በአዲስ አበባና ሸገር ከተማ የሽብር ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

የጦር መሳሪያ በመያዝ በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተማ ላይ የሽብር ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ የክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።

የክስ መመስረቻ ጊዜ የፈቀደው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሲሆን፤ ተጠርጣሪዎቹ ያድንናኦል ሱራፌል ፣ ሚካኤል ዮሐንስ እና ወላቡ ደረጀ ይባላሉ።

ተጠርጣሪዎቹ የሸኔ የሽብር ቡድን አባል በመሆን፣ የሽብር ቡድኑ አመራሮች ጋር በመገናኘት፣ መረጃዎችን በማቀበል፣ የብሬን የጦር መሳሪያና 2 ሺህ 63 የክላሽ ጥይቶችን በሃዩንዳይ መኪና በመያዝ በአዲስ አበባና ሸገር ከተማ የሽብር ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ በፀጥታ ኃይሎች ክትትል ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መርማሪም ተጠርጣሪዎቹ በተደረገባቸው ብርበራ፥ በ3ኛ ተጠርጣሪ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የነዋሪነት መታወቂያዎችን እና ማህተሞችን መያዙን ገልጾ ለፍርድ ቤት ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

መርማሪ ፖሊስ በዛሬ ቀጠሮው ደግሞ ያድንናኦል ሱራፌል እና ሚካኤል ዮሐንስ በተባሉ ግለሰቦች ላይ ብቻ የምርመራ ስራውን አጠናቆ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን ለችሎቱ አስታውቋል።

3ኛ ተጠርጣሪ ወላቡ ደረጀን በሚመለከት ግን የምርመራ ስራ አለማጠናቀቁን ጠቅሶ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆበታል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ፤ ያድንናኦል ሱራፌል እና ሚካኤል ዮሐንስ በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የምርመራ መዝገብ ከፖሊስ መረከቡን ገልጿል።

የምርመራ መዝገቡን ተመልክቶ ክስ ለመመስረት እንዲያስችለውም በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 109 መሰረት የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ለክስ መመስረቻ ተብሎ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ እንደማይገባ በመከራከር የዋስትና መብታቸው እንዲከበር መጠየቃቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የጠየቁትን የዋስትና ጥያቄ በመቃወም ተከራክሯል።

የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ በዐቃቤ ሕግ ክስ የመመስረቻ ጊዜ የተጠየቀባቸው ያድንናኦል ሱራፌል እና ሚካኤል ዮሐንስ ላይ የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ለዐቃቤ ሕግ ፈቅዷል።

ፖሊስ ምርመራየን አላጠናቀኩበትም ያለውን ወላቡ ደረጀ በሚመለከት ግን ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም በማለት የ20 ሺህ ብር ዋስ አስይዞ ከእስር እንዲፈታ ፈቅዷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

See also  ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት መኖር እና የሚያስከትለው ውጤት

ይህንን ማስፈንጠሪያ ethio12news ተጭነው በቴሌግራም ገጻችን ይከተሉን

Leave a Reply