ETHIO12.COM

በሽብር ወንጀል እንደሚፈለጉ ዝርዝራቸው ይፋ የሆኑትን በኢንተርፖልና በደህንነት ስምምነቶች ተላልፈው እንዲሰጡ ስራ መጀመሩ ይፋ ሆነ

የፌደራሉ የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ሃይል ጽንፈኛ ባላቸው ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ይፋ ካደረገ ሃያ አራት ሰዓት ውስጥ አርባ ሰባት ተጠርጣሪዎችን ከነ ሙሉ ትጥቃቸው በቁጥጥር ስር ማዋሉን ይፋ ሲያደርግ እንዳስታወቀው በአሜሪካና በሌሎች አገራት በትስስር ሽብርን በማሰራጨት ወንጀል የሚፈለጉ የሚዲያና የህቡዕ ሃይላት መሪዎች በኢንተርፖል ተላልፈው እንዲሰጡ ስራ መጀመሩን አመልክቷል።

“እነዚህ የሽብር ኃይሎች ከሚኖሩባቸው ሀገራት በአለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) እንዲሁም እነሱ ከሚኖሩባቸው ሀገራት መንግሥት የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት ጋር በተመሠረቱ የትብብር ማዕቀፎች አማካኝነት ወደ ሀገር ቤት ተላልፈው እንዲሰጡ በህግም እንዲጠየቁ እየተሰራ ነው” መሆኑን ገልጾ ይኸው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል።

የጋራ ግብረ ሃይሉ እንዳለው የእነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎችን የሚዲያና ፕሮፓጋንዳ ክንፍ የሚመራው መስከረም አበራ በተባለች ግለሰብ መሆኑን ጠቅሶ፤ በዚህ ህቡዕ አደረጃጀት ውስጥ ከሀገር ውስጥ ዳዊት በጋሻው የተባለ ግለሰብ እንዲሁም ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ደግሞ ከኢትዮ 360 እና መረጃ ቲቪ ሀብታሙ አያሌው፣ ምንአላቸው ስማቸው፣ ብሩክ ይባስ እና እየሩሳሌም ተ/ፃዲቅ በተጨማሪም ዘመድኩን በቀለ እና ልደቱ አያሌው ከአንከር ሚዲያ መሳይ መኮንን እንዲሁም ሌሎች ግለሰቦች የዚህ እኩይ ዓላማ አስፈፃሚ አባላት መሆናቸውን በምርመራ መረጋገጡን አመልክቷል።

እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች የሀሰት ወሬዎችን በመፍጠር እና ከፍተኛ የሽብር ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ህዝቡን በብሄር እና በሀይማኖት በመከፋፈልና በማጋጨት የክልል እና የፌደራል መንግሥትን በኃይል ለመጣል እንዲሁም ሀገሪቱ ከጀመረችው የለውጥና የልማት መንገድ ወጥታ ወደ ለየለት ሁከትና ትርምስ እንድትገባ በህቡዕ ተደራጅተው እየሠሩ መሆናቸውን የገለፀው የጋራ ግብረ ኃይሉ፤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሆነው በሀሰት ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩትን እነዚህን ጨምሮ ሌሎችም በህቡዕ አደረጃጀቱ ውስጥ ያሉ ግለሰቦችም ጭምር በሽብርተኝነት ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

እነዚህ የሽብር ኃይሎች ከሚኖሩባቸው ሀገራት በአለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) እንዲሁም እነሱ ከሚኖሩባቸው ሀገራት መንግሥት የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት ጋር በተመሠረቱ የትብብር ማዕቀፎች አማካኝነት ወደ ሀገር ቤት ተላልፈው እንዲሰጡ በህግም እንዲጠየቁ እየሰራ መሆኑን እና ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ አክሎም፤ እነዚህ ውጭ ሀገር የሚኖሩ ተፈላጊዎች ከውጭ ሀገር የሚያገኙትን እና በሀገር ውስጥ ያላቸውን ሀብት ተጠቅመው ለዚህ እኩይ ተግባር እያዋሉ መሆኑን በምርመራ የተደረሰበት ስለሆነ በሀገር ውስጥ ያላቸውን ሀብት የመለየት እና በህግ የመቆጣጠር ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጭምር አስታውቋል።

ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ የነበሩ እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች የኢትዮጵያን አንድነት ከማይፈልጉ የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው መንግሥትን በኃይል ለማስወገድ ሲሰሩ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው የሚገኝ መሆኑን ያመለከተው የጋራ ግብረኃይሉ መግለጫ፤ ኅብረተሰቡ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወሰደውን እርምጃ ከትጥቅ ማስፈታት ጋር በማያያዝ ውዥንብር ለመፍጠርና የተሳሳተ መረጃ ለማሰራጨት ከሚጥሩ አካላት ራሱን እንዲጠብቅ በጋራ እንዲታገል ጥሪ አቅርቧል።

በመጨረሻም የተጀመረው ህጋዊ ኦፕሬሽን ከግቡ እንዲደርስ ህብረተሰቡ እያደረገ ላለው ከፍተኛ ተሳትፎ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ምስጋና እያቀረበ፤ በህግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ጥብቅ ክትትል እየተደረገባቸው ያሉ ተፈላጊዎችን ካሉበት ጠቁሞ እንዲያስይዝ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን እያቀረበ በቀጣይ የሚደርስበትን ውጤት ለህዝብ እየገለጸ እንደሚሄድ ያስታውቃል።

የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል በአማራ ክልል እየወሰደ ባለው እርምጃ  ህቡዕ አደረጃጀት ውስጥ ሲንቀሳቀሱና የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ 47 ተጠርጣሪዎችን ከበርካታ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎች፣ ቦንቦችና ተቀጣጣይ ፈንጂዎች እንዲሁም ከሳተላይት መገናኛ መሣሪያዎች እና የተለያዩ መረጃዎችን ከያዙ ላፕቶፖች ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።

የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ሚያዝያ 22 ቀን 2015 ዓ.ም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል “በሽብር በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎች” ሲል ስም ዘርዝሯል እነሱም

1. ሀብታሙ አያሌው፣

2. ምንአላቸው ስማቸው

3. ብሩክ ይባስ እና

4. እየሩሳሌም ተ/ፃዲቅ

5. ዘመድኩን በቀለ

6. ልደቱ አያሌው

7. መሳይ መኮንን

8. ጎበዜ ሲሳይ

9. ምህረት ወዳጆ (ምሬ ወዳጆ)

10. በለጠ ጋሻው እና

11. ሙሉጌታ አንበርብር

Exit mobile version