Site icon ETHIO12.COM

የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርምርራና አጠቃላይ ሂደት ኢትዮጵያ ለተመድ ሪፖርትና ማብራሪያ አቀረበች

በተባበሩት መንግስታት የፀረ-ማሰቃየትና የጭካኔ አያያዝ አለምቀፍ ስምምነት (Convention Against Torture) መሰረት የተጣለባትን ግዴታ ለመወጣት እያደረገች ያለዉ ጥረት እና የስምምነቱን አፈጻጸም በሚመለከት ሪፖርት አዘጋጅታ በማቅረብም ሆነ በኮሚቴው ፊት ቀርባ ለመገምገም በመወሰን ከኮሚቴዉ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠቷ ሀገሪቱ ሰብዓዊ መብትን ለማክበር እና ለማስከበር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የፀረ-ማሰቃየትና የጭካኔ አያያዝ አለምቀፍ ስምምነት አተገባበርን የሚከታተለዉ ኮሚቴዉ ሰብሳቢ ሚስተር ክላውደ ሄለር ገለጹ፡፡

ኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት እና በዉይይት ወቅት የተሰጡ ምላሾች ላይ ተመርኩዞ በቀጣይ የሚሰጣቸው ምክረ ሃሳቦች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ የበለጠ ያሻሽለዋል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ76ኛው የተባበሩት መንግስታት የፀረ-ማሰቃየትና የጭካኔ አያያዝ ኮሚቴ (Committee Against Torture) የውይይት መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ከኮሚቴው አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠች ሲሆን በዉይይቱ ላይ በፍትህ ሚኒስቴር ፤ ሚኒስትር ድኤታ አቶ ዓለምአንተ አግደዉ የተመራና ከተለያዩ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ጭምር የተካተቱበት የልዑካን ቡድን ተሳትፏል፡፡

በስዊዘርላንድ ጄኒቫ እ.ኤ.አ ሜይ 3 እና 4 በተካሄደው በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ አለምአንተ አግደው ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለማቀፋዊ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች መሰረት የተጣሉባትን ግዴታዎች ከመወጣት አንጻር የስምምነቶቹን አተገባበር በሚመለከት ወቅቱን የጠበቀ ሪፖርት ማቅረቧ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለመከላከል ቁርጠኝነት እና ዝግጁነትን እንዳላት ያሳያል ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴዴታው አክለውም በሀገሪቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመቋቋም መንግስት ለሰብዓዊ መብት እሴቶች እና ለዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት ካለው ቁርጠኝነት አንጻር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምህዳሩን ለመቀየር የሚያስችሉ ጉልህ ተቋማዊ፣የሕግና የአሰራር ማሻሻያ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡

መንግስት ሴቶች፣ ህጻናት እና አካል ጉዳተኞችን እና ሌሎች ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ የማህበረሰቡን ክፍሎች ቅድሚያ በመስጠትም ከማሰቃየትና የጭካኔ አያያዝ ለመጠበቅ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ዜጎችን ከማሰቃየት እና ከኢ-ሰብዓዊ አያያዝ የተጠበቁ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ያላቸውን መብት በሚመለከት የህግ ንቃታቸውን ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ትምህርቶችን ከመስጠት ጀምሮ የመንግስት አገልግሎቶችም ይህን መብት በጠበቀ መልኩ እንዲመሩ ከማድረግ አንጻር የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የተለያዩ ቁርሾዎችንና በተለያዬ ጊዜ የሚያጋጥሙ ግጭቶችን በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው ፤ ልዩነትን የሚያስተናግድ እና ሰብዓዊነትን ያከበረ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ያላትን ጽኑ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ለማሳደግ የመጀመሪያውን እና 2ኛውን የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሃ ግብር አጽድቃ ስትተገብር የቀየች ሲሆን በአሁኑ ጊዜም 3ኛውን ድርጊት መርሃ ግብር አጽድቃ ወደ ተግባር ለመግባት በዝግጅት ላይ ትገኛለች ያሉት አቶ አለምአንተ ሰባት አባላት ያሉት እና በክቡር የፍትሕ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሄራዊ ቦርድ ተቋቁሞ ስራዎችን በትኩረት በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የሰብአዊ መብት አተገባበር ሁኔታን በአግባቡ ለመከታተል እንዲቻል የሚመለከታቸዉ ተቋማት ፎካል ፐርሰን መድበዉ እንዲሰሩ የተደረገ ሲሆን ከመረጃ አያያዝ አንጻር የሚጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍም በተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ ከፍትህ ሚኒስትር ጋር በትብብር ዳታ ቤዝ የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እ.ኤ. አ በ2018 የተጀመረዉን ሀገራዊ ሪፎርም ተከትሎ ሰፋፊ የሕግና የፍትህ ማሻሻያ ስራዎች መሰራታቸዉን ጠቅሰዉ በተለይም የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነዉ እንዲሰሩ ለማስቻል መንግስት ከፍተኛ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡
ተቋማትን ከመገንባት አንጻር በፍርድ ቤቶች፣ በፖሊስ፣ በማረሚያ ቤቶችና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ የዴሞክራሲ ተቋትማን ሪፎርም ለማድረግ የተወሰዱ እርምጃዎችም አብይ ትኩረት ተሰጧቸዉ በመክፈቻ ንግግር ላይ ተዳሰዋል፡፡

