Site icon ETHIO12.COM

ሟችን በጭፈራ የሚሸኘው ማህበረሰን

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኮንሶ ዞን ውስጥ ተወልደው ያደጉት ዶ/ር ኦንጋዬ ኦዳታ በቅርቡ ነው አያታቸውን በሞት ያጡት።

የሚወዷቸው አያታቸው ቀብር የተፈፀመው ግን ወዳጅ ዘመድ ተሰብስቦ ዘፍኖ እና ጨፍሮ በተከናወነ ሥነ ሥርዓነት መሆኑን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ሞት በሁሉም ዘንድ ሁሌም አዲስ ነው። በመጣ ቁጥር የሚያስደነግጥ በብዙ ማኅበረሰቦች ዘንድም ማቅ የሚያስለብስ እና እንባ የሚያራጭ ክስተት ነው።

ሟችን ለመሰናበትም ሆነ ቤተሰቡን ለማጽናናት የሚሰበሰበውም ሐዘኑን የሚገልጸው እንባውን እያፈሰሰ፣ ደረቱን እየደቃ ነው።

በአንዳንድ አካባቢ ዘመድ የሞተባቸው ቤተሰቦች ጥቁር መልበስ፣ ፀጉር መላጨት እና ወትሮ ሲፈጽሙት ከነበሩ የደስታ ድርጊቶች መታቀብ የተለመደ ነው።

በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የኮንሶ ማኅበረሰብ ግን ሰው በሚሞትበት ሰዓት በዘፈን እና በጭፈራ በደስታ የሚሸኝበት ባህል አለው።

ይህም ባህልም “ሺሌታ” ይባላል።

በሺሌታ ባሕል አባቱ አልያም እናቱ የሞቱበት ልጅ በዘፈን እና በጭፈራ ይሸኛቸዋል። ዶ/ር ኦንጋዬም ያደረጉት ይህንኑ ነው።

በዲላ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ኦንጋዬ “ሰው ሲሞት በዘፈን እና በጭፈራ የሚሸኝበት ባሕልን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ወላጅ የሞተባቸው ልጆችም መጨፈራቸው ነው” ይላሉ።

የሞተ ሰው በዘፈን የሚሸኘው መቼ ነው?

የኮንሶ ብሔረሰብ ማኅበራዊ ትስስሩን ከሚያጠነክርባቸው እና ኢኮኖሚያዊ አቅሙን ከሚገልጥባቸው ባህላዊ ክዋኔዎቹ መካከል “የለቅሶ ሥርዓት” ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

ባህላዊው የለቅሶ ሥርዓት የብሔረሰቡ ልዩ ልዩ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች የሚገለጡበት፣ የሚፀኑበት እና ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉበት ሁነኛ መድረክ ነው።

ዶ/ር ኦንጋይ ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ናቸው። ራሳቸውም ሁለት ልጆችን ወልደዋል። አባታቸው አሁንም በሕይወት አሉ።

ዶ/ር ኦንጋይ እንደሚሉት የሞተ ሰው አስከሬን ወደ ሚቀበርበት በሚወሰድበት ጊዜ በዘፈን እና ጭፈራ ታጅቦ ይሸኛል።

ከቀብር ሥነ ሥርዓቱም በኋላ ዘፈኑ ይቀጥላል።

በዚህ የዘፈን ስንኞች ውስጥም ስለሞተው ሰው ደግነት፣ በሕይወት ሳለ ስላከናወናቸው መልካም ሥራዎች በማንሳት ይወደሳል፤ የትውልድ ዘር ሐረጉም ተቆጥሮ ይዘከራል።

በዘፈን የሚሸኙ ሰዎችም፣ “የተመረቁ ሰዎች ናቸው” ተብሎ ይታመናል።

እነዚያም ዘፈኖች የተለያየ ግጥም አላቸው።

ይሁን እንጂ ዘፈኑ የሚዘፈንበት ቆይታ የተለያየ ነው።

የኮንሶ ማኅበረሰብ ሕይወት ከእርሻ ገር የተያያዘ በመሆኑ፣ እርሻ በሚታረስበት ወቅት የሞተ ሰው የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ የዘፈን ሥርዓቱ አመቺ ነው ወደሚባሉት ብራ ወራት [መስከረም ወይም ጥቅምት] እንዲሆን ይደረጋል።

