ETHIO12.COM

ሃይማኖትና ብሄርን የተሸሸገው “ጽንፈኝነት”እና ጣጣው

ማንም ያድርገው ማን ጽንፈኝነት ውጤቱ ኪሳራ ነው። ጽንፈኝነት የመረጡ አካላት አዋጪ መንገድ እንዳልተከተሉ ብዙ ምስክር አገሮች አሉ። ጽንፈኛነት የገነገነባቸው አገራት ወድመዋል። ተበትነዋል። ፈርሰዋል። የሚምሉበት ህዝብ ተበትኖ ስቃይ ላይ ወድቋል። ለማኝ ሆኗል። ሃፍረት ለብሷል። ጽንፍ መያዝ በየትኛውም ሂሳብ አዋጪ አይደለም። በአገራችን ይህ አክሳሪ መርዘኛ አመለካከት እየወረረን ነው። ይህ ውዳቂ መንገድ ጨርሶ እንዳይበላን እገሌ ከገሌ ሳይባል መታገል ግድና ህልውና ነው። ካልሆነ የሌሎች አገሮችን ዕጣ መቀበል አምራጭ ሳይሆን ግዴታ ይሆናል።

ይህ ሳይሆን ቀርቶ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ እየገነገነ ከሄደ ግን እንደ ሀገር የምንመኘውን ዘላቂ ሰላምም ሆነ ልማት ማረጋገጥ ከዚያም ከፍ ሲል እንደአገር በጋራ ለመኖር የሚኖረን ተስፋ የመነመነ ይሆናል …. ጽንፈኝነት ለሌላው አመለካከት ቦታ የማይሰጥ በመሆኑ አብሮ የመኖርን እና በመነጋገር ችግሮችን የመፍታት ባህልን የሚያጠፋ ነው። የእኔ ሃሳብ ብቻ ትክክል ነው ብለው የሚያስቡ አካላት የሚሰባሰቡበት እንደመሆኑ ለሌላው ሃሳብ ፈጽሞ ቦታ ባለመስጠት በመነጋገር እና በመደራደር ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ፍላጎትን በሃይል ለመጫን ተገቢነት የሌላቸው ኢፍትሃዊ እንቅስቃሴዎች እንዲደረጉ ምክንያት

አሁን አሁን ጽንፈኝነት በአገራችን ከሃሳብ አልፎ ጉዳቱ በተግባር እየታየ መምጣቱን ብዙዎች ይስማማሉ።ጽንፈኝነት በብሔር ወይም በሃይማኖት ዋሻ በመደበቅ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማሳካት የሚፈልጉ ኃይሎች መሰባሰቢያም ነው።

ጽንፈኝነት ለሌላው አመለካከት ቦታ የማይሰጥ በመሆኑ አብሮ የመኖርን እና በመነጋገር ችግሮችን የመፍታት ባህልን የሚያጠፋ ነው። የእኔ ሃሳብ ብቻ ትክክል ነው ብለው የሚያስቡ አካላት የሚሰባሰቡበት እንደመሆኑ ለሌላው ሃሳብ ፈጽሞ ቦታ ባለመስጠት በመነጋገር እና በመደራደር ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ፍላጎትን በሃይል ለመጫን ተገቢነት የሌላቸው ኢፍትሃዊ እንቅስቃሴዎች እንዲደረጉ ምክንያት እየሆነ መሆኑን ምሁራን ይገልጻሉ፡፡

ጽንፈኝነት እንደ አገር የእርስ በእርስ ግንኙነትን በማሻከር ወንድማማችነት እንዳይኖር በማድረግ ማህበራዊ ግንኙነትን የሚጎዳ፣ አገር እንዳይረጋጋ በማድረግ ኢኮኖሚው እንዳያድግ ማነቆ በመሆን እና ፖለቲካዊ ቀውስ የሚፈጥር በመሆኑ በጊዜ መገታት እንዳለበትም ያሳስባሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሃሳባቸውን የሰጡት የደቡብ ክልል ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ፤ የጽንፈኝነት ምንጩ የራስ ጥቅም እና የግል ፍላጎት ማሳካት ሲሆን እኔ የበላይ ፣ፍጹም እና ትክክል ነኝ በሚል ሌላውን የሚጨፈልቅ አስተሳሰብ ነው ይላሉ፡፡

እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ፤ ጽንፈኝነት በአገራችን ብሔርን እና ሃይማኖትን መሸሸጊያ አድርጎ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች እያስከተለ ነው።እኛ ኢትዮጵያውያን የምንታወቀው በአቃፊነት እና አብሮ በመኖር ነው።በአንጻሩ ጽንፈኝነት በዓለም የምንታወቅበት የአብሮነታችን ማህበራዊ እሴት እንዲሸረሸር እያደረገ ይገኛል፡፡

በጽንፈኝነት አስተሳሰብ ምክንያት በአገራችን ብዙ ሰዎች መፈናቀላቸውን፤ ንብረት መውደሙን፤ የሰው ሕይወት ጭምር መጥፋቱን የሚናገሩት አቶ ጥላሁን፤ በኢኮኖሚውም የውጭ ኢንቨስተሮች ነጻ ሆነው እንዳይሰሩ መሰናክል በመሆን፣ በሰከነ ሁኔታ የሚሰሩ እጆች ሁሉ ባለመስራታቸው የጉልበት ምርታማነት እንዲቀንስ በማድረግ ለኑሮ ውድነት አንድ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

