ETHIO12.COM

አርሰናል – ነዳጅ የጨረሰው አውቶሞቢል

አሁን ሁሉም ነገር አክትሟል። አርሰናል ጥሩ ሁለተኛ ሆኗል። ሲቲ ከአርሰናል ጉሮሮ ፈልቅቆ ዋንጫውን ወስዷል። ሲቲ ዋንጫ መውሰዱ ሳይሆን አስገራሚው የሚቀጥለው ዓመትስ ማን ይቀማዋል? የሚለው ጉዳይ ነው። ሪያል ማድሪድን እንደ ቀበና የሰፈር ቡድን እንዳይሆን አድርጎ ሲጨፍርበት ላየ፣ ሲቲን እንዴት ማቆም እንደሚቻል አሳብ ለመስጠት ይቸገራል። መጀመሪያ የአርሰናልን የመከነ ዕድል ለማሳየት ስለሲቲ አጭር ጉዳይ ላሳይ።

ሲቲ ጋርድዮላን ያስፈረመው 2016 ነው። ሲያስፈርመው ለተጨዋቾች ዝውውር በቂ ወይም ከበቂ በላይ በጀት ፈቅዶ ነበር። ያለፉት ሰባት ዓመታት በዚህ መልኩ የተገነባው ሲቲ ያለምንም ማጋነን ሁለት ብቁ ቡድን አለው። በቁ ሁለት ቡድን ብቻ ሳይሆን ተጨዋቾቹ አብረው የተላመዱ፣ ኳስን እንዳሻቸው የሚያብሱ አርቲስቶች ሆነዋል። በስፖርት ቋንቋ የኳስ ቆሌ ወይም ውቃቢ አምላክ ወርዶባቸዋል። በዚህ መንፈስ አስር ዋንጫዎችን ወስደዋል። አምስቱ የፕቲማየር ሊግ ዋንጫ ነው። five Premier League titles, four EFL Cups, and the FA Cup, including a domestic treble in the 2018–19 season. ገና ከፊቱ ደግሞ የሻምፒዮን ሊግ ድል ያለው ይመስላል።

እንግዲህ ይህ ቡድን አርሰናልን ልቆ ዋንጫ መውሰዱ ከአድናቆት በቀር ዜና የማይሆነው በዚህ ምክንያት ነው። በአጭሩ አርሰን ቬንገር ከለቀቁ በሁዋላ በዛሬው የአስቶን ቪላ አሰልጣኝ Unai Emery ኡናይ ኢምሪ አርሰናል ቀና ብሎ ነበር። ቀና ማለት ብቻ ሳይሆን በአሻናፊነት መንፈስ መስፍንጠር ጀምሮ መወያያ ክለብ ሆኖ ነበር። አንጋፋ ተጫዋቾች አሲረው አሰልጣኙ እንዲሰናበቱ አደረጉና አርቴታ መጣ። ይህን ያነሳሁት አርቴታ ክለቡ ውስጥ የነበሩትን ድማሚት አጽድቶ በወጣቶች ማስቀጠሉ አድናቆት የሚያሰጠው በመሆኑ ለማሳየት ብቻ ነው።

አርሰናልን በሃላፊነት ለመምራት የተረከበው አርቴታ ያለፈውን ዓመት አምስተኛ ሆኖ ጨርሶ በዘንድሮው ዓመት አስገራሚ ቡድን ቢገነባም፣ ቡድኑ ልክ እንደወትሮው ሁሉ ዓመት መገባደጃ ላይ ተስብሯል። ይህ የኖረ የአርሰናል ችግር የማይቀርፈው በበጀት ማነቆ ሳቢያ እንደ ሌሎች ቡድኖች ሁለት ቡድን ማዘጋጀት አለመቻሉ ነው። አርሰናል ሁሌም ጥሩ አስራ አንድ ተጨዋች አያጣም። ችግሩ ከነሱ መካከል በቅጣትና በጉዳት ሲጎድሉ የሚተካ አለመኖሩ ነው። በዚሁ ሳቢያ ዓመቱ መገባደጃ ላይ ተጨዋቾቹ ” ዝለት ወይም ፍቲግ” ይገጥማቸዋል። ሳካ፣ ኦዲጋርድ፣ ማርቲኔሊ፣ ፓርቲ፣ የመሳሰሉት ቁልፍ ተጫዋቾች አቋም የወረደው በዚሁ የአቅም መላሸቅ ምክንያት ነው። ሲያጠቁ ፍጥነታቸውና ከፍጥነታቸው ጋር ኳስን የሚያበሩበት መናበብ የከሰመው በዚህ ምክንያት እንጂ በሌላ አይደለም። እንደ ማንችስተር ዩናይትድ፣ ቼልሲ፣ ሊቨርፑል፣ የዘንድሮው ጦረኛ ቡድን ኒውካስትል፣ ሮተን ሃም ዓይነት ሁለት ቡድን ስኳድ ቢኖረው አርሰናል ይህን ዋንጫ ያጣ ነበር? መከራከሪያ አጀንዳ ነው!!