አረም በሚታረምበት ወቅት ለሞተ ሰው ደግሞ የዘፈኑ ጊዜ ለጊዜው እንዲቆይ ይደረጋል።

ለሞተ ሰው የሚዘፈነው ዘፈን ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉም “ሀራና” በመባል ይታወቃል።

ከዚያ በኋላ የዘፈን ቀን ይወሰን እና ለአካባቢው ሰዎች ይነገራል።

በመጀመሪያም በአካባቢው ለሚገኙ መንደርተኞች፣ ቀጥሎም፣ የኮንሶ ጎሳ ለሆኑ በርቀት ለሚኖሩ ይነገራል።

በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው ርቀት ያሉ ሰዎች የዘፈን ሥነ ሥርዓቱ ላይ ነጥተው የሚሳተፉት።

በሺሌታ ባህል ለመሸኘት መስፈርቶቹ ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ኦንጋይ አንደሚሉት፣ እንደ ኮንሶ ባህል አንድን ሰው በዘፈን እና በጭፈራ ለመሸኘት ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች አሉ።

በቅርቡ የሞቱት አያታቸው ይህንኑ መስፈርት ስለሚያሟሉ በዘፈን፣ በደስታ እና በጭፈራ መሸኘታቸውን ይናገራሉ።

በዚህ ዓይነት ሥርዓት የሚሸኝ ሰው ረዥም እድሜ ኖሮ፣ አያት ለመሆን የበቃ ሰው መሆን አለበት።

ከዚህም በተጨማሪ በሺሌታ ባህል መሠረት የሚሸኝ አንድ ሰው አያት ለመሆን ከበቁት መካከል ታላቁ ወንድ መሆን አለበት።

ይኹን እንጂ የተባሉትን መስፈርቶች እስካሟሉ ድረስ በዚህ ሥርዓት የሚሸኙ ሁለቱም ጾታዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

በኮንሶ ዞን ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የቋንቋ እና ባህል አስተባባሪ የሆኑት፣ አቶ ገመቹ ገንፌ በዶ/ር ኦንጋይ ሀሳብ ይስማማሉ።

እንደ እነዚህ የኮንሶ ተወላጆች ገለጻ ሽሌታ አንድ የልጅ ልጅ ያየ አያት(አካ-ወንድ አያት፣ኦኮዮታ ሴት አያት) ከሞቱ የሚጨፈርላቸው የጭፈራ ዓይነት ነው።

በሽሌታ ወንድ፣ ሴት፣ ትልቅ ትንሽ ሳይባል ያለልዩነት ይጨፍራል።

ጭፈራውን ለማድመቅ ሁለት እንጨት ጉማድ(ካውላ) እርስ በእርስ በመምታት ይጨፈራል።

ጭፈራውን የሚመለከቱ ሰዎች በተለይ የሟቹ ዘመዶች ለጨፋሪዎቹ የገንዘብ ሽልማት ይሰጣሉ።

ጨፋሪዎቹ መጨረሻ በገንዘቡ መጠጥ ይጠጣሉ። የልጅ ልጅ ለማየት ያብቃችሁ ብሎ እንደማለት፣ በተጨማሪ ደግሞ የሟች ቤተሰቦችን ለማዝናናት ነው

ዘፈኑ እንዴት ይጀመራል?