ጽንፈኝነት እርስ በእርስ ተናቦ መጓዝ እንዳይኖርና መጠራጠር እንዲኖር በማድረግ የፖለቲካ ቀውስ እንደሚፈጥር የተናገሩት አቶ ጥላሁን ፤ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የነበረው ጦርነትም እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን በሚል ወደ ትልቅ ቀውስ የተሸጋገረ የጽንፈኝነት ውጤት እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

በጽንፈኝነት አካሄድ የትኛውም አገር አልሰለጠነም ያሉት ኃላፊው፤ የሃሳብ ልዩነቶች ካሉ በተለመደው መንገድ ቁጭ ብለን በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር እና በመወያየት መፍታት አለብን ብለዋል፡፡

ጽንፈኝነት የማህበራዊ ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ቀውስ በመፍጠር አገርን ስጋት ውስጥ የሚከት አደገኛ አስተሳሰብ በመሆኑ መገታት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

አቶ ጥላሁን ጽንፈኝነትን እያበረታታ እና አቅም እንዲያገኝ እያደረገ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች የሀሰት ፕሮፓጋንዳ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያውያን ሆነው ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚሰሩ ሰዎች ከእኩይ ድርጊታቸው መታረም እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ጽንፈኝነት ላይ ሃሳባቸውን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሰጡት በአማራ ክልል የተፎካካሪ ፓርቲዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን አለምነህ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ፅንፈኝነት ካለ መነጋገር፣ መደራደር እና መስማማት የሚባል ነገር የለም።

ፅንፈኝነት በከፍተኛ ጥላቻ ላይ በመመስረት የራስን ፍላጎት ብቻ ማሳካትን መሠረት ያደረገ ነው። አንዳንዱ የራሱን ፍላጎት መሬት ለማስነካት የትኛውንም ዓይነት እርምጃ ይወስዳል። ፅንፈኝነት ደም በማፍሰስም ቢሆን አሸናፊ መሆን የሚፈልግ በመሆኑ ይህን ለማድረግ ግብረገብነት፣ መቻቻል እና መከባበር የመሳሰሉትን ጉዳዮች ረግጦ እንደሚሄድ የገለጹት አቶ ተስፋሁን፤ በዋናነት ከበደልና ከቂም በመነጨ ወሰን አልባ ጥላቻ የራስን ፍላጎት ማስፈፀም መፈለግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ተስፋሁን አገላለጽ፤ ከፅንፈኝነት የሚወለደው ሽብርተኝነት ነው። በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት፣ በመነጋገርና በመቻቻል የማያምን አካል ወደሽብር ይሄዳል፤ በዚህ አይነት አካሄድ መንግሥታዊ ሥልጣንን ለመቆጣጠርም ሆነ ሰላማዊ አገርን ለመፍጠር ያለው ዕድል ግን አናሳ እንደሆነ ገልጸዋል።

ፅንፈኝነት ከጋራ አሸናፊነት ይልቅ ለብቻዬ አሸናፊ ልሁን የሚል በመሆኑ ጥፋት፣ ውድመት እንዲሁም አለመረጋጋት እንደሚያስከትል ጠቁመው፤ የሕዝብን አንድነት እና አብሮ የመኖር ባሕልንም እንደሚሸረሽር ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ፅንፈኝነት ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ እያደረገ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ተስፋሁን፤ በዚህም ዜጎች በማንነታቸው ሲፈናቀሉ እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኔ ብቻ ነው የሚል እና ሌላውን አግላይ ሁኔታ እንዳለ ተናግረው፤ ከእኔ ውጪ ለምን ሌላ ሃሳብ ታራምዳለህ በሚል መገዳደሎችም እንደነበሩ አስታውሰዋል።

እንደ አቶ ተስፋሁን ገለጻ፤ ጽንፈኝነት አገር ሰላም እንዳይኖራት፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይኖር እና ማኅበራዊ እሴት እንዲበጠስ የሚያደርግ የአገር ጠንቅ ነው። ኢትዮጵያ የበለጸገው ዓለም የደረሰበት የእድገት ላይ እንድትደርስ እንጂ እኔ ብቻ የሚል ሃሳብ ይዞ መንቀሳቀስ ብዙ ርቀት እንደማያስኬድ ጠቁመው ፤የመፍትሔ ሃሳቦች የሚገኙት አብሮ ከመኖር እንጂ ከመነጣጠል አለመሆኑ መታወቅ አለበት ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን ለራሳችንም ሆነ ለአገራችን የሚጠቅመን የነበረንን አብሮ የመኖር ባህል በማሳደግ አገራዊ አንድነትን ማስጠበቅ እንደሆነ የታመነ ነው።ብሔር እና ሃይማኖት ሳይለይ የሁላችንም ጠላት የሆነውን የጽንፈኝነት አስተሳሰብ በማስወገድ ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን በማጎልበት በይቅርታና በፍቅር ማንኛውንም ችግሮች በውይይት መፍታት ብልህነት ነው።በሃሳብ የበላይነት በማመን እና በማሳመን ተባብሮ በመስራት የአገር አለመረጋጋት ስጋት የሆነውን ጽንፈኝነት ማስወገድ ለነገ የማይባል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አቶ ጥላሁንና አቶ ተስፋሁን ይገልጻሉ።

ይህ ሳይሆን ቀርቶ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ እየገነገነ ከሄደ ግን እንደ ሀገር የምንመኘውን ዘላቂ ሰላምም ሆነ ልማት ማረጋገጥ ከዚያም ከፍ ሲል እንደአገር በጋራ ለመኖር የሚኖረን ተስፋ የመነመነ እንደሆነ የአዲስ ዘመን ሪፖርት ያስረዳል።

መዓዛ ማሞ

Exit mobile version