Site icon ETHIO12.COM

ሳማንታ ፓወር “ከባድ የሆነዉን ዉሳኔ ወስነናል”

አሜሪካ ለትግራይ ክልል የምታደርገዉን የምግብ እርዳታ ልታቆም መሆኑን ገለጸች፡፡

የአሜሪካዉ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስ ኤድ ዋና ሃላፊ በጦርነት ወደተጎዳችዉ ትግራይ ክልል የምናደርገዉን የምግብ እርዳታ እናቆማለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ወደ ትግራይ የሚላኩ የምግብ እርዳታዎችን የሚያጓጉዙ ተሸከርካሪዎች አገልግሎት እንዲያቆሙ እያደረግን ነዉ ያለ ሲሆን ለዚህም በእርዳታ የሚሰጠዉ ምግብ በገበያዎች ዉስጥ ሲሸጥ መገኘቱን ነዉ እንደ ምክንያት ያነሳዉ፡፡

የዩኤስ ኤድ ሃላፊ ሳማንታ ፓወር ትናንት በሰጡት መግለጫ‹‹ እርዳታዉ በጦርነት ምክንያት ክፉኛ በረሃብ ለተጎዱ የትግራይ ህዝቦች ታስቦ የተሰጠ ነዉ፡፡›› ብለዋል፡፡

‹‹ወደ ፊት የሚሻሻል ጉዳይ እስኪመጣ ድረስ በዩኤስ ኤድ አማካኝነት ወደ ትግራይ የሚላከዉን ሁሉንም ምግብ ነክ እርዳታ ለማቆም ከባድ የሆነዉን ዉሳኔ ወስነናል፡፡›› ሲሉ አክለዋል፡፡

የዩኤስ ኤድ ኢንስፔክተር ጀነራል ጉዳዩን መመርመሩን ገልጸዉ እርዳታዉን ማቆሙ ትክክለኛ ዉሳኔ ሆኖ በመገኘቱ ይህን ለመወሰን መገደዳቸዉን ገልጸዋል፡፡

ሳማንታ ፓወር እንዳሉት ጉዳዩን ከፌደራል መንግስት እና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር መወያየታቸዉን ገልጸዉ ፣ የፌደራሉም የክልሉም መሪዎች በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ለይቶ በማዉጣት እና ተጠያቂ በማድረግ ረገድ ሀላፊነታቸዉን እንደሚወጡ አሳዉቀዉኛል ብለዋል፡፡

ነገሮች ከተስተካከሉ እና ወደ ቀድሞ ቦታቸዉ ከተመለሱ ዩኤስ ኤድ በድጋሚ እርዳታ የሚያስፈልጋቸዉን በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመርዳት ዝግጁ ሆኖ ይጠብቃል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ወደ ትግራይ በሚላኩ የምግብ እርዳታዎች ዙሪያ የተበራከተዉን የሌብነት ጉዳይ ለመመርመር በማሰብ እርዳታዎችን ለጊዜዉ ማቆሙን ካሳወቀ ከጥቂት ቀናት በኋላ ዩኤስ ኤድ ይህን ዉሳኔ ማስተላለፉ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ወደ 20 ሚሊየን የሚጠጉ እርዳታ ጠባቂ ዜጎችን ችግር ላይ ይጥላቸዋል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በክልሉ ተፈጸመ በተባለው የዕርዳታ እህል ዝርፊያ ዙሪያ አስተዳደራቸው ምርመራ መጀመሩን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል።
ከዓለማቀፍ የረድዔት ድርጅቶች፣ ዲፕሎማቶችና ከክልሉ ማኅበረሰብ መሪዎች የዕርዳታ እህል ላልታሰበለት ዓላማ እየዋለ ስለመኾኑ ጥቆማ እንደደረሳቸውና ድርጊቱቱ እንደተፈጸመ “በርካታ መረጃ” መኖሩን የገለጡት ጌታቸው፣ ጥፋተኛው ማንም ይኹን ማን ተጠያቂ እናደርጋለን ያሉ ሲሆን ኾኖም ኹሉም ረድኤት ድርጅቶች በክልሉ የዕርዳታ አቅርቦታቸውን እንዲቀጥሉ አቶ ጌታቸው ጠይቀዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8

Exit mobile version