Site icon ETHIO12.COM

መከላከያ ሠራዊት በጥፋት ሃይሎች ታግቶ የቆየ 7250 ኩንታል እህል አሥለቀቀ

በአማራ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አጉራባች ወረዳዎች በጥፋት ሃይሎች ታግቶ የቆየ 7250 ኩንታል እሕል በቀጠናው የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ባደረገው ዘመቻ በማሥለቀቅ ለባለንብረቶች ገቢ ተደርጓል ።

ሻለቃ አማከል ባልቻ እንደገለፁት ከራሱ በፊት ሀገሩንና ሕዝቡን ያሚያስቀድመው ስራዊታችን በቀጠናው በነበሩ ሕገወጥ ሃይሎች የኢ-መደበኛ እንቅስቃሴ በበርሃ ታግቶ የነበረውን አህል በ104 የጭነት መኪና በመጫን ወደ ጃዊ ወረዳ ፈንደቃ ከተማ ማድረስ ችሏል።

የህንኑ የግል ንብረት ከጥፋት ሃይሎች አስለቅቆ ለባለንብረቶች ለመመለስ በተደረገው እንቅስቃሴ የህብረተሠቡ የተቀናጀ ትብብር እና ጥቆማ የሚደነቅ መሆኑን የገለፁት ሻለቃ አማከለ በአካባቢው የሚገኙ የሜካናይዝድ እና እግረኛ ክፍለጦሮች ከሃገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ጋር ተቀናጅተው በመስራት የተገኘ ውጤት መሆኑንም አብራርተዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ ብርቱ ጥረት እና የአካባቢው ነዋሪ ተቀራርቦ በመስራቱ በድብቅ ተከማችቶ የነበረው እህል ለባለ ንብረቶቹ የደረሠ ሲሆን በባለ ንብረቶች አማካኝነት ለገበያ እንዲውል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የጃዊ ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ሃላፊው ንጉስ ይፍሩ ተናግረዋል።

የጃዊ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደስታ አንለይ በበኩላቸው የሃገር ባለውለታ የሆነው ጀግናው የመካለከያ ሠራዊት በአስቸጋሪ መልክዓ ምድር በመሰማራት ሃገርን እና ህዝብን የሚያኮራ ተግባር በወረዳው ባሉ አካባቢወች በማከናወን ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

የሕዝብ ፍቅር ያለው ጀግናው ስራዊታችን በአጎራባች ወረዳዎች በመሰማራት ለሚያከናውነው የሠላም እና የልማት ስራ ማህበረሰቡ እንደወትሮው ሁሉ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ኩራባቸው ግርማ የኢፌዴሪ መከላከያ

Exit mobile version