ሰው በሞተበት ቅጽበት የደስታው ዘፈን አይጀመርም ይላሉ የማኅበረሰቡ ተወላጆች። በመጀመሪያ የቅርብ ዘመዶች በማልቀስ እርማቸውን ያወጣሉ።

ዘፈኑ ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ ነው የሚጀመረው።

ከዚያ በኋላም ዘፈኑ ለተወሰኑ ቀናት የሚቀጥል ይሆናል።

በበርካታ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ውስጥ ለቀስተኞች ወይንም ሐዘኑ የደረሰባቸው ሰዎች፣ ዘመዶቻቸው በሚሞቱበት ጊዜ ጥቁር ልብስ ለብሰው ሐዘናቸውን ይገልፋሉ።

በኮንሶ ባህል ግን ዘመድ የሞተባቸው ቤተሰቦች እና ጎረቤቶች ለቅሶው ቤት ሲሄዱ ነጭ ልብስ ይለብሳሉ።

ይኹን እንጂ በሺሌታ ሥነ ሥርዓት የሚሳተፉ ሰዎች የተለያየ ቀለም ያለው ልብስ መልበስ ይፈቀድላቸዋል።

ወደ ለቅሶው ቤት በሚኬድበት ጊዜ ግን ነጭ ልብስ ይለበሳል።

ሐዘን ከጥቁር ልብስ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም ይላሉ የማኅበረሰቡ ተወላጆች።

በሌላ በኩል ደግሞ በኮንሶ ባህል ስም ያልወጣለት ጨቅላ ሕጻን ሲሞት አይለቀስም።

ለሺሌታ የሚደረግ ዝግጅት

ወንዶች ለዘፈን፣ ከአንድ ክንድ የማይበልጥ ዱላ ቆርጠው ያዘጋጃሉ።

“ይህም ዘፈን ደስታን ለመግለጽ የሚዘፈን እንጂ ለሐዘን እና ለለቅሶ አይደለም። ሰዎች ይስቃሉ፣ ይቀልዳሉ፣ አያዝኑም” ይላሉ አቶ ገመቹ።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ዘፈን እያወጡ፣ የተገኙትን ሰዎች በማሞገስ የሚያገኙትን ገንዘብ ይካፈላሉ።

ዘፈኑም ሁለት ሰዎች ሆነው ተራ በተራ እየተቀባበሉ የሚዘፍኑት ዓይነት ነው።

ሴቶች ደግሞ በማጨብጨብ ያደምቁታል።

በዚህ ሁኔታ ታጅቦ ነው አስከሬኑ ወደሚቀበርበት ቦታ ሲወሰድ አጅበው ተከትለው ይሄዳሉ።

ዘፈኑን የሚዘፍኑ ሰዎች ጥቂት ሲሆኑ፣ በመጀመሪያ ዘመድ የሞተባቸው ሰዎች በር ፊት ለፊት ነው የሚዘፈነው።

የሚዘፍኑ ሰዎች ቁጥር እየበዛ ከሄደ ደግሞ ወደ አደባባይ ወጥቶ ይዘፈናል ይላሉ አቶ ገመቹ።

ይህም ባህል ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ መጥቶ አሁን መድረሱን የማኅበረሰቡ ተወላጆች ይናገራሉ።

የሺሌታ ሥርዓትን ማከናወን ወጪ ስላለውም በመተጋገዝ እንደሚከናወን አቶ ገመቹ ያስረዳሉ።

የጎሳ መሪ ሲሞት

እንደ ኮንሶ ባህል አንድ የኮንሶ ጎሳን የሚመራ ሰው ከሞተ፣ ሞተ ሳይሆን “ጥጋብ ይዟቸዋል ነው” የሚባለው።

ለጎሳ መሪዎችም የሚዘጋጅ የዘፈን ሥርዓት ከሺሌታ ጋር የሚመሳሰል ነው።

የጎሳውን መሪዎቹ ሴትም ሆኑ ወንድ ሲሞት የሚሸኝበት የዘፈን ዓይነት “መና” በመባል ይታወቃል።

እነዚህ የኮንሶ ተወላጆች እንደሚሉት ኮንሶ ዘጠኝ ጎሳዎች አሉት።

ድሮ የጎሳ መሪ በሞተበት ቦታ ላይ ለቀጣዮቹ ዘጠኝ ዓመታት አይዘፈንም አይጨፈርም ይባል ነበር።

ይህም የጎሳ መሪ ከሞተ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ነው የዘፈን ሥነ ሥርዓቱ መከናወን የሚጀመርለት ማለት ነው።

BBC Amharic

Exit mobile version