‹‹የኤች.አር 6600 ረቂቅ ሕግ በሕዝቡ ዘንድ ተገቢ መረጃ እንዳይገኝ እንቅፋት ይሆናል ›› ዳንኤል በቀለ (ዶክተር)

በአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የቀረበው የኤች.አር 6600 ረቂቅ ሕግ ኮሚሽኑ ከመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ጋር በጣምራ የጀመረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶክተር) አመለከቱ። ረቂቅ ሕጉ በሕዝቡ ዘንድ ተገቢ መረጃ እንዳይገኝ እንቅፋት ይሆናል ብለዋል።

ጉዳዩን በገለልተኝነት መርምሮ የተጠያቂነት ስርዓት ለማስፈን በአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የቀረበው የኤች.አር 6600 ረቂቅ ሕግ በሕዝቡ ዘንድ ተገቢ መረጃ እንዳይገኝ እንቅፋት ይሆናል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ከለላ የሚደረገው ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ የማዕቀብ ሀሳብ የያዘው ረቂቅ ሕግ በተለይ ሴቶችና ህጻናትን ክፉኛ ይጎዳል። ይህም ለኢትዮጵያ አዎንታዊ መፍትሄ እንደማያመጣ አስገንዝበዋል።

ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶክተር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከተከሰተው ጦርነት ጋር ተያይዞ በተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመሆን ሰፊ ምርመራ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል።

ይህን መሰረት አድርጎ ከሁሉም ወገኖች የተጠያቂነት ስርዓት እንዲሰፍን እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት ወቅት በአሜሪካ ውስን የኮንግረስ አባላት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳው ኤች. አር 6600 ረቂቅ ሕግ መዘጋጀት ሂደቱ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚኖረው ጉዳዩ እንደገና ሊጤን ይገባዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተወሰነ መልኩ መሻሻል ቢያሳይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጦርነቱና በመሰል ውስብስብ የፖለቲካ ችግሮች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተበራክተዋል ያሉት ዶክተር ዳንኤል፤ በተለይ በአማራና በአፋር ክልሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

ጉዳዩን በገለልተኝነት መርምሮ የተጠያቂነት ስርዓት ለማስፈን በአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የቀረበው የኤች.አር 6600 ረቂቅ ሕግ በሕዝቡ ዘንድ ተገቢ መረጃ እንዳይገኝ እንቅፋት ይሆናል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ከለላ የሚደረገው ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ የማዕቀብ ሀሳብ የያዘው ረቂቅ ሕግ በተለይ ሴቶችና ህጻናትን ክፉኛ ይጎዳል። ይህም ለኢትዮጵያ አዎንታዊ መፍትሄ እንደማያመጣ አስገንዝበዋል።

የተፈጠረ ችግር ቢኖርም ጉዳዩን በሚመለከታቸው የአገሪቱ ተቋማት መታየት ሲገባው በኢትዮጵያ ጉዳይ በቀጥታ ጣልቃ ለመግባት የሚደርገው ጥረት ሌላ ቀውስን የሚያመጣ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ አሁን በኮንግረስ አባላት የቀረበው ረቂቅ ሕግ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን የዓለም አቀፍ ሕጎች መርህን ያልተከተለ የጣልቃ ገብነት ጫናና የሰብዓዊ መብት ሕጎችን የሚጠስ ነው ብለዋል።

ይህ ሲባል በሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ አገራት አይመለከታቸውም ማለት እንዳልሆነም ተናግረዋል።

በአሜሪካ የኮንግረስ አባላት የረቀቀው የኤች.አር 6600 ረቂቅ ሕግ ከዚህ በፊት በኢራን፣ በሱዳንና በኩባ ላይ ተጥሎ እንደነበር ያስታወሱት ኮሚሽነር ዳንኤል፤ በእነዚህ አገሮች ያስከተለው ሁለንተናዊ ቀውስ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በጦርነቱ ምክንያት የተፈጸሙትን የመብት ጥሰቶች በተመለከተ ኮሚሽኑ ከተመድ ጋር ባደረገው ምርመራ ያስቀመጣቸውን ምክረ ሃሳቦችን ተቀብሎ የተጠያቂነት ስርዓት ለማስፈን እንቅስቃሴ ላይ ባለበት ወቅት ማዕቀብ እንዲጣል ማሰብ የወደፊቱን የተጠያቂነት ስርዓትም ሆነ የመረጃ አሰባሰብ ሂደት ላይ ጫና ያሳድራል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በተጨባጭ በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የመግለጽ ሥራ ቀደም ሲል እንደጀመረው ሁሉ አሁንም በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ለሚሠሩት አካላት ጫናውን የማሳወቅ ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኢትዮጵያን በተመለከተ በአሜሪካን የኮንግረስ አባላት የተዘጋጀው ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላገናዘበ መሆኑን ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በአሜሪካ የሚኖሩ የተለያዩ የኢትዮጵያውያን አደረጃጀቶችና የዲያስፖራ አባላት ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡ ኢትዮጵያ ለሰላም የዘረጋችውን እጅ ከግንዛቤ ያላስገባ እንደሆነ እየተቹት ይገኛሉ።

በዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2014

Leave a Reply