አቶ አለምአንተ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አንጻር የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በጋራ ባካሄዱት ምርመራ መሰረት ባስቀመጡት ምክረ ሀሳብ ላይ ተመርኩዞ የሚኒስትሮች ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በጦርነቱ መሃል የተፈጸሙ ወንጀሎችን የመመርመር እና የወንጀል ተጎጂዎችን ለመደገፍ ያለሙ ስራዎች የተሰሩ መሆኑን አውስተው በኮሚቴው ምክረ ሀሳብ እና የፕሪቶሪያዉን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር የተያያዙትን ጨምሮ ሁሉንም ጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትህ ለማየት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ለማዘጋጀት የሚስችል ጥናት እና የፖሊሲ አማራጭ ሃሳቦች ረቂቅ ተዘጋጅቶ አገር አቀፍ ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከማሰቃየት እና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ እና ቅጣት የመጠበቅ መብትን ጨምሮ የሰዎች መብቶችን ከመጠበቅ እና ከማስከበር አንጻር የተወሰዱት እርምጃዎች የሚበረታቱ ቢሆንም ያልተሰሩ እና በቀጣይ ሊሰሩ የሚገቡ ተግባራትን ለመከወን መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም የተገኙ ተጨባጭ ለውጦችን ቀምሮ ለኮሚቴው ወቅቱን የጠበቀ ሪፖርት ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመክፈቻ ንግግሩን ተከትሎ በኮሚቴው ውይይት ላይ ከማሰቃየት እና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ የሀገራትን አፈጻጸም ለመገምገም የተቋቋመው ኮሚቴ አባላት በተለይም ራፖርተሮች በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠሩ ግጭቶች ዙሪያ የተፈጠሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከማጣራት እና ተጠያቂነትን ከማስፈን አንጻር ስለተሰሩ ስራዎች፣ ፍርድ ቤትን እና የዴሞክራሲ ተቋማትን ከማጣናከር እና ህግ እና ስርዓትን ከማሻሻል አንጻር እንዲሁም የተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎች አያያዝን ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎችን አስመልክተው ላነሷቸው ጥያቄዎች በልዑካን ቡድኑ ማብራሪያ እና ምላሽ ተሰጧል፡፡

አቶ አለምአንተ አግደው በማጠቃለያ ንግግራቸው ከውይይቱ በመነሳት የለየናቸውን ተግዳሮቶች እና ውስንነቶች የዜጎችን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ እና በተለይም የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያጎሉ የህግ ማዕቀፎችን ማውጣትና ማሻሻልን ጨምሮ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ በትኩረት ከሚሰሩ ስራዎች መካከል እንደሆኑ ገልጸዋል፡:

በመላ ሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንም ከታጠቁ ሀይላት ጋር ድርድር በማድረግ እና የሰላም ስምምነት በመፈራረም የጀመርናቸው ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ሚኒስትር ዴኤታው በመልዕክታቸው በሀገራችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲጎለብት ፤ የአገራችንን ልዋላዊነት፣የግዛት አንድነትና ነጻነት ባከበረ መልኩ በጋራ ለመስራት ከፈቀዱ አለም አቀፍ እና አህጉራዊ እንዲሁም ሀገር በቀል ድርጅቶች እና ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት ከወትሮው በተሻለ ዝግጁ ነን ካሉ በኋላ በተለይም ኮሚቴው በውይይቱ ላይ የተጠየቁትን ጥያቄዎች እና የመንግስታችንን ምላሽ ከግምት አስገብቶ የሚሰጠውን ምክረ ሀሳብ ተቀብለውን ተግባር ላይ ለማዋል ተገቢውን ጥረት እንደምናደርግ ቃል እገባለው ብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የፀረ-ማሰቃየትና የጭካኔ አያያዝ ኮሚቴ (Committee Against Torture) ሰብሳቢ የሆኑት ክላውደ ሄለር መድረኩን ሲቋጩ ኢትዮጵያ በስምምነቱ መሰረት የተጣሉባትን ግዴታዎች ለመወጣት ያደረገችው ጥረት እና ሪፖርቱን አዘጋጅታ ለማቅረብም ሆነ በኮሚቴው ፊት ቀርበው ምላሽ መስጠታቸው ሀገሪቱ ሰብዓዊ መብትን ለማክበር እና ለማስበር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ካሉ በኋላ ኮሚቴው የቀረበው ሪፖርት ላይ ተመርኩዞ በቀጣይ የሚሰጣቸው ምክረ ሃሳቦች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በበለጠ ያሻሽለዋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

Ministry of justice

Exit mobile version