Site icon ETHIO12.COM

በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩ በ38 ግለሰቦች ላይ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ ተፈቀደ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በ3 መዝገብ የቀረቡ የ38 ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ተመልክቷል።

ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ያቀረበው የፌደራል ፖሊስ መርማሪ በቀዳሚነት በነመላክ ምሳሌ መንግስቱ መዝገብ የተካተቱ 16 ግለሰቦችን እና በነደበበ በሻህ ውረድ መዝገብ የተካተቱ በ12 ተጠርጣሪዎች አጠቃላይ 26 ግለሰቦች ላይ የሽብር ወንጀል የጥርጣሬ መነሻውን በፅሁፍም በቃልም አቅርቧል።

የተከሳሾች ጠበቆቻቸው ፖሊስ ባቀረበው የሽብር ወንጀል የጥርጣሬ መነሻ ላይ ማን ምን አደረገ? መቼ ? የሚሉት ተሳትፎዎች ተለይተው ባላቀረበበት እና በደፈናው የሽብር ወንጀል ተብሎ በቀረበበት ሁኔታ ላይ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ በመቃወም ተከራክረዋል።

የፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ የደንበኞቻችን የዋስትና መብት ሊፈቀድ ይገባል ሲሉም የዋስትና ጥያቄ አንስተዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ፥ ”በህቡዕ በመደራጀት የሽብር ተግባር ለመፈፀም የተደረገ እንቅስቃሴን በሚመለከት ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት ተቋም በመጣ የመነሻ ማስረጃ መሰረት በቀጣይ የተሳትፏቸውን ለይተን ለማቅረብ ነው ተጨማሪ ጊዜ የጠየቅነው” በማለት መልስ ሰጥቷል።

የተጠርጣሪዎች በዋስ ቢወጡ ማስረጃ ሊያሸሹብኝ ይችላሉ በማለት የዋስትና ጥያቄያቸውን በመቃወም ተከራክሯል።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ፥ ከግንቦት 18 በፊት በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ አስተዳደር በገላን እስር ቤት ታስረው እንደነበረ ጠቅሰው ፤ በዚህ ጊዜ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው አቤቱታ አቅርበዋል።

አካላዊ ጥቃት ተፈጽሞብናል ያሉ መላክ ምሳሌ የተባሉ ግለሰብ ልብሳቸውን በማውለቅ ለችሎቱ ዳኞች አሳይተዋል።

ኮማንደር ጌታሁን የተባሉ የቀድሞ የፌደራል ፖሊስ አባል የነበሩ ተጠርጣሪ ለሊት ላይ ተጠርጣሪዎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈፀም እንደተመለከቱ ለችሎቱ አብራርተዋል።

የችሎቱ ዳኞች በተጠርጣሪዎች ላይ ደረሰ ስለተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያውቀው ነገር ካለ ለማጣራት ለፖሊስ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ፥ በመርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ እኛ ጋር የመጡት ከግንቦት 18 ጀምሮ ነው በማለት መልስ ሰጥቶ ነበር።

በአንድ ተጠርጣሪ በኩል ግን በችሎት የተገኙት መርማሪ ሚያዝያ 27 ቀን ይዘዋቸው እንደነበር ጠቅሰው ፥ ለችሎቱ አቤቱታ አቅርበዋል።

መርማሪ ፖሊሱም በወቅቱ ተረኛ የዕስረኛ መኮንን ሆኖ ተጠርጣሪውን መመልከቱን እና ከዚያ በኋላ ግን እንዳልተመለከታቸው ጠቅሶ መልስ ሰጥቷል።

እንደ አጠቃላይ መዝገቡን የተመለከተው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጠርጣሪዎቹ ደረሰብን የሚሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማን እና መቼ እንደሆነ ጠቅሰው ፤ በዝርዝር በፅሁፍ እንዲያቀርቡ እና ፍርድ ቤቱም እንዲጣራ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት ገልጿል።

በፖሊስ የቀረበውን የጥርጣሬ መነሻ መዝገብና እና በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል የተነሳውን ክርክሩን የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ከወንጀሉ ውስብስብነትና ካለው ልዩ ባህሪ እና ከነባራዊ ሁኔታ አንጻር የተጠርጣሪዎቹን ዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ተጨማሪ ማጣሪያ ማድረግን አስፈላጊነትን በማመን የ14 ቀን ምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ተፈቅዷል።

በሌላ በኩል በዚህ ችሎት በቀለ ቢራራ፣ ፍቃዱ አሰፌ፣ ኤርሚያስ ደረሰ፣ ዳንኤል ደምሰው፣ በላይ ጋሻው፣ ሄኖክ ኪንገሻ፣ ክብረት ይርዳው፣ ደጉ አያሌው፣ መላኩ ደርብ እና ደፈሩ ሰማው የተባሉ ሌሎች 10 ተጠርጣሪዎችን በሚመለከት ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በማቀድ፣ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ግድያ ለመፈጸም፣ በህገወጥ መንገድ ለተደራጁ ቡድኖች ወታደራዊ ስልጠና በመስጠትና የጦር መሳሪያ በማስታጠቅና በመታጠቅ ጭምር ጫካ በመግባት ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ጦርነት ከፍተው ሲዋጉ ተማርከው የተያዙ ናቸው በማለት መርማሪ ፖሊስ የጥርጣሬ መነሻውን ለችሎቱ አቅርቧል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ በአማራ ክልል የብልፅግና ጽ/ቤት ኃላፊ ከነበሩት ከአቶ ከግርማ የሺጥላ ግድያ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች ናቸው በማለት ፖሊስ ለችሎቱ አብራርቷል።

ተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል በምን ዓይነት መሳሪያ ተማረኩ የሚለው አልተገለፀም ፤ ተማርከው የሚለው በደፈናው የቀረበ ግልጽነት የሚጓለው ነው በማለት ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መሰጠት የለበትም የሚሉ ነጥቦችን ጠቅሰው ተከራክረዋል።

በተጨማሪም አንድ ተጠርጣሪ በምርመራ ላይ በመሳሪያ በደረሰበት ጥቃት ተጎድቷል የሚለውን የጠበቃቸው መከራከሪያን በሚመለከት የችሎቱ ዳኛ እኛ ግምታዊ ክርክር አንመዘግብም በማለት ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ አድርገዋል።

በዚህም መነሻ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በሙሉ ትጥቅ ከመከላከያ ጋር ጦርነት ከፍተው ሲዋጉ እንደነበር በመግለጽ በዚህ ሂደት ላይ ተጠርጣሪው ሊሸሽ ሲል መመታቱን ጠቅሶ መልስ ሰጥቷል።

በጠበቆች በኩል ተጠርጣሪዎቹ ከመከላከያ ተማርከው ተይዘዋል ከተባለ ሊታይ የሚገባው በቀጥታ በመደበኛው እንጂ በሽብር አዋጁ ሊሆን አይገባም የሚሉ መከራከሪያዎችንም አንስተው ነበር።

እንዳጠቃላይ ክርክሩን የተከታተለው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጨማሪ ምርመራ መደረግ አስፈላጊነትን በማመን በዛሬው ቀጠሮ በተመሳሳይ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version