Site icon ETHIO12.COM

መከላከያ በስንዴ ምርት ራሱን ለመቻል እርሻ ጀመረ

የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ የሀገር የልማት ደጋፊ ለመሆን በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል ከፍተኛ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ። ኣላማው መከላከያ ወደ ምርት ስራ ገብቶ ለራሱ የሚሆን ፍጆታ ለማምረት ነው፡፡

በዋና መምሪያው ለልማት የተዘጋጀውን የእርሻ ቦታ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣ የመከላከያ ፋይናንስ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሊዊጂ፣ ጄኔራል መኮንኖች ፣ የሠራዊቱ አመራሮችና አባላት ምልከታ አድርገዋል፡፡

የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ÷ ዋና መምሪያው ባለፈው የህግ ማስከበር ዘመቻ በተለያዩ ቀጠናዎች በመዘዋወር ለሠራዊቱ የግዳጅ አፈፃፀም አይነተኛ ሚና ያላቸውን እንደ ቀለብ፣ ተተኳሽ፣ አልባሳት እና ተሽከርካሪዎችን በማቅረብ ችግር ፈቺነቱን በተግባር ሲያረጋግጥ የመጣ ጠንካራ መምሪያ መሆኑን ገልፀዋል።

ዋና መምሪያው አሁን ላይ ፊቱን ወደ ልማት እና ወደ ፈጠራ በማዞር በባለቤትነት ስሜት እያከናወነ ሥላለው ተግባር መከላከያ አድናቆት አለው ብለዋል።

የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ሀላፊ ሌተናል ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል ስንዴን በሀገራችን ውስጥ ለማምረት በተነደፈው የልማት ፓሊሲ መሠረት ለተቋሙ የተቀመጠውን አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የተቋሙን እና የሀገርን ልማት ለመደገፍ እንዲሁም ሠራዊቱ የልማት ሀይል መሆኑን ለማረጋገጥ በይዞታው ውስጥ የሚገኘውን ከ30 ሄክታር በላይ የእርሻ ቦታ በሰራዊቱ ጉልበትና እገዛ ለልማት ዝግጁ ማድረግ ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ ተግባር የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ እና ሰራዊቱ ጠባቂ ከመሆን አልፎ በስንዴ ምርት እራሡን እንዲመግብ ትኩረት ተሠጥቶት እየተሠራ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ከመከላከያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version