Site icon ETHIO12.COM

ለረዥም ጊዜ ሳንጠቀምባቸው የቆዩ የጎግል አካውንቶች ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገለጸ

ጎግል አዲስ ባሻሻለው ፖሊሲ መሰረት ለረዥም ጊዜ እንቅስቃሴ ለማይታይባቸው (Inactive accounts) የግል የጎግል አካውንቶች የሚሰጠው የጊዜ ርዝማኔ ቢበዛ ለሁለት ዓመት ብቻ እንደሆነ አሳውቋል፡፡

ጎግል የፖሊሲ ለውጡ የመስመር ላይ ደህንነትን ለማሻሻል ያለመ እንደሆነ ተናግሯል::
ለረዥም ጊዜ ሳይንቀሳቀሱ የቆዩ አካውንቶች ለሳይበር ጥቃት ዒላማ ስለሚሆኑ፣ በተለይም ደካማና ያልዘመኑ የይለፍ ቃሎች ስለሚኖሯቸው እና ምንም ተጨማሪ የደህንነት ማዘመኛ ስለማይደረግላቸው ለጥቃት አጋላጭ እንደሚሆኑ ተነግሯል።

የሁለት ዓመት ጊዜው ካለፈ በኋላ መለያዎቹ ከሁሉም ይዘታቸው፣ ቅንብሮቻቸው፣ ምርጫዎቻቸው እና በተጠቃሚው የተቀመጡ ውሂቦች ሊሰረዙ ይችላሉ።

ይህ እንደ ጂ ሜይል፣ ዶክመንቶች፣ ፎቶዎች፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ዩቲብ እና ከሌሎች የጎግል አገልግሎቶች ላይ የተከማቹ ፋይሎችን (Gmail፣ Docs፣ Drive፣ Meet፣ Calendar፣ Google Photos and YouTube) ማጥፋትን ያካትታል።

ሆኖም ይህ አዲስ መመሪያ እንደ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች ተቋማት የጎግል አካውንቶች ላይ ተፈጻሚ አይሆንም።

ከያዝነው የፈረንጆቹ 2023 ዓ/ም ጀምሮ የጎግል አካውንቶች ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ጥቅም ላይ ካልዋሉ ወይም የአካውንቱ ባለቤት ካልጎበኛቸው መለያውን/አካውንቱን ከነይዘቱ ሊሰርዝ እንደሚችል የጎግል የምርት አስተዳደር ምክትል ኃላፊ የሆኑት ሩት ክሪችሊ ገልጸዋል።

የጎግል ካምፓኒ የውስጥ ጥናት እንደሚያሳየው ሳይንቀሳቀሱ የቆዩ አካውንቶችን ባለ ሁለት ደረጃ ማረጋገጫን (two-factor authentication) የማዋቀር ዕድላቸው እንቅስቃሴ ከሚታይባቸው (active account) በትንሹ በአስር እጥፍ ያነሱ ናቸው። ይህም እነዚህን አካውንቶች ለአደጋ የተጋለጡ ያደርጋቸዋል፡፡

አንድ አካውንት ከተሰበረ ደግሞ፣ ከማንነት ስርቆት እስከ ተንኮል አዘል ወይም ለተበከሉ ይዘቶች ማስተላለፊያነት መጠቀሚያ ሊሆን ይችላል።

የጉግል አዲሱ መመሪያ በታህሳስ 2023 እ. አ. አ. የእንቅስቃሴ-አልባነት ገደብ ላይ የደረሱትን የጎግል አካውንቶች በማጥፋት ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ይህ ከመሆኑ ከወራት በፊት ለአካውንቶቹ ባለቤቶች ብዙ ማስጠንቀቂያዎች እንዲደርሳቸው እንደሚደረግ ተገልጿል።

Exit mobile version