Site icon ETHIO12.COM

ዓባይ ከግብጽ እስከ አረብ ሊግ!

ከሳምንት በፊት “ኢትዮጵያ አራተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት በቅርቡ ትጀምራለች፤ አሁንም አቤቱታችሁን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ልትወስዱት ትችላላችሁ?” የሚል ጥያቄ በጋዜጠኞች የቀረበላቸው የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ የሰጡት ምላሽ የአረብ ሊግ የአቋም መግለጫን ቀድሞ ያመላከተ ነበር፡፡ “ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ” እንደሚባለው ከስብሰባው በፊት የአቋም መግለጫውን የስብሰባው ዘዋሪዎች ለዓለም ሕዝብ ጆሮ አደረሱት፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሽኩሪ በምላሻቸው “እስከአሁን አቤቱታችንን ከጸጥታው ምክር ቤት እስከ አፍሪካ ኅብረት አቅርበን የተለየ ነገር አልመጣም፡፡ በተደጋጋሚ መንገድ መሄድ ሳይኾን ጉዳዩን አቅጣጫ ቀይሮ መመልከት ተገቢ ነው፡፡ የግድቡን የውኃ ሙሌት በተመለከተ ግብጽ ጉዳዩን ወደ አረብ ሊግ ትወስደዋለች” ሲሉ ተደመጡ፡፡ እንደ እውነቱ ከኾነ በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ የተካሄደው 32ኛው የአረብ ሊግ ስብሰባ ከወትሮው የተለየ እና ትኩረት የሚሹ የመወያያ አንገብጋቢ ነጥቦች ነበሩት፡፡

የአረብ ሊግ እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር መጋቢት 22/1945 ሲመሰረት ከመሥራቾቹ ሰባት ሀገራት መካከል አንዷ የኾነችው የበሽር አላሳዷ ሀገር ሶሪያ ከ12 ዓመታት በኋላ በተመለሰችበት ስብሰባ ከኢትዮጵያ የተሻገረ የአባል ሀገራቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ነበሩባቸው፡፡ የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት እና በጦርነት የተጎዳችውን ሶሪያን ከማቋቋም በላይ በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ አቋም መያዝ ከሊጉ ጀርባ የስብሰባው ዘዋሪዎች እነማን እንደነበሩ በግልጽ አመላካች ኾኖ ታይቷል፡፡

ላለፉት ሦስት ዓመታት በሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ዙሪያ ከካይሮ ጋር የወገነችው ካርቱም በሁለቱ ጀኔራሎቿ እልኽ አስጨራሽ ጦርነት ድምጿ ጠፍቷል፡፡ በጦርነቱ ዋዜማ እንዴት እና ለምን ሱዳን ውስጥ እንደተገኙ እስካሁንም ድረስ ምክንያቱ ግልጽ ያልኾነው የግብጽ ወታደሮች ጉዳይ ለሱዳን ሕዝብ የእግር እሳት በኾነበት በዚህ ወቅት ግብጽ በውኃ ሙሌቱ ዙሪያ ሱዳንም ተመሳሳይ አቤቱታ እንዳላት ሳዑዲ አረቢያ ጅዳ ተገኝታ ጉዳይ ፈጻሚ መኾኗን አረጋገጠች፡፡ ይህ ሁሉ ተሰባስቦ የዓባይ ጉዳይ ከግብጽ እስከ አረብ ሊግ ውስብስብ እጆች እንዳረፉበት አመላካች ነው ይላሉ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር አደም ካሚል፡፡

ግንባር ቀደም ጉዳይ አስፈጻሚዎቹ እና ዋና ጽሕፈት ቤቱ ካይሮ ላይ ከተቀመጠ ሊግ ከዚህ የተለየ አቋም መጠበቅ “በተኩላ ዘመን በግ መኾን” ነው ያሉት ፕሮፌሰር አደም ሳዑዲ አረቢያም የዓባይን ጉዳይ የአረቡ ዓለም ጉዳይ ለማድረግ በቅርቡ የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የሊጉ አቋም ቅድመ ምልክቶች ነበሩ ይላሉ፡፡ በሳዑዲ አረቢያው የሊጉ ስብሰባ የሕዳሴ ግድቡን በሚመለከት የታየው አቋም ከወትሮው ያልተለየ እና መሻሻል ያልታየበት ነውም ብለዋል፡፡

“የግብጽ የውኃ አቅርቦት ጉዳይ የአረብ ሊግ ሀገራት የፀጥታ ስጋት ጉዳይ ነው” የሚለው የሊጉ ወቅታዊ አቋም የሳዑዲ አረቢያን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር አደም ምክንያቱን ሲያነሱም ሳዑዲ አረቢያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግብጽ እና ሱዳን ከፍተኛ የእርሻ ኢንቨስትመንት ማስፋፋቷን ተከትሎ የቀረበ ስጋት ነው ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ በየጊዜው “አልቀበለውም” ከሚል ምላሽ ወጥታ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን በጥናት እና በውጤት ተመስርታ መሥራት እንደሚኖርባትም አስገንዝበዋል፡፡ በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጎላ የመጣው የፐብሊክ እና ዲጂታል ዲፕሎማሲ ለግብጽ ሴራ ፍቱን መድኃኒት እንደኾነም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው ባሕር ዳር ፡ (አሚኮ)

Exit mobile version