Site icon ETHIO12.COM

ሳይፋቱ ፍቺ (Defacto Divorce)

ጋብቻ የቤተሰብ መሰረት በመሆኑ በህግ እውቅና የተሰጠው እና ከምስረታው ጀምሮ ጥበቃ የሚደረግለት ተቋም ነው፡፡ በዚህም የሚፈርስበት ሁኔታ ጭምር በቤተሰብ ህጉ በግልፅ ተመላክቷል፡፡ በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ እንደተደነገገው ጋብቻ የሚፈርሰው ከተጋቢዎች አንዱ ሲሞት ወይም በፍርድ ቤት የመጥፋት ውሳኔ ሲሰጥ፣ ጋብቻ ለመፈፅም መሟላት ካለባቸው ሁኔታዎች አንዱ በመጣሱ ምክንያት በህግ መሰረት ጋብቻ እንዲፈርስ ሲወሰን ወይም የፍቺ ውሳኔ ሲሰጥ ነው፡፡ በዚህ አጭር ፅሁፍ በቤተሰብ ህጉ ፍቺ የሚፈፀምባቸውን ሁኔታዎች እና በፍርድ ቤት ሳይወሰን ተለያይቶ መኖር በህጉ የሚስተናገድበትን ሁኔታ እንመለከታለን፡፡

ፍቺ የሚፈፀምበት ሁኔታ

ጋብቻ በፍቺ እንዲፈርስ ሊወሰን የሚችለው ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት ሲወስኑና ይህንኑ ለፍርድ ቤት አቅርበው ውሳኔያቸው ተቀባይነት ሲያገኝ እና ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ሁለቱም ተጋቢዎች በአንድነት ጋብቻቸው በፍቺ እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት ጥያቄ ሲያቀርቡ ነው፡፡ ጋብቻ በስምምነት ሲፈርስ ፍርድ ቤት የፍቺ ስምምነቱን የሚያፀድቀው የባልና ሚስቱ ትክክለኛ ፍላጎት መሆኑን እንዲሁም ስምምነቱ ከህግና ሞራል ጋር የማይቃረን መሆኑን ሲያምን ነው (የቤተሰብ ህግ አንቀፅ (አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2)፡፡ ፍርድ ቤቱ የፍቺን ስምምነት ያፀደቀው እንደሆነ ስለፍቺው ውጤት ያደረጉትንም ስምምነት አብሮ ሊያፀድቀው የሚችል ሲሆን ባልና ሚስቱ ስለፍቺ ውጤት ያደረጉት ስምምነት የልጆቻቸውን ደህንነትና ጥቅም በበቂ ሁኔታ የማያስጠብቅ ወይም የአንደኛውን ተጋቢ ጥቅም የሚጎዳ ሆኖ ካገኘው ፍርድ ቤት የፍቺውን ስምምነት ብቻ በማፅደቅ የፍቺውን ውጤት በተመለከተ ጉድለቶቹ እንዲስተከካሉ ተገቢ መስሎ የታየውን ውሳኔ ይሰጣል (የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 80/3)። በመሆኑም ጋብቻ በፍቺ የሚፈርሰው ፍርድ ቤት የፍቺ ውሳኔ ሲሰጥ መሆኑን መረዳት ይቻላል::

ሳይፋቱ ፍቺ (Defacto Divorce) ምንነት

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በ1999 ዓ.ም በሰበር መዝገብ ቁጥር 20938 ሰጥቶት በነበረው ውሳኔ መሰረት ሳይፋቱ ፍቺ ማለት በፍርድ ቤት የፍቺ ውሳኔ ሳይሰጥበት ባልና ሚስት ለበርካታ ዓመታት ተለያይተው በመኖር፣ የየራሳቸውን ሕይወት እየኖሩ (አግብተው ወይም ሳያገቡ) ከቆዩ፣ ምንም እንኳን ቀደም ብሎ የተፈጸመ ጋብቻ የነበራቸው ቢሆንም ሁለቱም በየፊናቸው የየራሳቸውን ሕይወት መጀመራቸው ከተረጋገጠ ጋብቻቸው እንደፈረሰ የሚቆጠርበትን ሁኔታ የሚያመለክት ነው፡፡

