመሩ የተገለጸው። ሽብርን አጥብቆ በሚቃወመው የአሜሪካ አገር ህግ መሰረት ክስ ለመስረት የህግ ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ መረጃ እየሰበሰቡ መሆኑንን ለጉዳይ ቅርብ የሆኑ ገልጸዋል። ምን አልባትም ድርጊቱ ወንጀል ከሆነ ይህንኑ ተግባር በገንዘብ የሚደጉሙ በተመሳሳይ በአሜሪካ ህግ መሰረት ማጣራት ሊካሄድባቸው እንደሚችል ተመልክቷል።

Exit mobile version