አርሰናል የዓመቱን ዋንጫ እንደማይወስድ ማሳየያዎች ብቅ ያሉት በፈብሩዋሪ ነው። በኤቨርተን ተሸነፈ። በብሬንትፎርድ ላይ ያስቆጠሩት ጎል ተሽሮባቸው ነጥብ ጣሉ። አፕሪል ሳካ ዌስት ሃም ላይ ፍጹም ቅጣት ምት ስቶ ነጥብ ጣሉ። የሚገርመው ዌስት ሃም ፔናሊቲ በተሳተ 140 ሰኮንድ ውስጥ ነው ጎል ያስቆጠረው። ሳካ ከዚያን ጊዜ በሁዋላ አቋሙ ወርዷል። የመሃል ሜዳው አቅም ከመቀነሱ ጋር ተዳምሮ በአቅም ዝለት የተፈተነው አጥቂው ክፍል ከገብሬል የሱስ ጉዳት ጋር አንድ ላይ የቀድሞ አይነት አቋም ሊኖረው አልቻለም። የሱስ ከተመለስም በሁዋላ ይህ ነው የሚባል ነገር ማሳየት አልቻለም። እዚህ ሁሉ ችግር ላይ ሳሊባ ተጎዳ። ጥብቅ የነበረው ተከላካይ ክፍሉ ተከፈተ። አርሰናልን የማይመጥኑ ተጠባባቂዎች ሲደናበሩ ማየት ግድ ሆነ። የአርቴታም ሆነ የክለቡ የጃንዋሪ ድንብታ ዋጋ አስከፈለ። በጃንዋሪ ቡድኑን በድንብ አጥብቀውት ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ባልሆነ።

በዚሁ መንገዳገድ የቀጠለው አርሰናል የመጨረሻዎቹን አምስት ጨዋታዎች አድርጎ ማግኘት ከሚገባው 15 ነጥብ ስድስት ብቻ ሲሰበስብ ሲቲ አስራ አምስቱንም አግኝቶ አናቱ ላይ ቂብ አለ። ሲቲ የተጨዋች ችግር ስለሌለበት በወሳኝ ቦታዎች ላይ ሽግሽግና የታክቲክ ለውጥ በማድረግ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎቹ ሲነድ አርሰናል እዚህ ግቡ በማይባሉ ቡድኖች ሳይቀር ነጥብ ጣለ።

ወደሁዋላ ያሉትን ጨዋታዎች ማስላቱ ለጊዜው ቢቀር እንኳን አርሰናል በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ያሳየው ብቃት ቡድኑ አቅሙ ማልቁን የሚያረጋግጡ ናቸው።

በብራይተን ሶስት ለአንድ የተሸነፈበት ጨዋታ የእረፍት መልስ እንቅስቃሴ ምንም ትነተና የማያስፈልገው የጉልበት ማነስ ነው። ሰፊ ሜዳ በማካለል ረገድ ያሉ መረጃዎችና ዳታዎችም የሚመሰክሩት ይህንኑ ነው። ሲቋጭ አርሰናል ሄዶ ሄዶ የቆመው ነዳጅ ጨርሶ እንደሆነ ማመን ግድ ነው። ከዚ አንጻር በሁለት ታላላቅ መመዘኛዎች አርሰናል አይወቀስም። እንደውም ትልቅ ውጤት ነው።