ሳይፋቱ ፍቺ (Defacto Divorce) በኢትዮጵያ ህግ የሚታይበት ሁኔታ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጠው ውሳኔ በሥር ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅ በመሆኑ ምክንያት ችሎቱ የሰጠው የህግ ትርጉም ሥራ ላይ ሲውል የቆየ ቢሆንም በርካታ ሴቶች ሀብት ንብረታቸውን እንዳሳጣቸው ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ ይኸውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79 ሕግ የመተርጎም ሥልጣን ለፍርድ ቤት፣ በአንቀጽ 55 ደግሞ ሕግ የማውጣት ሥልጣንን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰጠ ቢሆንም ሰበር ሰሚ ችሎት ግን ከሕጉ ዓላማ ውጪ የሆነ አስገዳጅ ትርጉም መስጠቱ ሕገ መንግሥቱን እንደሚቃረን በመጥቀስ ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቤቱታ ቀርቧል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎት በውሳኔው ጋብቻ ሊፈርስ የሚችልባቸውን ምክንያቶች በተመለከተ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75 እና 82 የተመለከቱ ድንጋጌዎችን በማለፍ አራተኛ ምክንያት ማስቀመጡም ተገቢ አለመሆኑ፣ የጋብቻን ፍቺ የመወሰንና የጋብቻው በፍቺ መፍረስ የሚያስከትለውን ውጤት የመወሰን ሥልጣን የፍርድ ቤት ብቻ ሆኖ የተደነገገበት የራሱ ዓላማ ያለው መሆኑን፣ ጋብቻ በፍቺ ሲፈርስ የተጋቢዎችን የንብረት ክፍፍልና የሕፃናትን የአስተዳደግ ሁኔታ አገናዝቦ ውሳኔ መስጠት ያለበት ፍርድ ቤት መሆኑ እንዲሁም ተጋቢዎች ተለያይተው በመኖራቸውና የየራሳቸውን ሌላ ሕይወት በመጀመራቸው ‹‹ጋብቻቸው ፈርሷል›› የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ተጋቢዎች በቸልተኝነት ጋብቻቸውን ከፍርድ ቤት ዕውቅና ውጪ በፍቺ መልክ እንዲያቋርጡ መንገድ የሚከፍትና ሕገ-ወጥነትን የሚያበረታታ መሆኑ ቅሬታው ተቀባይነት እንዲያገኝ ያስቻሉ ምክንያቶች ናቸው፡፡

በመሆኑም የሰበር ሰሚ ችሎቱ አስገዳጅ ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 ከተመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር፣ በአንቀጽ 51 ከተመለከተው የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር ድንጋጌዎች ጋር የሚጋጭ ሆኖ ስላገኘው የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ጉባዔው በሙሉ ድምፅ በመወሰን በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 84(1) እና በአዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 3(1) ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡ ፌዴሬሽን ምክር ቤትም የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ በመቀበልና ይሁንታ በመስጠት አስገዳጁን የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ሰርዞ ጋብቻ ሊፈርስባቸው ከሚችሉ ሦስት በህግ ከተመለከቱ ምክያቶች ውጪ ዝም ብሎ መለያየትና መቆየት ጋብቻን ሊያፈርስ እንደማይችል በፌደሬሽን ምክር ቤት 5ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 5ኛ ዓመት፣ 1ኛ መደበኛ ጉባዔ መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም የመዝገብ ቁጥር 49/10 ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/93 አንቀጽ 11/1 እና 56 መሰረት በህገ-መንግስት ትርጉም ላይ ምክር ቤቱ የሚሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ አጠቃላይ ውጤት የሚኖረው ሲሆን ወደፊት በሚወሰኑ ተመሳሳይ ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች ላይ የአስገዳጅነት ባህርይ ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም ምክር ቤቱ በቀረበለት ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ውሳኔውን የማክበርና የመፈፀም ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡

በአጠቃለይ የጋብቻ መፍረስ በልጆች እና በንብረት አስተዳደር ላይ ውጤት ያለው በመሆኑ በህጉ የተቀመጡትን የጋብቻ መፍረስ ምክንያቶች ብቻ መከተል ግዴታ መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት ከሰጠው የህገ-መንግስት ትርጉም መረዳት ይቻላል፡፡ ስለሆነም በጋብቻ ውስጥ ያሉ ሰዎች መለያየት ከፈለጉ በህጉ መሰረት ፍቺ መፈፀም ይኖርባቸዋል፡፡
በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

Ministry of justice

Exit mobile version