Site icon ETHIO12.COM

“ግብጽ የአረብ ሊግ መሪነቷን በመጠቀም የዓባይ ግድብ ላይ ያላትን ኢፍትሃዊ ፍላጎት ለማሳካት እየሞከረች ነው”

ግብጽ የአረብ ሊግ መሪነቷን በመጠቀም በዓባይ ግድብ ላይ ያላትን ኢፍትሃዊ ፍላጎት ለማሳካት እየሞከረች መሆኑን የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪና የዓባይ ግድብ ዓለም አቀፍ ተደራዳሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአረብ ሊግ መግለጫ የሰጠው ምላሽ የዓለምአቀፍ ማህበረሰቡ እውነታውን እንዲረዳ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የአረብ ሊግ መግለጫ ለግብጽ መወገኑ የመጀመሪያው ሳይሆን በተከታታይ አመታትም የታየ ነው። ግብጽ የአረብ ሊግ መሥራችና መሪ ናት። ሊጉን እንደ መሣሪያ በመጠቀምም ፍላጎቷን ለማስፈጸም በተደጋጋሚ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። ይህም ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር በየአመቱ የሚከናወነውን የውሃ ሙሌት በማደናቀፍ የግድቡ ሥራ እንዳይጠናቀቅ ካላት ፍላጎት የሚመነጨ ነው።

እንደ ዶክተር ያዕቆብ ገለጻ፤ ግብጽ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ሲደረግ በነበረው የግድቡ ድርድር ላይ እግሯን እየጎተተች ቆይታለች። ይህም የሆነበት ምክንያት በአፍሪካ ህብረት መድረክ ላይ የሚካሄደው ድርድርና ውይይት ለምታደርገው ኢ-ፍትሃዊ ጥያቄ አመቺ ባለመሆኑና የሚፈልጉትን ኢፍትሃዊ የሆኑ መስመሮችን ማግኘት ስለማትችል ነው። ‹‹ሙሉ ሀሳቧን ዘመዶቼና ወገኖቼ ናቸው፤ በእኔ ተፅዕኖ ስር ናቸው በምትላቸው የአረብ ሊግ ላይ አተኩራለች›› ብለዋል።

ትክክለኛ ፍትህ ባለበት በአፍሪካ መድረክ ስር ኢፍትሃዊ ፍላጎቷን ማሳካት ስለማትችል ሀሳቧን ወደምትጭንበት የአረብ ሊግ መውሰዷ የመጀመሪያ ሳይሆን ተደጋጋሚ ሙከራ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ያዕቆብ፣ የዓባይ ጉዳይ የተፋሰሱ አገራት ጉዳይ ቢሆንም ግብጽ ብቸኛ የወንዙ ባለቤት ሆና ለመምጣት የምታደርገው እንቅስቃሴ የቆየና የረጅም ጊዜ ፍላጎቷ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህም ውሃውን በብቸኝነት ስትጠቀም የቆየችበትን ልምዷን ለማስቀጠል መሆኑንና በብቸኝነት መጠቀም አለብኝ የሚል እሳቤ በመያዝ እንጂ የተፋሰሱ ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ ስለሆነ ብቸኛ ባለቤት የምትሆንበት ምክንያታዊ መሠረት የላትም ብለዋል።

ግብጽን ጨምሮ የተፋሰሱን አገራት ፍላጎት በሚገባ በመገንዘብ ፍትሃዊ የውሃ ሀብትን ለመጠቀም ኢትዮጵያ ጠንካራ አቋምና ፍላጎት አላት ያሉት ተደራዳሪው፤ የዓባይ ግድብ ለኢትዮጵያ መልማት መልስ የሚሰጥ ጠቃሚ ፕሮጀክት ነው፤ ነገር ግን በግብጽ የሚዘወረው የአረብ ሊግ መግለጫ ግብጽ መሪነቷን በመጠቀም ኢፍትሃዊ ፍላጎቷን ለማሳካት የምታከናውነው ቀቢጸ ተስፋ ፍላጎት ነው ብለዋል።

እንደ ተደራዳሪው ገለጻ፤ ግብጽ የኢትዮጵያ የውሃ አጠቃቀም በዚህ ከቀጠለ የእኔ ብቻ ነው የምትለው አቋምና ፍላጎቷ የሚቋረጥ መሆኑን ስለተረዳች ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ መቃወም ትፈልጋለች። በዚህም የግብጽ መወራጨት ኢፍትሐዊ የሆነ ፍላጎትን ለማስጠበቅ ከመፈለጓ የሚመነጭ ነው። እስካሁን ድረስ ሦስት ጊዜ የውሃ ሙሌት ተከናውኗል። ለአራተኛው ሙሌትም ዝግጅቱ ተጠናቋል። ከዚህ በኋላም ኢትዮጵያን በውሃ ሙሌቱ ዙሪያ አስገዳጅ የሆነ ስምምነት እንድትፈርም የሚያደርግ ሁኔታ አይፈጠርም። ስለዚህ ሙሌቱ ከማንኛውም የውጭ ኃይል ተፅዕኖና ክልከላ ውጪ በቀጣይም ይከናወናል ሲሉም ተናግረዋል።

በዲፕሎማሲው የተጀመውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ያሉት ዶክተር ያዕቆብ፤ አረብ ሊግ ከንቱ ድካም ላይ ነው። ኢትዮጵያ ማናቸውንም የውጭ ኃይል ፍላጎትና ጥቅም በአጎብዳጅነት የምትፈጸም ሳይሆን የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችል የዲፕሎማሲ ሥራዋን አጠናክራ መቀጠል አለባት። ግብጽ የያዘችውን ለብቻ የመጠቀም ፍላጎት ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የማስረዳትና የማሳወቅ ሥራን አጠናክራ ልትቀጥልበት ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ባላት የውሃና ሌላ የተፈጥሮ ሀብቷ ላይ አቅዳ፣ አስባና አልማ በጥንቃቄ የመጠቀም መብትን መቀጠል አለባት። ውሃን ጨምሮ በድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች ላይ ስትጠቀም ሌሎችን እንዳይጎዳ እያረጋገጠች በእቅዷ መሠረት እንድምትቀጥል ተስፋ አለኝ። ይህንን መብት የሚከለክል የግብጽም ሆነ የሌሎች ወዳጅ ወገኖቿ ጫና ተፈጻሚነት ሊኖር አይገባም ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአረብ ሊግ መግለጫ የሰጠው ምላሽ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን እንዲረዳና በሚዛናዊ መንገድ እንዲመለከት የሚያደርግ ነው። ኢትዮጵያ ከአረብ ሊግ ጋር በጥቅሉ ከምታደርገው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አንጻር እንዲያዩትና ለሊጉ አባል አገራት በግልም ሆነ በተናጠል ለወዳጅነትና ለትብብር በሯ ክፍት እንደሆነ እንዲገነዘቡ፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረር ውሳኔም ትክክል አለመሆኑን እንዲገነዘቡ የሚያስችል መሆኑን ዶክተር ያዕቆብ ጠቁመዋል።

በሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2015

Exit mobile version