ቁጥር አንድ አርሰናል የያዘው ስኳድ ዋንጫ ድረስ የሚያዘልቅ አይደለም። ለምሳሌ ከሊዘርፑል ስኳድ ጋር ሲነጻጸር፣ ከዩናይትድና ከቼልሲ ጋር ሲመዛዘን፣ ከኒውካስትልና ቶተንሃም ጋር ሲወዳደር አንሶ የሚታይ ነው። አርሰናል ቡድኑ በወጣቶች የተገነባ እንደመሆኑ ጫና መቋቋምም አይችልም። ይህ ሁለተኛው ምክንያት ሚዛን ይደፋል። ሲቲ ሲቀርባቸው ልምድ የሌላቸውና በዋንጫ ጉጉት ውስጥ የነበሩት የአርሰናል ወጣቶች በስነልቦና ተጎድተዋል። ከላይ እንደተባለው ቡድኑ አቅም መጨረሱ ያስከተለው በሽታ፣ ከመጨረሻዎቹ የውጥረት ጨዋታዎች ውጤት ጋር ተዳምሮ ለኪሳራ ዳርጎታል።

በግል እየታዬ አርሰናል የመጨረሻዎቹን ጨዋታዎች ነዳጅ ጨርሶ በግፊ እንደሚሄድ አውቶሞቢል እመስለዋለሁ። በግፊ ሄዶ ሁለተኛ በመውጣቱ ደግሞ እጅግ አደንቀዋለሁ። ከአርቴታ የተሻለ ስብስብና ተተኪ የመቅመጫ ተረኞች ያሰብሳሰቡ ቡድኖች ሲያነክሱ አርሰናል ባነሰ ስኳድ ይህን ውጤት ማስመዘገቡ ከትችት ይልቅ አድናቆት ሊቀድመለት ይገባል ባይ ነኝ። አርሰናልን ሌላ ሃብታም በገዛው ስል የምመኘውም ለዚህ ነው። አርሰናል ተጠባባቂ የለውም ማለት የሚቻል ቡድን ነው። ይህ ቡድን እንዴት ብሎ የሚቀጥለው ዓመት ሻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ መፎካከር የሚችለው? ስጋቴ ነው።

አርሰናል አዳዲስ ተጨዋቾችን እንደሚያስፈርም መረጃዎች እየወጡ ነው። ሁሌም መረጃዎች ይወጣሉ። ግና ከሚሰሙት መረጃዎች ውስጥ የሚሆኑት እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። የሚሆነውን ጠብቆ ማየት ነው። ኒውካስትል ኔይማርን ሊጠቀልል ተቃርቧል። በኒውካስትል ጉልበተኞች መካከል ኔይማር ቢገባ ምን ቡድኑን እንዴት ውበት እንደሚሰጠው አስቡት።

ለሁሉም በቁጭትም ቢሆን አርሰናልንና አርቴታን አለማድነቅ ነውር ይሆናልና አድናቆት ግድ ነው። ቡድኑ በተዋቀረበት ልክ፣ በፈሰሰበት መጠን ሄዷል። አቅም ሶያልቅ አለቀ ነው። አርቴታ እንዳለው ስብራቱ ከባድ ነው። ጉዳቱ ክፉ ነው። “ይህ እግር ኳስ ነው። በጣም አሳዛኝ ቀን ነው ለእኛ። ለ11 ወራት ዓላማ ይዘን ስንሠራ ነበር። በሊጉ አናት ላይ ለበርካታ ወራት ከርመናል። አጠናቀናል ግን የሠራነው በቂ አይደለም”

“አሁን ማገገም አለብን። በጣም ከባድ ነው። ተጫዋቾቼን ለማነሳሳት እሞክራለሁ። ከባድ ሳምንት ነው የሚጠብቀን።” ምንም እንኳ ማንቸስተር ሲቲ ያለፉት 11 የሊግ ጨዋታዎችን ቢያሸንፍም “ጥፋቱ የራሳችን ነው” ግብ ጠባቂው ራምስዴል ገልጿል። “ካለፉት ስድስት የውድድር ዘመኖች አንድ ቡድን ብቻ ነው ሲቲን በልጦ የተገኘው። ወጣም ወረደ ጥፋቱ የራሳችን ነው። ማሸነፍ የሚገባንን ፍልሚያ በግለሰብ ጥፋት ሳናሸንፍ ቀርተናል።” ሲልም አክሏል። ያው ሲያልቅ መውቃቀሱ የተለመደ ቢሆንም አርቴታ እንዳለው ማገገሙ ለአርሰናል ታላቅ ፈተና ነው።

Exit mobile version