Site icon ETHIO12.COM

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርገውን ሕግ በፊርማቸው አጸደቁ

ምዕራባውያን አገራት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቢያወግዙትም የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ አነጋጋሪ የሆነውን የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርገውን ሕግ በፊርማቸው አጸደቁ። ረቂቅ ሕጉ መጋቢት ወር ላይ በአገሪቱ ምክር ቤት አባላት ተቀባይንት ያገኘ ሲሆን፣ ማሻሻያ እንዲደረግበት ለፓርላማው ተመልሶ ቀርቦ ነበር።

ቀደም ሲል ቀርቦ በነበረው ረቂቅ ሕግ ላይ ማንኛውም ራሱን በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት አፍቃሪነት የመደበ፣ ወይም የጾታ ለውጥ ያስደረገ እንዲሁም ከዚሁ ጋር በተያያዘው ዝርዝር ውስጥ የሚካተት የጾታ ዝንባሌ ያለው ዜጋን ሁሉ ወንጀለኛ የሚያደርግ ነበር። ሆኖም ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ይህ ሰዎች እንዲታሰሩ እና በአካላዊ ገጽታቸው ብቻ እንዲከሰሱ ያደርጋል ሲሉ ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

በመሆኑም ፕሬዝዳንቱ ረቂቅ ሕጉ እንዲሻሻል ወደ ፓርላማ መልሰውት ነበር። በዚህ መሠረት ተሻሽሎ አሁን ላይ የቀረበው ረቂቅ ሕግ፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ወንጀልነት ወንድ ከወንድ ጋር በሚያደርገው ወሲባዊ ድርጊቶች ላይ የተወሰነ ሆኗል። ይህንን ሕግ ተላልፈው የተገኙም እስከ እድሜ ልክ እስራት ይጠብቃቸዋል።

ለከባድ ወንጀሎች ማለትም ወሲባዊ ጥቃቱ በሕጻናት ላይ፣ በአካል ጉዳተኛ እንዲሁም ተጋላጭ በሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ በሚፈፀምበት ጊዜ አሊያም የጥቃት ሰለባዎቹ ለዕድሜ ልክ ህመም የሚዳረጉ ከሆነ በድርጊቱ ፈፃሚ ላይ የሞት ቅጣትን ይደነግጋል።

ማኅበረሰቡም በሕጻናት ወይም በሌሎች ተጋላጭ በሆኑ የሕብረተሰቡ አባላት ላይ ማንኛውንም ዓይነት የተመሳሳይ ጾታ ጥቃት በሚያዩ፣ በሚሰሙ ጊዜ ለባለሥልጣናት ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።

ግሎባል ፈንድ፣ የአሜሪካ መንግሥት የፕሬዝዳንት የአስቸኳይ ጊዜ የኤድስ ድጋፍ ዕቅድ (ፔፕፋር) እና ዩኤንኤድስ አዲሱን ሕግ ተከትሎ በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ በሰጡት ምላሽ፣ ጎጂ ተፅዕኖ ያስከትላል በሚል ጉዳዩ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

ተቋማቱ ጨምረውም ሕጉ የጤና ትምህርት ለመስጠት እና የኤድስ ሥርጭትን ለመከላከል የሚሰራውን ሥራ እንደሚያደናቅፍ ገልጸው፣ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሚካተት የጾታ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎችም ለደኅንነታቸው ያላቸው ስጋት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል። በርካቶችም ጠቃሚ የጤና አግልግሎቶች እንዳያገኙ እየተበረታቱ አለመሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል። ሕጉ በፍርድ ቤት ክርክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

እንደ አውሮፓውያኑ 2014 የወጣ ተመሳሳይ ሕግ በኡጋንዳ የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጎ ነበር። ያን ጊዜ የሕገ መንግሥቱ ፍርድ ቤት ረቂቁን ውድቅ ያደረገው ፓርላማው ይህን ሲያጸድቅ የተሟሉ አባላት ባልተገኙበት ነበር በሚል ነበር። የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ምዕራባውያን አገራት የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን መብቶች በአፍሪካ አገራት ላይ በኃይል ለመጫን እየጣሩ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ። የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ከ30 በሚበልጡ የአፍሪካ አገራት ክልክል አሊያም ወንጀል ተደርጎ ተደንግጓል።

ቢቢሲ አማርኛ

Exit mobile version